በፕሪምየር ሊጉ ማን ይበልጥ ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻቸ ?

ቀጣዮቹ ቁጥራዊ መረጃዎቻችን በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች የትኞቹ ተጫዋቾች በርካታ ግቦችን አመቻችተዋል እንዲሁም እነማን በይበልጥ በግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበሩ የሚሉትን እና ተያያዥ ጥያቄዎች ይመልሳሉ።

በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር በተከናወኑት 120 ጨዋታዎች 227 ግቦች ተቆጥረዋል። ከነዚህም ግቦች ውስጥ 166ቱ ኳሶች ከመረብ እንዲያርፉ ከአስቆጣሪዎቹ በተጨማሪ አጋጣሚዎቹን ያመቻቹ ተጫዋቾች እርዳታ አስፈላጊ ነበር።

በመሆኑም በጥቅሉ 86 ተጫዎቾች በግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ ሲካተቱ አጋጣሚዎቹን በመፍጠሩ ሂደት ውስጥ ደግሞ በድምሩ 101 ተጫዋቾች ተመዝግበዋል። ከነዚህ ውስጥ 59 ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው አንድ ግብ የሆነ ኳስን አመቻችተዋል። በክለብ ደረጃ ስንመለከታቸው በወላይታ ድቻ ፣ አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ሁለት ፤ በድሬዳዋ ከተማ ፣ ደቡብ ፖሊስ ፣ ስሐል ሽረ ፣ ወልዋሎ ዓ /ዩ እና ደደቢት ሦስት ፤ በመቐለ 70 እንደርታ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ጅማ አባ ጅፋር ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ አራት ፤ በፋሲል ከተማ እና መከላከያ አምስት እንዲሁም በሲዳማ ቡና ስምንት ተጫዋቾች በዝርዝሩ ውስጥ መካተት ችለዋል።

ቀጣዩን ደረጃ የሚወስዱት ሁለት ግቦችን ማመቻቸት የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው። እነዚህ በቁጥር 26 ሲሆኑ በድምሩ ለ52 ግቦች መቆጠር ምክንያት መሆናቸውን እንረዳለን። ከመካከላቸውም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ አራት ፤ ፋሲል እና መቐለ ሦስት ፤ ሲዳማ ፣ ሀዋሳ እና ባህርዳር ሁለት እንዲሁም አባ ጅፋር ፣ ቡና ፣ መከላከያ ፣ ድቻ ፣ ሽረ እና አዳማ አንድ አንድ ተጫዋቾችን አስመዝግበዋል።

በሦስተኛ ደረጃ ዕኩል ሦስት ኳሶችን ማመቻቸት የቻሉ 11 ተጨዋቾችን እናገኛለን ። ሱሌይማን ሰሚድ እና በረከት ደስታ ከአዳማ ከተማ ፣ ዲዲዬ ለብሪ እና መስዑድ መሀመድ ከጅማ አባ ጅፋር ፣ ብሩክ በየነ እና ታፈሰ ሰለሞን ከሀዋሳ ከተማ ፣ ብሩክ አየለ እና በረከት ይስሀቅ ከደቡብ ፖሊስ ፣ ወንድሜነህ ዓይናለም ከሲዳማ ቡና ፣ ዮናስ ገረመው ከመቐለ 70 እንደርታ እና ቸርነት ጉግሳ ከወላይታ ድቻ በዚህ ውስጥ ይካተታሉ።

– የሀዋሳው አማካይ ታፈሰ ሰለሞን ስድስት ግቦችን በማስቆጠሩ በድምሩ አስራአንድ ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ ብሩክ በየነ እና ወንድሜነህ ዓይናለም ደግሞ በአራት ግቦች ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።

– የደቡብ ፖሊሶቹ በረከት ይስሀቅ እና ብሩክ አየለ ለጎል ያመቻቿቸው ሦስት ሦስት ጎሎች ቡድናቸው ጅማ አባ ጅፋርን 6-1 በረታበት ጨዋታ የተመዘገቡ ነበሩ።

– የአዳማ ከተማው የመስመር ተከላካይ ሱሌይማን ሰሚድ ከ10ኛው እስከ 12ኛው ሳምንታት በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ የሆኑ ኳሶች ማመቻቸት ችሏል።

አራት ኳሶችን ለግብ ያመቻቹ ተጫዋቾች

አማኑኤል ገብረሚካኤል – መቐለ 70 እንደርታ

– የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት ከምንይሉ ወንድሙ ጋር በመሆን በ11 ግቦች በመምራት ላይ የሚገኘው የመቐለዎች አጥቂ አማኑኤል አራት ጎሎች እንዲቆጠሩ ደግሞ ቀጥተኛ ሚና ተወጥቷል። በዚህም በ15 ግቦች ላይ በቀጥታ በመሳተፍም ጭምር በሊጉ ቀዳሚ ነው። የፊት አጥቂው ከክፍት ጨዋታ ለሳሙኤል ሳሊሶ ሁለት ለያሬድ ከበደ እና ኦሰይ ማወሊ ደግሞ አንድ አንድ ኳሶችን በማመቻቸት ቡድኑ ዙሩን በመሪነት እንዲጨርስ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

ሐብታሙ ገዛኸኝ – ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ጥሪ እየተደረገለት የሚገኘው ወጣቱ የመስመር አጥቂ ሐብታሙ ገዛኸኝ አራት ግቦችን በማስቆጠር አራት ጊዜ ደግሞ ከክፍት ጨዋታዎች ኳሶችን በማመቻቸት በጥቅሉ በስምንት ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኗል። ተጫዋቹ በተለያዩ አራት ጨዋታዎች ፀጋዬ ባልቻ ፣ ወንድሜነህ ዓይናለም ፣ አዲስ ግደይ እና መሐመድ ናስር ላስቆጠሯቸው ግቦች ነበር ኳሶችን ያመቻቸው።

ደስታ ዮሃንስ – ሀዋሳ ከተማ

ካለው ደረጃ አንፃር በተደጋጋሚ ጉዳቶች ሳቢያ በቂ የጨዋታ ጊዜን ያላገኘው የመስመር ተከላካዩ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦች በተጨማሪ ታፈሰ ሰለሞን ፣ እስራኤል እሸቱ ፣ ገብረመስቀል ዱባለ እና አዳነ ግርማ ከመረብ ያገናኟቸው ኳሶችን በማመቻቸት ሰባት ጎሎች ላይ በቀጥታ ተሳተፏል። ሆኖም ተጫዋቹ አጋጣሚዎቹን የፈጠረው በዙሩ የመጀመሪያ ሰባት ጨዋታዎች ወቅት ሲሆን የተሻለ የመሰለፍ ዕድሉ ቢኖረው ከዚህ በተሻለ በግቦች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ይችል እንደነበር መረዳት ይቻላል።

አምስት ኳሶችን ለግብ ያመቻቹ ተጫዋቾች

ዳዊት እስጢፋኖስ – መከላከያ

የመለላከያ የጨዋታ አቀጣጣይ የሆነው ዳዊት እስጢፋኖስ ምንም ግብ ማስቆጠር ባይችልም አማካይ ክፍሉን በፊት አውራሪነት በመራባቸው ጨዋታዎች አምስት ኳሶችን ለአግቢዎች ማድረስ ችሏል። ከነዚህም ውስጥ ለምንይሉ ወንድሙ ግቦች ሁለት ኳሶችን ከቅጣት ምት ማሻገር የቻለ ሲሆን በክፍት ጨዋታ ደግሞ ለፍሬው ሰለሞን ሁለት እንዲሁም ለፍቃዱ ዓለሙ ደግሞ አንድ ኳስን አመቻችቷል።

ዘላለም ኢሳይያስ – ደቡብ ፖሊስ

ወደ ግብ የተቀየሩ የማዕዘን ምቶችን በማሻገር ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈው ዘላለም ኢሳይያስ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እና አምስት በማመቻቸት ቡድኑ ከመረብ ካገናኛቸው 16 ግቦች በሰባቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። ከነዚህም መካከል ለዘሪሁን አንሼቦ ሁለት ጊዜ ለዮናስ በርታ ደግሞ አንዴ ያደረሳቸው ኳሶች ከማዕዘን ምት የተነሱ ሲሆኑ ለሄኖክ አየለ ያደረሳቸው ሁለት ኳሶች ደግሞ ከክፍት ጨዋታ የተገኙ ነበሩ።


© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *