ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የዛሬ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችንን በሽረ እና ጊዮርጊስ ጨዋታ እንጀምራለን።

ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ ባደረጓቸው ጨዋታዎች በሽንፈት የተመለሱት ስሑል ሽረ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ 09፡00 ላይ በሽረ ሜዳ ለ19ኛ ሳምንት ጨዋታ ይገናኛሉ። ከሁለት ጨዋታች አራት ነጥቦችን አሳክተው ሁለተኛውን ዙር የጀመሩት ሽረዎች ወደ አዳማ ባደረጉት ጉዞ ግን ሽንፈት ደርሶባቸዋል። የትናንቱን የደቡብ ፖሊስ ሽንፈት ተከትሎ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረዎች ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻሉ ቢያንስ አንድ ደረጃ የማሻሻል ተስፋ ይኖራቸዋል። በቡድናቸው ውስጥ ምንም የጉዳት እና ቅጣት ዜና የሌለባቸው ስሑል ሽረዎች በውጪ ሀገር ተጫዋቾች በተዋቀረው የፊት መስመራቸው የቅዱስ ጊዮርጊስን የመስመር ተመላላሾች የማጥቃት ተሳትፎ ተከትሎ ሊኖሩ የሚችሉ ክፍተቶችን መጠቀም ላይ ያተኮረ የማጥቃት አጨዋወትን ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ድል የቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቐለ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ከአስር ዝቅ ማድረግ አልቻለም። በተለይም ሳምንት በጅማ ያጋጠመው ሽንፈት ልዩነቱን ወደ ሰባት እንዳይቀንስ እንቅፋት ሆኖበታል። ከውጤቱ ባለፈ ቡድኑ ግብ ከማስቆጠር መራቁም ትልቁ ፈተናው ሆኗል። አዳማ ላይ በጌታነህ ከበደ አማካይነት ያስቆጠራት ግብም በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች የተገኘች ብቸኛ ግብ ናት። በርግጥ ጊዮርጊስ ሳላዲን እና ጌታነህን ማጣቱ ያጎደለው ሲሆን የሪቻርድ አርተር በቶሎ መላመድ እና በሜዳ ላይ የሚያሳየው የጎንዮች እና የኋላ እንቅስቃሴ በተጋጣሚ ተከላካዮች መካከል ክፍተትን የሚፈጥር ቢሆንም ይህን በመጠቀም የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ ማስቆጠር ከቡድኑ ይጠበቃል። የነገው ተጋጣሚው ደግሞ በሊጉ በርካታ ግቦች ከሚቆጠርባቸው ክለቦች መካከል አንዱ መሆኑ ለቡድኑ የተሻለ ተስፋን የሚሰጥ ነው። መሀሪ መና ፣ ሳላዲን ሰዒድ ፣ ለዓለም ብርሀኑ እና ጌታነህ ከበደ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ የሆኑ የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ናቸው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የአዲስ አበባው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ4-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

– ስሑል ሽረዎች በሜዳቸው በሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ አንዴ የተሸነፉ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት ባህር ዳርን ባስተናገዱበት ጨዋታ የመጀመሪያ የሜዳ ላይ ድላቸውን ማግኘት ችለዋል።

– እስካሁን ከመዲናዋ ውጪ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስቴ ድል የቀናው ሲሆን ሁለት ጊዜ በአቻ አራት ጊዜ ደግሞ በሽንፈት ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታው ለፌድራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ የዓመቱ ሦስተኛው ጨዋታ ይሆናል። አርቢትሩ እስካሀን በዳኘባቸው ሁለት ጨዋታዎች ሰባት የማስጠንቀቂያ ሃርዶችን ሲመዝ አንድ የቀይ ካርድ እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – አሳሪ አልመሐዲ – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ረመዳን ዮሴፍ

ሀብታሙ ሸዋለም – ደሳለኝ ደበሽ

ሳሊፍ ፎፎና – ያስር ሙገርዋ – ቢስማርክ ኦፖንግ

ቢስማርክ አፒያ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

አብዱልከሪም መሀመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ሄኖክ አዱኛ

ሃምፍሬ ሚዬኖ

ሪቻርድ አርተር – አቤል ያለው


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡