የጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ ራሳቸውን ከኃላፊነት አነሱ

ከዓመቱ መጀመርያ አንስቶ ጅማ አባጅፋርን በዋና አሰልጣኝነት እያገለገሉ የቆዩት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ራሳቸውን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታወቁ።

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ያለፉትን ስድስት ወራት ቡድኑን በቴክኒክ ወንበር ላይ ተቀምጠው መምራት ባይችሉም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ጅማ አባ ጅፋርን እያገለገሉ መቆየታቸው ይታወሳል። ሆኖም የሁለተኛው ዙር የውድድር አጋማሽ ከመጀመሩ አስቀድሞ በነበረው የዝግጅት ወቅት እንዲሁም ከአዳማ ከተማ እና ከመከላከያ ጋር በተደረጉት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በመገኘት ቡድኑን አለመምራታቸው ይታወቃል።

አሰልጣኝ ዘማርያም ማምሻውን ለሶከር ኢትዮጵያ ራሳቸውን ከኃላፊነት ያነሱበትን ምክንያት ተናግረዋል። ” ያለፉት ሰባት ወራት ክለቡን ሳገለግል ላገኘው የሚገባውን ክፍያ ሊፈፀመልኝ አልቻለም። ይህን በተደጋጋሚ ብጠይቅም ከቃል ውጭ ምንም ነገር በተግባር ሊፈፀምልኝ ባለመቻሉ ራሴን ከዛሬ ጀምሮ ከኃላፊነት ለማንሳት ተገድጃለው። እስከ ዛሬ ድረስ በነበረኝ ቆይታ የክለቡ አመራር፣ ተጫዋቾች በተለይ ደግሞ የክለቡ ደጋፊዎቹ ላደረጉልኝ ነገር ሁሉ አመሰግናለው። ” ብለዋል

የጅማ አባጅፋር እግርኳስ ክለብ የበላይ አመራሮች በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ካለ በቀጣይ የምናስተናግድ መሆናችንን ከወዲሁ መግለፅ እንወዳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *