ደቡብ ፖሊስ ከአንጋፋው አማካይ ጋር ተለያይቷል

ባለፈው የውድድር ዓመት ዳግም ወደ እግር ተመልሶ መጫወት የጀመረውና በዓመቱ መጀመርያ ደቡብ ፖሊስን ተቀላቅሎ የነበረው አማካዩ ሙሉዓለም ረጋሳ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል።

ለሁለት ዓመታት ከሜዳ ከራቀ በኋላ አምና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት ከወራት በላይ የፈጀ የሙከራ ጊዜን አሳልፎ ለሀዋሳ ከተማ በመፈረም በድጋሚ እግር ኳስን መጫወት የጀመረው ሙሉዓለም መልካም የውድድር ዓመት በማሳለፍ በክረምቱ ለሌላኛው የሀዋሳ ክለብ ደቡብ ፖሊስ በአንድ አመት የውል ስምምነት በመቀላቀል ሲጫወት የቆየ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ወጣ ገባ እያለ በክለቡ መጫወት የቻለ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ከክለቡ ጋር እንደማንመለከተው ታውቋል።

በ1989 ከታችኛው  የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ በኢትዮጵያ እግርኳስ ከሚጠቀሱ ድንቅ አማካዮች አንዱ መሆን የቻለውና በ1994 የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ሙሉዓለም በ2000 ፈረሰኞቹን ከለቀቀ በኋላ በሰበታ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን እስከ 2007 ድረስ መጫወት ችሏል።

ደቡብ ፖሊስ ከሙሉዓለም ቀደም ብሎ ከግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ እና ቴዎድሮስ ሁሴን ጋር መለያየቱ የሚታወስ ሲሆን ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችንም ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *