ከፍተኛ ሊግ ሐ | የምድቡ መሪ ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ሲጥል ወራቤ፣ ሻሸመኔ እና ነጌሌ ቦረና አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ጅማ አባ ቡና በሜዳው ከመሪው ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርቷል። ነጌሌ ቦረና እና ሻሸመኔ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ ሲያሸንፉ ስልጤ ወራቤ በሜዳው ድል አስመዝግቧል።

09:00 ላይ በጅማ ስታድየም ጅማ አባ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና 1-1 ተለያይተዋል። ሳቢ ያልሆነና ቀዝቃዛ የጨዋታ እቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ እድሎችን በመፍጠርና ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ሀድያዎች ከባለሜዳዎቹ አንፃር የተሻሻሉ ነበሩ። የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ በ13ኛው ደቂቃ ፍራኦል መንግስቱ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን እዩኤል በግንባሩ የሞከረውና የወጣው አጋጣሚ፣ በድጋሚ ከቀኝ መስመር በ14 ኛው ደቂቃ እዩኤል ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ የሞከረውን የአባቡናው ግብ ጠባቂ ሙላት ዓለማየው እንደምንም ያወጣበት በሀድያዎች በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ባለሜዳዎቹ አባ ቡናዎች ከመስመር ተከላካዮች በኩል ለግዙፉ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው በረጅሙ የሚሻገሩት ኳሶች ውጤታማ አልነበሩም። በ30ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ አብዱልላዚዝ ሚፍታ በግንባሩ ገጭቶ የሀድያ ተከላካይ ከመስመር ላይ በግንባሩ ከመለሰው ሙከራ ውጭ የሀድያን ተከላዮች አልፈው ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በ45ኛው ደቂቃ ግን በሀድያ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው አስቆጥሮ በባለሜዳዎቹ 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ቤት አቅንተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ዳግም በቀለን በኤሪክ ሙራንዳ በመተካት ጨዋታውን የጀመሩት ሀድያዎች ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ አባቡናዎች ላይ ጫና በመፍጠር መጫወት ችለዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የኳስ ቁጥጥርም ሆነ ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በ51ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር አብደላ መሐመድ ያሻገረው ኳስ ቀጥታ የግቡን አግዳሚ ብረት ለትማ የወጣችበት አጋጣሚ፣ በ54ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ አባ ቡና የግብ ክልል ከገቡ በኃላ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት የተገናኘው ስንታየው አሸብር ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነበር፡፡ ሀዲያዎች ተደጋጋሚ ጫና ማድረጋቸውን በመቀጠል በ77ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ዮሴፍ ድንገቱ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ሀዲያዎች ውጤት ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዘው ታይተዋል። አባቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ እንቅስቃሴ ከእረፍት በፊት ያስቆጠሩትን ግብ ለማስጠበቅ ወደ ኃላ አፈግፍገው መጫወታቸው እንዲሁም በተደጋጋሚ ሰዓት ለማዘግየት ያደረጉት ጥረት ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት 1-1 ተጠናቋል።

ቡታጅራ ከተማ 1-2 ሻሸመኔ ከተማ
(በአምሀ ተስፋዬ)

በግብ ረገድ ቀዳሚ መሆን የቻሉት እንግዳዎቹ ሻሸመኔዎች በአብርሀም ዓለሙ አማካኝነት ሲሆን ባለ ሜዳዎቹ የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቂያ ላይ ክንዴ አቡቹ አቻ አድርጓቸዋል። ለረጀረም ደቂቃዎች በዚሁ ውጤት በዘለቀው ጨዋታ በ87ኛው ደቂቃ አብርሀም ዓለሙ በድጋሚ ሻሸመኔን መሪ ማድረግ ሲችል ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ጨዋታው ለረጅም ደቂቃዎች ሊቋረጥ ችሏል። በጉዳዩ ዙርያ ከሁለቱ ቡድኖች አስተያየት አካተናል።

የቡታጅራ ቡድን መሪ

በ88ኛው ደቂቃ ላይ የሻሸመኔ ግብ ጠባቂ ከኛ አጥቂ ጋር በመጋጨት ወደ መሬት በመውደቅ ተርገጫለው በሚል ውዝግብ ውስጥ የተገባ ሲሆን ሻሸመኔዎች ልዩ ሀይል ካልመጣ የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ልዩ ኃይል እስከሚመጣ ጨዋታው ቆሟል።

የሻሸመኔ አሰልጣኝ መስፍን አህመድ

በ88ኛው ደቂቃ ላይ የኛ በረኛ ግጭት ደርሶበት በሚወድቅበት ወቅት በመጎዳቱ እዛው ሲወድቅ ደጋፊዎቹ ለመግባት ጥረት አድርገዋል። አንደኛው የመስመር ዳኛም ወደ መሐል ሜዳ ፈጥኖ በመግባት ያለውን የደጋፊ ተፅዕኖ ማሳወቅ ችሏል። ይህን ደሞ እኛ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በመስጋት ልዩ ኃይል እንዲመጣ ጠይቀናል። ከብዙ ደቂቃ በኋኃላ 10 ደቂቃ ተጨምሮ ጫዋታው ተጠናቋል።

ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ነቀምት ከተማን አስተናግዶ በፀደቀ ግርማ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል። ወደ ሚዛን አማን ያመራው ነጌሌ ቦረና 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ለነገሌ ቦረና በ33ኛው ደቂቃ ላይ ምናሉ ተፈራ ቀዳሚዋን ሲያስቆጥር የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ኃይለየሱስ ኃይሉ ለባለሜዳዋቹ ግብ አስቆጥሮ አቻ መሆን ቢችሉም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ያለው ተሾመ ቦረናን አሸናፊ የምታደርገውን ግብ አስቆጥሯል። ሺንሺቾ ላይ ከንባታ ሺንሺቾ ከ ካፋ ቡና ያለጎል አቻ ሲለያዩ አርባምንጭ ከተማ ከ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ የሚያደርጉት ጨዋታ ነገ ይካሄዳል።

 


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *