ፌዴሬሽኑ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በታዳጊዎች ላይ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከኢፌዴሪ ሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እድሜያቸው ከ13-15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ላይ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ እና የውይይት መድረክ ዛሬ ከጠዋቱ 3:00 ጀምሮ በካፒታል ሆቴል ተደርጓል፡፡ 15 ዩኒቨርስቲዎች የሚሳተፉበት ይህ የልማት ፕሮግራም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የባለሙያ እና የገንዘብ አቅምን ከአካባቢው የእግርኳስ እምቅ አቅም ጋር በማቀናጀት በእግርኳሱ ላይ ለውጥ ለመፍጠር ያለመ ነው።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም፣ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንና ተወካዮች በዕለቱ የተገኙ ሲሆን አቶ ኢሳይያስ ጂራ በመክፈቻ ንግግራቸው “በዓለም ላይ እግር ኳስ ተወዳጅ ስፖርት ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያም ይህን ተወዳጅ ስፖርት በአፍሪካ ከመሰረቱ አንዷ ናት። ሆኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ በውጤትም ሆነ በእድገቷ ወደ ኋላ እየቀረች ነው። ይህን ከስር መሠረቱ ለማስቀረት እና ውጤታማ ለመሆን በወጣቶች ላይ ጠንክሮ ለመስራት ቆርጠን ተነስተናል። ለዚህም ደግሞ ዩኒቨርሲዎች ትልቁን ሚና ይወስዳሉ። እኛም በእናንተ እምነቱ ስላለን በጋራ ለመስራት ተዘጋጅተናል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን ለአላማው ቁርጠኛ በመሆን ላሳየው ተነሳሽነት ምስጋናዬን ማቅረብም ፈልጋለሁ” ብለዋል።

ከአቶ ኢሳይያስ ንግግር በኋላ የዚህ መድረክ መዘጋጀት እና ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር መሠራት ባለባቸው የታዳጊዎች ልማት ዙሪያ በፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዲፓርትመንት ተወካይ መኮንን ኩሩ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡ አቶ መኮንን በገለፃቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ ስላሉ ዲፖርትመንቶች፣ ስለ ፌድሬሽኑ አሰራር፣ በእግርኳሱ ስላሉ ችግሮች እና መፍትሄዎች ላይ ያተኮሩ ሲሆን በመቀጠል ስለ ዛሬው ጉዳይ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ ከተነሱት ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ላይ ትኩረትን በማድረግ ልዩ የግብ ጠባቂዎች ብቻ አካዳሚ ማቋቀም ይገኝበታል። በአንድ ዩኒቨርሲቲ እድሜያቸው ከ13 እና 15 በታች የሆናቸው  በሁለቱም ፆታ ወደፊት ቁጥሩ የሚያድግ ከ120 በላይ ተጫዋቾችን በማቀፍ እንዲሰሩ ማድረግ፤ ለነዚህም ድጋፍና ክትትል ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሆን በመስራት ከሁለት ዓመታት በኋላ ከ13 ዓመት በታች ብቻ ያሉትን አቅፎ ለመስራት እንደታሰበም ባቀረቡት ገለፃ ላይ ተጠቅሷል።

በመጀመሪያው ዙር 1.800 በላይ ሰልጣኞችን የሚያቅፈው ይህ ፕሮግራም ለጊዜው 15 ዩኒቨርሲቲዎችን አሳታፊ ያደረገ ሲሆን በሂደት ግን ቀሪዎቹን ዩኒቨርሲቲዎች በተመሳሳይ በሁለተኛው ዙር በመጥራት በጋራ ለመስራት በቀጣይ ታስቧል፡፡ በመጀመርያው ዙር የሚሳተፉትና በዛሬው እለት የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት ሀዋሳ፣ ባህርዳር፣ ወለጋ፣ አርባምንጭ፣ ሶዶ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ ሀረማያ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ አዲስ አበባ፣ መቐለ፣ ዓዲግራት፣ ድሬዳዋ እና አሶሳ ዩኒቨርሲዎች ናቸው።

በአቶ ኢሳይያስ መድረክ መሪነት ከተሳታፊ የዩኒቨርስቲ ተወካዮች ለተነሳለቸው ጥያቄዎች እና ሀሳቦች ዙሪያ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደገብርኤል የመዝጊያ ንግግርን አድርገዋል፡፡ “የዛሬው የሰነድ መፈራረማችን የነገውን አዳነ ግርማ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ሳላሀዲን ሰዒድ፣ ብርቱካን ገብረክርስቶስ እና ሎዛ አበራን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ለማፍራት ይረዳናል፡፡ የእግር ኳስ ልማት ስራ ለፌዴሬሽኑ ብቻ የሚተው አይደለም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ አቅሙ ስላለ የመፍትሔው አካል ለመሆን በጋራ መስራቱ እግርኳሱ አንድ እርምጃ እንዲራመድ ይረዳል። ” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *