ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ቀጣዩ የቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት የድሬዳዋ እና የጅማ ጨዋታ ይሆናል።

በድሬዳዋ ስታድየም የሚደረገው የድሬዳዋ ከተማ እና የጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ ከሚጀምሩ አራት ጨዋታዎች መካከል አንዱ ነው። ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ የተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ ሳምንት ሜዳው ላይ በመከላከያ ሲመራ ቆይቶ ነበር ነጥብ የተጋራው። ከዛ ቀደምም በደቡብ ፖሊስ ሽንፈት የደረሰበት ክለቡ ከወዲሁ ነጥቦችን መሰብሰብ ካልቻለ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ላለመውረድ እንሳይጫወት ያሰጋዋል። ከዚህ አንፃር እንዲሁም በሜዳው ተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታውን እንደማድረጉ ሙሉ ነጥቦችን አሳክቶ ለመውጣት እንሰሚፋለም ይጠበቃል። ብርቱካናዎቹ በረከት ሳሙኤልን በቅጣት ፍቃዱ ደነቀ እና ራምኬል ሎክን ደግሞ በጉዳት ሲያጡ ወሳኙ የግራ መስመር ተከላካይ ሳሙኤል ዮሃንስ ከሳምንታት በኋላ ከጉዳት ይመለስላቸዋል።

የአምናዎቹ ቻምፒዮኖች ያለምንም ጉሳት እና ቅጣት ዜና ሙሉ ስብስባቸውን በመያዝ ነው ከምዕራብ ወደ ምስራቅ የተሻገሩት። ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በድል መወጣት የቻሉት ጅማዎች በድምሩ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ መረባቸው ከተደፈረም ሦስት ጨዋታዎች አልፈዋል። ቡድኑ ከድሬ በድል ከተመለሰ የነጥብ ድምሩ ሠላሳን መሻገር ሲችል እስከ አራተኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድልም ይኖረዋል። ከዚህ ውጪ ጅማን ዳግም የተቀላቀለው ኦኪኪ አፎላቢ ተቀይሮ በገባበት የጊዮርጊሱ ጨዋታ ለ12 ያህል ደቂቃዎች መጫወቱ ነገም የተሻሉ ደቂቃዎችን ሊያገኝ እንደሚችል የሚጠቁም ነው። ይህ መሆኑም ቡድኑ ፊት መስመር ላይ ከሚጠቀመው ተለምዷዊው የሦስትዬሽ ጥምረት ላይ ተጨማሪ አማራጭ ያሚያስገኝለት ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– አባ ጅፋር ሊጉን በተቀላቀለበት የአምናው የውድድር ዓመት በተገናኙባቸው ጨዋታዎች ሁለቱም በሜዳቸው የ1-0 ድልን ሲያዝመዘግቡ አስገራሚ በነበረው የዘንድሮው ጨዋታ ደግሞ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ስድስት ግቦች 3-3 ተለያይተዋል።

– ድሬዳዋ ከተማ ከተማ ሜዳው ላይ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አራት የሽንፈት ፣ ሦስት የድል እና ሁለት የአቻ ውጤት አስመዝግቧል።

– ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳ ውጪ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ሦስቴ በድል ሁለት ጊዜ ደግሞ በአቻ ውጤት ሲመለስ በአራት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ይመራዋል። በአማካይ በጨዋታ 3.6 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የሚሰጠው አርቢትሩ በስምንት ጨዋታዎች ሁለት የቀይ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምትም ሰጥቷል። ዳዊት በያዝነው ዓመት ጅማ አባ ጅፋርን ከደደቢት እና ወልዋሎ ጋር ያጫወተ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኛል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ዘነበ ከበደ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ረመዳን ናስር – ሚኪያስ ግርማ – ኤልያስ ማሞ – ምንያህል ተሾመ

ሐብታሙ ወልዴ – ኢታሙና ኬይሙኒ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ዳንኤል አጄዬ

ዐወት ገ/ሚካኤል – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ይሁን እንዳሻው – አክሊሉ ዋለልኝ – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡