38ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ ወደ ወሳኝ ምእራፍ ተሸጋግሯል፡፡ ዛሬ በተደረጉ ሁለት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎችም ዩጋንዳ እና አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግረዋል፡፡
በ7፡00 ተጋባዧ ማላዊን የገጠመችው ዩጋንዳ 2-0 አሸንፋለች፡፡ የቫይፐርሱ አጥቂ ፋሩክ ሚያ በ5ኛው ደቂቃ ዩጋንዳን ቀዳሚ ሲያደርግ ሲዘር ኦኩቲ በ47ኛው ደቂቃ 2ኛውን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የዩጋንዳው አምበል ፋሩክ ሚያ የጨዋው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
ቀጥሎ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና የታንዛንያ ጨዋታ እንደከዚህ ቀደሙ በርካታ ተመልካች ያልተመለከተው ፣ ሜዳ ላይ ውዝግብ የነበረበት እና ኢትዮጵያ በዘንድሮው ውድድር የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየችበት ሆኖ በዋልያዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ታንዛንያ በአንበሉ ጆን ቦኮ የ45ኛ ደቂቃ ግብ ስትመራ ብትቆይም በ57ኛው ደቂቃ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ ጋቶች ፓኖም ኢትዮጵያን አቻ አድርጓል፡፡ የፍፁም ቅጣት ምት ለኢትዮጵያ መሰጠቱን ተከትሎ የታንዛንያ ተጫዋቾች በስሜታዊነት ሲቃወሙ እና ግርግር ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡
የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ 1-1 በመጠናቀቁ አሸናፊውን ለመለየት በቀጥታ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሲያመሩ ኢትዮጵያ በጋቶች ፣ በኃይሉ ፣ መሃመድ እና አስቻለው አማካኝነት ሁሉንም ወደ ግብ ቀይራለች፡፡ ከታንዛንያ በኩል በጆን ሙኩዴ እና ሾማሪ ካሞምቤ የተመቱትን የፍፁም ቅጣት ምቶች አቤል ማሞ አድኗቸዋል፡፡ ኢትዮጵያም በፍፁም ቅጣት ምት 4-3 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተሸጋግራለች፡፡
በዚህ ጨዋታ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ጨምሮ ወሳኝ የግብ ሙከራዎችን ያዳነው አቤል ማሞ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
ኢትዮጵያ በግማሽ ፍፃሜው ዩጋንዳን ሀሙስ ትገጥማለች፡፡