ከፍተኛ ሊግ ሐ | መሪዎቹ ቡድኖች ድል አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 13ኛ ሳምንት የምድብ ሐ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተደርገው መሪው ሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም ተከታዮቹ አርባምንጭ ከተማ እና ነቀምት ከተማ ድል አስመዝግበዋል። 

ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ከቤንች ማጂ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በምድቡ መሪ ሀድያ ሆሳዕና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ24ኛው ደቂቃ ላይ ኤሪክ ሙራንዳ እና በ41ኛው ደቂቃ ዳግም በቀለ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ሆሳዕናዎች የምድቡ መሪነታቸውን አስጠብቀው እንዲጓዙ አስችለዋል።

አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ግቦች ሦሥት ነጥብ ማግኘት ችሏል። 

(በፋሪስ ንጉሴ)

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአንድ ጨዋታ ከሜዳ ውጪ እንዲጫወት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ዛሬ አርባምንጭ ከተማ ከካፋ ቡና ጋር በሜዳው ማድረግ የነበረበትን ጨዋታ በወላይታ ሶዶ ስታድየም ለመጫወት ተገዷል። በርካታ የአርባምንጭ ከተማ ደጋፊዎች ክለባቸውን ለመደገፍ በተገኙበት ጨዋታ 2-0 አሸንፏል። በዛሬው ጨዋታ ላይ ሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞቻቸውን ሳይዙ ወደ ሜዳ ገብተዋል። አርባምንጭ ከተማ መሳይ ተፈሪ የተላለፈበትን የአራት ጨዋታ ቅጣት ተከትሎ ቡድኑን ያልመራ ሲሆን የከፋ አሰልጣኞችም ከክለቡ ጋር በመለያየታቸው በቡድን መሪው እየተመሩ ጨዋታው ተጀምሯል።

እልህ አስጨራሽና እና ሙቀት የተቀላቀለበት የመጀመርያው አስር ደቂቃ በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ብቻ የታጀበ ነበር። በተለይ የከፋ ቡና የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ መሀል ግን አርባምንጮች አልፎ አልፎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን ያደርጉ ነበር። 13ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ዋኮ ያሻገርውን ኳስ ስንታየሁ መንግስቱ በግንባሩ ገጭቶ በግቡ አናት የወጣበት፣ 20ኛው ደቂቃ ላይ እሱባለው ያሻማውን ኳስ ስንታየሁ በድጋሚ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት፣ እንዲሁም በ33ኛ እና በ43ኛው ደቂቃ አለልኝ እና አካሉ አበራ የሞከሯቸው ሙከራዎች በአርባምንጭ በኩል የሚጠቀሱ ሲሆን 40ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጭ ከተማ ተከላካዮች የፈጠሩትን ስህተት ተከትሎ አድማሱ ጌትነት በግብ ጠባቂው አናት ለማሻገር ሞክሮ የተመለሰበት በከፋ ቡናዎች የመጀመርያ አጋማሽ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

ከእረፍት መልስ እንደመጀመርያው አጋማሽ የግብ እድሎችን ፈጥረው ግብ ያስቆጥራሉ ተብለው የተጠበቁት አርባምንጭ ከተማዎች የከፋን የመሀል ክፍል ለመቆጣጠርና ትክክለኛ የሆነ ቅብብል ለማድረግ ሲቸገሩ የታዩ ሲሆን ካፋ ቡናዎች በአንፃሩ በአንድ ሁለት ቅብብል ማራኪ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልልም ለመድረስ የሚያደርጉት ሙከራ በአርባምንጭ ከተማ ተከላካዮች በቀላሉ ሲከሽፍ ታይቷል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይም አርባምንጭ ከተማዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በ47 በ51 እና በ82ኛ ደቂቃ ላይ በስንታየሁ መንግስቱ በአባነህ ገነቱ እና በመልካሙ ቦጋለ አድርገዋል።
አርባምንጭ ከተማዎች የጨዋታው ሰዓት ወደማለቁ ሲጠጋ ያላቸውን አቅም ሁሉ በመጠቀም ረጃጅም ኳሶችን በማቀበል የግብ እድል ለመፍጠር ሲሞክሩ ቆይተው በ90ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ፍቃዱ መኮንን ከበረከት የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሯት አርባምንጮችን ጮቤ አስረግጧል። ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ ተስፋ የቆረጡ የሚመስሉት ከፋ ቡናዎች አርባምንጭ ከተማዎች የሚፈጥሩትን ጫና ለመቋቋም ተቸግረው በሁለት ደቂቃ ልዩነት ሁለተኛ ግብ በስንታየሁ መንግስቱ ሊቆጠርባቸው ችሏል። ጨዋታው በዚህ ዉጤት ሲጠናቀቅ አርባምንጭ ከተማ ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት ባለበት እንዲቆይ ረድቶታል።

ሌሎች ጨዋታዎች (በአምሀ ተስፋዬ)

ነቀምት ላይ ነቀምት ከተማ ከ ቡታጅራ ባደረጉት ጨዋታ ነቀምት 3-2 አሸንፏል። ለነቀምት ከተማ በ13ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ብርሃኑ እንዲሁም ዳንኤል ዳዊት በ21ኛው እና በ25ኛው ደቂቃ ግቦችን አስቆጥረዋል። ለቡታጅራ ደግሞ በ40ኛው ደቂቃ ክንዴ አቡቹ እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ ፉአድ እንድሪስ ጎሎችን አስቆጥሯል።

ቦረና ላይ ነገሌ ቦረና ሻሸመኔ ከተማን 4-2 ረቷል። ለነገሌ ቦረና በ45ኛው ደቂቃ ምናሉ ተረፈ፣ በ57ኛው ደቂቃ ላይ እስጢፋኖስ የሺጌታ፣ በ62ኛው ደቂቃ ዮርዳኖስ ስሜ እና በ71ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ አላሮ ግቦችን ሲያስቆጠሩ ለሻሸመኔ ከተማ በ29ኛው ደቂቃ መሳይ ወንድሙ እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ ላይ ፌይሱ ከድር ግቦችን አስቆጥረዋል።

ሺንሺቾ ላይ ሺንሺቾን ከ ጅማ አባቡና ያገናኘው ጨዋታ 1-1 ተፈፅሟል። የባለሜዳዎቹ በደጋፊዎች ባሳዩት ስርአት አልበኝነት በተነሳ ግጭት ጅማ አባቡናን ለመደገፍ ወደ ሺንሺቾ ከተማ ያቀኑ ጥቂት ደጋፊዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። የእለቱ ኮሚሽነር የአባ ቡና ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲገቡና ከግብ ጀርባ እዲቀመጡ ካመቻቹ በኃላ ጨዋታው ከተቋረጠበት በመቀጠል በባለ ሜዳዎቹ የ1-0 መሪነት ለረጅም ደቂቃዎች ቢቆይም አባቡናዎች በ72ኛው ደቂቃ በካርሎስ ዳምጠው የአቻነት ግብ ጨዋታው 1-1 ከተጠናቀቀ በኃላ የሺሺንቾ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኞች እና የአባቡናን ተጫዋቾች ከሜዳ አናስወጣም በማለታቸው ለረጅም ሰዓት ሜዳ ውስጥ ለመቆየት ተገደዋል። በሜዳው ላይ የተገኙት ጥቂት የከተማው ፖሊሶችም ደጋፊውን ለመበተን መሳርያ ወደ ላይ ለመተኮስ ተገደዋል። ለጨዋታው የተመደቡት የፀጥታ አካላትም አነስተኛ መሆናቸው የተፈጠረውን ስርዓት አልበኝነት መቆጣጠር እንዳይቻል አድርጎታል፡፡

ቅዳሜ እለት በተደረገ የምድብ ብቸኛ ጨዋታ ቢሾፍቱ ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ በፍቃዱ በርባ ብቸኛ ጎል ስልጤ ወራቤን 1-0 አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡