ከፍተኛ ሊግ ሀ | መሪው ሰበታ ነጥብ ሲጥል ተከታዮቹ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዋች በተለያዩ ከተሞች ተደርገው ለገጣፎ፣ ኤሌክትሪክ፣ ደሴ እና አቃቂ ቃሊቲ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል። መሪው ሰበታ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ሰበታ ላይ ሰበታን ከአክሱም ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል። የነጥብ ልዩነቱን አስጠብቆ መጓዝ ያልቻለበትን ውጤት ያስመዘገበው ሰበታ አሁንም በግብ ክፍያ በመብለጥ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ይገኛል።

ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማ ከለገጣፎ ለገዳዲ ባደረጉት ጨዋታ ለገጣፎዎች ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን የ2-1 ድል አስመዝገበዋል። በባለፈው ሳምንት በሜዳቸው ነጥብ የተጋሩት ጣፎዎች በሀብታሙ ፍቃዱ እና ብሩክ መርጊያ ሁለት ግቦች ቡራዩን ማሸነፍ ችለዋል። የቡራዩ ከተማ ብቸኛ ግብ ክንድዓለም ፍቃዱ አስቆጥሯል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከፌዴራል ፖሊስ ያደረጉትን ጨዋታ ኤሌክትሪክ በአዲስ ነጋሽ እና መሐመድ ጀማል ጎሎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለፌዴራል ፖሊስ ደግሞ በሱፍቃድ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል። ኤሌክትሪክ ድሉን ተከትሎ ከመሪው ሰበታ ያለውን ልዩነት በማጥበብ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ በሚደረገው ፉክክር ላይ ነፍስ መዝራት ችሏል።

አቃቂ ቃሊቲ ወሎ ኮምቦልቻን ነው 1-0 ሲያሸንፍ በ22ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ጥላሁን ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል። ደሴ ላይ ደሴ ከተማ አውስኮድን በአሰፋ ይመር እና በድሩ ኑርሁሴን ጎሎች 2-1 ያሸነፈበት ጨዋታም ከእሁድ መርሐ ግብሮች መካከል ናቸው።

ቅዳሜ ዕለት በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ዱከም ላይ ገላን ከተማ ከ ወልዲያ ያገናኘው ጨዋታ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ለገላን ከተማ ሚካኤል ደምሴ ሁለት፣ እሸቱ ጌታሁን አንድ ሲያስቆጥሩ ለወልዲያ ተስፋዬ ነጋሽ እና ይረገም አስቆጥረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡