” እዚህ ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ” ዳንኤል አጄይ

ባለፈው ዓመት የታንዛኒያው ሲምባን በመልቀቅ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ያመራው ዳንኤል አጃዬ በዓምና ቆይታው ድንቅ ጊዜ በማሳለፍ በሊጉ ዝቅተኛ ጎል የተቆጠረበት ግብ ጠባቂ መሆን ሲችል ከቡድኑ ጋር የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን፣ በግሉ ደግሞ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ አጠናቋል።

ዘንድሮ ክለቡ በአምናው ወጥ አቋም እና ውጤታማነት ላይ ባይገኝም የ29 ዓመቱ ጋናዊ ዘንድሮም በጥሩ ብቃቱ ላይ ይገኛል። በሁለተኛው ዙር ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግብ ሳያስተናግድ በመውጣትም በወቅታዊ ድንቅ አቋም ላይ ይገኛል።

በሀገሩ ክለቦች ሊበርቲ ፕሮፌሽናልስ እና ሚዴአማ፣ በደቡብ አፍሪካው ፍሪ ስቴት ስታርስ እና በታንዛኒያው ሲምባ ተጫውቶ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ዳንኤል አጄይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጠር ያለ ቆይታ በእግርኳስ ህይወት ጉዞው፣ በተለያዩ ጊዜያት ከጨዋታ ስላራቀው የግል ጉዳይ እና ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ አስተያየቱን ሰጥቷል።

የእግርኳስ ጅማሮህ ድንቅ ነበር። የ2009 የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ስታነሳ ከነ አንድሬ አዬው፣ ጆናታን ሜንሳህ እና ዶሚኒክ ኤዴህ ጋር የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነበርክ። የ2010 አፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ድረስ የተጓዘው የጋና ስብስብም አካል ነበርክ… ከዚህ አጀማመር ያልቀጠልክበት ምክንያት ምንድነው?

በእኔ አመለካከት በ2009 ከኛ በፊት የትኛውም የአፍሪካ ሀገር ያላሳካውን የዓለም የ20 ዓመት በታች ዋንጫ አሸናፊ ከነበርን በኋላም የነበረው ጊዜ በትክክል ጥሩ እና ወጥ ነበር። በአፍሪካ ዋንጫ በአንጎላ አዘጋጅነት በተደረገው ላይ ከግብፅ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለፍፃሜ የደረሰው የቡድኑ አባል ነበርኩ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን ባዘጋጁት ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ላይም ተሳታፊ ነበርኩ፣ የ2010 የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ አምልጦኛል፣ በ2011 የመላው አፍሪካ ውድድሮች ማፑቶ ላይ በጋና ታሪክ በውድድሩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ከነበረው የቡድኑ አካል ነበርኩ። በተጨማሪም ጅማ አባጅፋር ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባደገበት ዓመት የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ በሆነው ቡድን ውስጥ የቡድኑ አባልና የታሪኩም አካል ነኝ። አባጅፋርን በተቀላቀልኩበት ዓመት ውጤታማ ነበርኩ፤ በሊጉ አነስተኛ ግብ የተቆጠረብኝ በአንድ ጨዋታ ከሁለት ግብ በላይ አልተቆጠረብኝም። ከዚህም በላይ ለመስራት ክለቤንና ቤተሰቤን ለመርዳት ጠንክሬ እየሰራሁ እገኛለሁ።

ከጋና ወደ ደቡብ አፍሪካ፤ ቀጥሎም ወደ ታንዛንያ አሁን ኢትዮጵያ… የእስካሁኑ የእግርኳስ ጉዞህስ በጠበቅከው መልኩ እየተጓዘ ነው?

ሰዎች ወደ አውሮፓ ወይም ወደ ሌሎች ሀገራት ሄደህ ለምን አትጫወትም ይሉኛል። ነገር ግን እዚህ ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ። አዳዲስ ነገሮችን እያወቅኩ ነው። በአሰልጣኞቼ እና እዚህ ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ፡፡ የትም ብትሄድ ለመማርና አዳዲስ ነገሮችን ዝግጁ መሆን አለብህ፤ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ብዙዎች ተቃውመውኝ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ምርጫዬ ትክክል ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ጥሩ የእግርኳስ ሀገር ናት፤ ብዙ ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾች አሏት። በብሄራዊ ቡድናችሁም ሙሉ ለሙሉ በሀገራችሁ ዜጎች ነው የምትጠቀሙት። ብዙ የዓለማችን ሀገራት የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች ለብሄራዊ ቡድናቸው ሲያጫውቱ እንመለከታለን። በኢትዮጵያ ግን በብሄራዊ ቡድኑ የኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው የሚጫወቱት። ለሀገራችሁ ተጫዋቾች ያላችሁን እምነት በእያንዳንዱ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያውያንን በመጠቀም ታሳያላችሁ። ሌሎች ሀገሮች የሀገራቸውን ተወላጆች ላይ እምነት የላቸውም። ሀገሬን ጋና ጨምሮ ሌሎች ሀገራት እንደዚህ አይደለም፤ አቋራጭን ነው የምንጠቀመው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የእግርኳስ ሀገር ናት ያልኩት። በአጠቃላይ እዚህ የመጣሁት ዋንጫዎችን ለማንሳትና አዳዲስ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ነው።

አምና በጅማ ድንቅ ጊዜ ከማሳለፍህ በተጨማሪ የሊጉ ዝቅተኛ ጎል የተቆጠረበት ግብ ጠባቂ ነበርክ… የዘንድሮው አቋምህ ባንተ እይታ ምን ይመስላል?

እስካሁን 15 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፌ 7 ግብ ብቻ ነው የተቆጠረብኝ። በሀዋሳ 3፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2 እና በመቐለ 2 ግቦች ናቸው የተቆጠሩብኝ። እነዚህም ግቦች ከሜዳችን ውጭ የቆጠሩብኝ ናቸው። በሜዳችን ባደረግናቸው ጨዋታዎች ምንም ግብ አላስተናገድኩም። በእርግጥ እኔ ባልነበርኩባቸው ጨዋታዎች ላይ በደቡብ ፖሊስ 6 በድሬዳዋ በሜዳችን 3 ግብ አስተናግደናል። ከተመለስኩ በኋላ ግን ተስተካክሏል። ለዘጠኝ ጨዋታዎችም ግብ አልተቆጠረብኝም። ስለዚህ በዚህ የውድድር ዓመት ለእኔ ጥሩ ነው ማለት እችላለሁ፡፡

ዘንድሮ በግልህ ጥሩ ብትሆንም ቡድኑ በሜዳ ላይ እየተቸገረ ነው። ይህን እንዴት ታየዋለህ?

ባለፈው ዓመት አብረውን ከነበሩት ተጫዋቾች በአብዛኛዎቹ ለቀዋል። አሁን ያሉት አዳዲስ ተጫዋቾች ከባለፈው ዓመቶቹ ብስለትና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው። ነገር ግን የሊጉ ቻምፒዮን መሆናችን ትኩረት እድንስብ አድርጎናል። ሁሉም ቡድን እኛኝ ለመግጠም በተለየ ትኩረትና ዝግጅት ነው የሚያደርጉት። ይህ ደግሞ ጨዋታዎችን ያከብድብናል። እንደዛም ሆኖ እንደባለፈው ዓመት ባይሆንም በግብ ክፍያ ተበልጠን 7 ጀረጃ ላይ ነው ያለነው። ደረጃችንን ለማሳደግ እና ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከተጫዋቾች ከቡድኑ አመራሮች ጋር ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡

አምናም ሆነ ዘንድሮ በግል ጉዳይ ወሳኝ ጨዋታዎች አልፈውሀል። የግል ጉዳዩ ምንድነው? ይህ በእግርኳስ ህይወትህ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብሀል?

ባሳለፍነው ዓመት ዘንድሮም የተወሰኑ ጨዋታዎች አምልጠውኛል። የግል ጉዳዬ ስለሆኑ መናገር አልፈልግም፤ ምክንንያቱም ሰዎች የግል ጉዳዮቼን እያነሱ ጫና እዲያደርጉብኝ እና ተፅዕኖ ውስጥ እንዲከቱኝ አልፈልግም። ወደ ጅማ አባጅፋር ከመምጣቴ በፊት ያለብኝን ጉዳይ አስረድቼ ፍቃድ እንደሚሰጡኝ ከተስማማን በኋላ ነው የፈረምኩት እንጂ በድንገት የተከሰተ ነገር አይደለም። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። በሚቀጥለው ዓመት ጉዳዬ መቋጫ ያገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በጅማ አባ ጅፋርም ቆየሁ፤ ወደ ሌላ ክለብም ሄድኩ ሙሉ ትኩረቴ ጨዋታ ላይ ነው እንዲሆን የምፈልገው። ምናልባት ልጄ ካልታመመችብኝ ወይም ሌላ ድንገተኛ ነገር ካልገጠመኝ በስተቀር መጓዝን አልፈልግም።

ሊጋችን በውጪ ጎል ጠባቂዎች እየተጨናነቀ ነው። የዚህ ምክንያቱ ምን ይመስልሀል? የአመለካከት ችግር ነው ወይስ በጉልህ የሚታይ የችሎታ ልዩነት አለ?

በእግሊዝ በስፔን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ሊጎች ውስጥ ብዙ የውጭ ሀገር ግብ ጠባቂዎች አሉ። ይህ መሆኑ የሀገሬው ግብ ጠባቂዎች ከውጪዎቹ ብዙ የሚማሩት ነገር አለ። ዋናው ነገር ለመማር ፈቃደኛ መሆን ነው። እኔ በግሌ ፕሮፍይሌ ትልቅ ነው ብዬ ወደ የኢትዮጵያ ሄጄ አልጫወትም አላልኩም። እዚህ ከመጣው በኋላ እዚህ ካሉ አሰልጣኞቼ ብዙ የተማርኳቸው ነገሮች አሉ። ዋናው ነገር አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ ራስን ዝግጁ ማድረግ ነው። ተሽሎ ለመገኘት ጠንክሮ መስራት ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡