ሎዛ አበራ አዳማ ከተማን ተቀላቀለች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያለፉትን አራት ዓመታት ማጠናቀቅ የቻለችው የፊት አጥቂዋ ሎዛ አበራ ለአዳማ ከተማ ፊርማዋን በዛሬው እለት አኑራለች፡፡

በሀዋሳ ከተማ የእግር ኳስ ህይወቷን የጀመረችው አጥቂዋ ወደ ደደቢት በማምራት ምርጥ ጊዜያት ማሳለፍ ስትችል ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከማንሳቷ በተጨማሪ በግሏ ለተከታታይ አራት ዓመታት የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆና አጠናቃለች። በክረምቱ ከሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ተጫዋች ቱቱ በላይ ጋር ወደ ስዊዲን አምርታ በከንግስባካ ክለብ ውስጥ ረጅም ጊዜን የፈጀ የሙከራ ጊዜ ብታሳልፍም ኮንትራት ሳትፈርም በመመለሷ ያለፉትን ስድስት ወራት ያለ ክለብ ከቆየች ወዲህ ማረፊያዋ ሌላኛው የኢትዮጵያ ክለብ የሆነው አዳማ ከተማ መሆኑን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጧል፡፡

ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ መሪ የሆነው አዳማ ከተማ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ሰንጠረዡ እየተፎካከረች የምትገኘው ሴናፍ ዋቁማን ጨምሮ በርካታ የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾች እንደመያዙ የሎዛ መፈረም የአጥቂ ክፍሉን ይበልጥ አስፈሪ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *