አዳማ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን አሳደገ

ያለፉትን ዓመታት ለታዳጊዎች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እና ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ ስኬታማ እየሆነ የመጣው አዳማ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ከተስፋ ቡድኑ አሳደገ።

ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖቹ በወጥነት ያለፉትን አምስት ዓመታት ውጤታማ ውድድሮችን በማድረግ ብቻ ሳይሆን ወደ ዋናው ቡድን ታዳጊዎችን በማሳደግ በሊጉ ካሉ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ክለቦች አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ ብሩክ ቦጋለ እና ዳግም ታረቀኝን በአረንጓዴ መታወቂያ (ቲሴራ) አሳድጓል።

ብሩክ ቦጋለ የግራ መስመር ተከላካይ ሲሆን ያለፉትን ሦስት ዓመታት ከ17 ቡድን ጀምሮ በመጫወት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ነው። ብሩክ በአዳማ ዋናው ቡድን ከተጫወተ በኋላ ወደ ወላይታ ድቻ በማምራት አሁን በከፍተኛ ሊግ ለገላን ከተማ በመጫወት ላይ የሚገኘው የወንደሰን ቦጋለ ታናሽ ወንድም ነው። ሌላው ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ዳግም ታረቀኝ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ሲሆን በአዳማ ከታችኛው የእድሜ እርከን ጀምሮ ያደገ ከመሆኑ ባሻገር በ2010 ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ስም ውስጥ ተፎካካሪ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር።

አዳማ ከተማ ከታዳጊ እና ወጣት ቡድኑ ከ2006 ጀምሮ ታከለ ዓለማየሁ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ቡልቻ ሹራ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ በረከት ደስታ፣ መናፍ ዐወል እና ፉአድ ፈረጃ የመሳሰሉ ተጫዋቾን ያፈራ ሲሆን በሲዳማ ቡና እየተጫወተ የሚገኘው ዮናታን ፍስሐም መነሻው አዳማ ከተማ ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *