የፈረንጆቹ 2014 ለኬንያው ታላቅ ክለብ ጎር ማሂያ በጥሩም በመጥፎም ጎኑ የሚታወስ ነው። ምንም እንኳን ክለቡ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ የኬንያን ፕሪምየር ሊግ በማንሳት በሜዳ ላይ ስኬታማ ሆኖ መቀጠል ቢችልም በክለቡ አስተዳደር በኩል የነበረው ችግር ጎልቶ የታየበት ዓመትም ነበር። የክለቡ ይፋዊ ስፖንሰር የነበረው ቱዞ የተሰኘ ወተት አምራች ኩባንያ ውሉን ካቋረጠ እና ክለቡ ከ1 ሚልየን ዶላር በላይ ያልተከፈለ ዕዳ እንዳለበት የኬንያ ግብር ሰብሳቢ ባለስልጣን ካስታወቀ በኋላ ከፍተኛ ጎር ማሂያ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር አጋጥሞት ነበር። በተወሰኑ የኬንያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ክለቡ በልምምድ ትጥቁ መጫወቱ እና በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ከማዳጋስካሩ CNAPS ክለብ ጋር ለማድረግ ወደ አንታናናሪቮ በሚጓዝበት ወቅት ለመልሱ ቲኬት የሚሆን ገንዘብ አውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩ ባለሃብት ለመለመን መገደዱ የችግሩን ጥልቀት የሚያሳይ ነበር።
በእንደዚህ ዓይነት የፋይናንስ ችግር ላይ የነበረው ጎር ማሂያ በጥር 2015 የዝውውር መስኮት የሊበርቲ ስፖርት አካዳሚ ተጫዋች የሆነ ሚካኤል ኦሉንጋ የተባለ ወጣት አጥቂ በውሰት ውል ማስፈረሙ በብዙዎች ገንዘብ ላለማውጣት የተደረገ ጥረት ተደርጎ ነበር የተወሰደው። ወጣቱ አጥቂ ወደ ጎር ማሂያ ከማምራቱ በፊት በተመሳሳይ የውሰት ውል ለተስከር እና ቲካ ዩናይትድ ክለቦች ተሰልፎ በተጫወተባቸው ሁለት ዓመታት ያስቆጠራቸው 11 ግቦች የሃገሪቱን ትልቁ ክለብ ለመቀላቀል በቂ ሆነው አልታዩም ነበር።
ሚካኤል ኦሉንጋ በችሎታው ጥርጣሬ የነበራቸውን ተመልካቾች ለማሳመን ግን ጊዜ አልፈጀበትም። ስኮትላንዳዊው አሠልጣኝ ፍራንክ ኑታል የልጁን የአካል ብቃት እና ግብ የማስቆጠር ችሎታ ተመልክተው ከክንፍ አጥቂነት ይልቅ የ9 ቁጥር ሚና ከሰጡት ጊዜ አንስቶ ከሩዋንዳዊው ሜዲ ካጌሬ ጋር የፈጠረው ጥምረት ግብ ማምረቱን ቀጥሏል። ኦሉንጋ በ2015ቱን የኬንያ ፕሪምየር ሊግ ያስቆጠራቸው 19 ግቦች ክለቡ በውድድር ዓመቱ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ዋንጫውን በማንሳት በ1976 እ.ኤ.አ. የሰራውን ታሪክ ከ39 ዓመት በኋላ እንዲደግም አስችለዋል። ጎር ማሂያ በታንዛኒያው የሴካፋ ክለቦች ሻምፒዮና 2ኛ ሆኖ ሲጨርስ ኦሉንጋም በአምስት ግቦች የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል።
ኦሉንጋ በሊጉ ላይ ያሳየው አስገራሚ አቋም ለኬንያ ብሔራዊ ቡድን እንዲጠራም መንገዱን ከፍቶለታል። የሃራምቤ ስታርስ አሠልጣኝ ቦቢ ዊሊያምሰን በመጋቢት ወር ከሲሼልስ ብሔራዊ ቡድን ጋር ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ለወጣቱ አጥቂ የመሰለፍ ዕድልን የሰጡት ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ኬንያ በዛምቢያ ናይሮቢ ላይ 2-1 ስትሸነፍ ኦሉንጋ የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ግቡን አስቆጥሯል። ሚካኤል ለክለቡ ካሳየው ምርጥ አቋም በተጨማሪ በዓመቱ የሃገሩን ማሊያ ለብሶ በተጫወተባቸው 9 ጨዋታዎች 4 ግቦችን ማስቆጠር መቻሉ 2015 ለ21 ዓመቱ አጥቂ ልዩ ዓመት እንደነበር የሚያሳይ ነው።
የሚካኤል ኦሉንጋ ብቃቶች
ሚካኤል ኦሉንጋ አንድ አጥቂ በተለይ በአፍሪካ እግርኳስ ውስጥ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ ተጫዋች ነው። ያለው ግዙፍ ተክለ ሰውነት የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች ላይ ብልጫ ወስዶ እንዲጫወት የሚረዳው ሲሆን ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶችን በግንባሩ የመግጨት ችሎታውን ለመዳኘት በሳለፍነው ሳምንት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ኬፕቨርዴ ላይ ያስቆጠረውን ግብ ማየት ይበቃል። ኳስን በሚያገኝበት ወቅት ያለው ፍጥነት እና ተጫዋቾችን አታሎ የማለፍ ብቃቱ በክንፍ አጥቂነት በተጫወተባቸው ጊዜያት ያዳበራቸው ችሎታዎች ናቸው። ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የሚያገኛቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ የመቀየር ችሎታው ጥሩ ሲሆን በግራ እግሩ አክርሮ ወደ ግብ የሚመታቸው ኳሶችም ኢላማቸውን የጠበቁ ናቸው።
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለሳውዝሃምፕተን የሚጫወተው የተከላካይ አማካይ ቪክተር ዋንያማ “ከሚካኤል ኦሉንጋ ጋር በብሔራዊ ቡድኑ አብረን ባሳለፍናቸው ጊዜያት የተረዳሁት ለአውሮፓ ክለቦች የሚመጥን ብቃት ያለው ተጫዋች መሆኑን ነው። እግርኳስ ከአንዱ ክለብ ወደሌላው በደረጃ እያደግክ የምትጫወተው ጊዜ የሚጠይቅ ስፖርት ነው። ኦሉንጋም በቅርቡ ችሎታውን ይበልጥ አሳድጎ ከአውሮፓ ክለቦች በአንዱ ሲጫወት እንደምናየው እርግጠኛ ነኝ፤” ሲል ነበር የብሔራዊ ቡድን አጋሩን ዕምቅ ችሎታ የገለፀው።
በእርግጥ ኦሉንጋ ተሰርቶ ያለቀ ተጫዋች ነው ለማለት አያስደፍርም። በተለይ ኳስን በተሳካ ሁኔታ የማቀበል እና ለቡድን አጋሮቹ የግብ አጋጣሚዎችን የመፍጠር ችሎታው ላይ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል። ለማጠቃለል ግን ከነድክመቶቹ ሚካኤል ኦሉንጋ በአሁኑ ሰዓት በምስራቅ አፍሪካ ከሚጫወቱ ምርጥ አጥቂዎች ውስጥ ስሙ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ነው።
ወደ ክለቦቻችን ለመዘዋወር ያለው ዕድል
በብሔራዊ ሊግ ከሚጫወቱ አጥቂዎች እንኳን የሚወዳደር ችሎታ ለሌላቸው ደካማ የምዕራብ አፍሪካ አጥቂዎች ብዙ ገንዘብ ማፍሰስ ልማዳቸው ያደረጉት የፕሪምየር ሊጋችን ክለቦች ያለባቸውን የሁነኛ ግብ አስቆጣሪ ችግር እንደ ኦሉንጋ አይነት ተጫዋች ያለጥርጥር ይቀርፍላቸዋል። በተለይ ረጅም ኳሶችን መሰረት አድርገው በአንድ የፊት አጥቂ (Target man) የሚጫወቱ የሊጉ ክለቦች ይህንን ተጫዋች አፅዕኖት ሰጥተው ሊከታተሉት ይገባል።
የሊጉ ከፍተኛ ተከፋይ ተጫዋች 1000 የአሜሪካን ዶላር ብቻ በሚያገኝበት ኬንያ መጫወቱ የሃገራችን ክለቦች የገንዘብ ካዝናቸውን ሳያራቁቱ በቀላል ደሞዝ ሊያስፈርሙት እንደሚችሉ የሚያሳይ ሲሆን ተጫዋቹ በኬንያ 4ኛ ሊግ የሚገኘው ሊበርቲ ስፖርትስ አካዳሚ ንብረት መሆኑ የዝውውሩን ዋጋ ሊያወርደው ይችላል።
ኦሉንጋ በኬንያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት የጂኦ-ስፓሻል ኢንጂነሪንግ ተማሪ መሆኑ ‘ኢንጂነሩ’ የሚል ቅፅል ስም ያሰጠው ሲሆን ለትምህርቱ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ይነገራል። ተጫዋቹ ከኬንያ ሊግ የሚወጣ ከሆነ በሚሄድበት ሃገር ትምህርቱን የመቀጠል ፍላጎቱ ምናልባትም በደቡብ አፍሪካው ፕሪምየር ሶከር ሊግ ክለቦች ሱፐርስፖርት ዩናይትድ እና ቢድቨስት ዊትስ ያሳለፈው የሙከራ ጊዜ እንዳይሳካ ካደረጉ ምክኒያቶች ውስጥ የሚጠቀስ ነው።