የደደቢት ተጫዋቾች ልምምድ አቆሙ

የሰማያዊዎቹ ተጫዋቾች በደሞዝ ምክንያት ልምምድ መስራት አቁመዋል፡፡

ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ወዲህ መልካም የውጤት መሻሻል በማሳየት ላይ ያሉት የደደቢት ተጫዋቾች ያለፉት ወራት ደሞዛቸው ያልተከፈላቸው በመሆኑ ምክንያት ልምምድ ማቆማቸውን ለማወቅ ተችሏል።

እንደጠበቁት ከአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ማግኘት ያልቻሉት ሰማያዊዎቹ ከጥቂት ወራት በፊትም በተመሳሳይ ምክንያት ልምምድ አቋርጠው የነበረ ሲሆን በዚሁ የፋይናንስ ችግር ሳቢያም በተከታታይ ሁለት ዓመታት  ከኢትዮጵያ ዋንጫ  ራሳቸው ማግለላቸውም ይታወሳል።

በጉዳዩ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጽያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የቡድን መሪው አቶ ኤፍሬም አበራ እንዳሉት ከሆነም ክለቡ የተጫዋቾቹን ደሞዝ ለመክፈል ጥረት እያደረገ ሲሆን በአጭር ቀናት ውስጥም ከፍለው እንደሚያጠናቅቁ  ገልፀዋል።

በሁለተኛው ዙር አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሃዬን ቀጥረው በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ደደቢቶች በቀጣይ ሳምንት በትግራይ ስታድየም  ጅማ አባ ጅፋርን የሚገጥሙ ይሆናል።