ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ሾመ

የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሀላባ ከተማ ካሊድን መሐመድን በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል፡፡

ሀላባ ከተማ ለረጅም ዓመታት በአሰልጣኝ ሚሊዮን አካሉ ስር በመሆን ሲሰለጥን የቆየ ሲሆን አሰልጣኙ ከሶስት አመት በፊት ወደ ሻሸመኔ ከተማ አምርተው ዳግም ወደ ክለቡ 2009 ላይ ከተመለሱ በኋላ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በውጤት ማጣት ምክንያት ተቃውሞዎች በመበርከታቸው ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል። ክለቡ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በምክትል አሰልጣኝ መኮንን ገላነህ እየተመራ ያደረገ ቢሆንም በተመሳሳይ መኮንን ገላነህን ከኃላፊነት ካነሳ በኋላ ያለ አሰልጣኝ ቆይቶ ካሊድ መሐመድን ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ የክለቡ አሰልጣኝ በመሆን እንዲመራ ሹሟል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ በመሆን ሲሰራ የነበረው ካሊድ ወደ ዳሽን ቢራም አምርቶ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ በመሆንም ሰርቷል። ለጥቂት ጊዜያት በኢትዮጵያ መድን ወጣት ቡድን ቆይታ ያደረገው ካሊድ ለቀጣዩ አንድ ዓመት የሀላባ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን የሚያገለግል ይሆናል፡፡ 


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *