ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል በብቸኝነት ዛሬ በሽረ እንዳስላሴ የሚካሄደውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በወጥ ብቃት ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ያልቻሉት አዲስ አዳጊዎቹ ስሑል ሽረዎች ከሽንፈት መልስ በሜዳቸው ያላቸውን ጥሩ ክብረ ወሰን የማስቀጠል ግዴታ ውስጥ ገብትው ነው ወደዚህ ጨዋታ የሚቀርቡት።

ባለፉት ጨዋታዎች ድንቅ  የአጥቂ ጥምረት እና ጥሩ የግብ ማስቆጠር ክብረ ወሰን ያላቸው ስሑል ሽረዎች ዛሬ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ደካማው የተከላካይ ክፍላቸው ላይ የቅርፅም የተጫዋችም ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሁለቱንም ፈጣን የማጥቃት ባህሪ ያላቸው የመስመር ተከላካዮች ያሳተፈ እና ሦስቱ አጥቂዎች ላይ ያነጣጠረ አጨዋወት የተከተሉት ሽረዎች ዛሬም በተመሳሳይ አቀራረብ ይገባሉ ሲጠበቅ ከመጠነኛ ጉዳት መልስ ጨዋታዎችን መጀመር ያልቻለው ደሳለኝ ደባሽ ወደ ቋሚ አሰላለፍ የመመለስ ዕድሉም የሰፋ ነው። ከማጥቃቱ ባሻገር ጥሩ መናበብ የማይታይበት እና በአማካዮቹ በቂ ሽፋን የማይሰጠው የመከላካል አደረጃጀታቸው እንደ ሀዋሳው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት አቀራረብ ክፍተት ሳይሰጥ መጨረስ ይጠበቅበታል።  ቡድኑ ሁለቱንም ግብ ጠባቂዎቹን ሀፍቶም ቢሰጠኝ እና ሰንደይ ሮቲሚን ጨምሮ አሳሪ አልመሃዲንንም በጉዳት አያሰልፍም።

ከአምስት ተከታታይ ሽንፈት በኃላ አንሰራርተው በተከታታይ ጨዋታዎች  ወልዋሎን እና ደደቢትን በማሸነፍ በወላይታ ድቻ እና በአዳማ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት በስተቀር በሁለተኛው ዙር ከባለፈው  ዙር አንፃር በጥሩ የውጤት ጉዞ ላይ የሚገኙት ቡናዎች ከሜዳቸው ውጪ ያላቸው መጥፎ ውጤት ለመቀየር እና ከተከታዮቻቸው ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት በማለም ወደዚህ ጨዋታ ይቀርባሉ።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በዚህ ዓመት በአማካይ ክፍል በተለያዩ ሚናዎች  በቋሚነት ያገለገላቸው አልሃሰን ካሉሻ በጉዳት ስለማያገኙ እንዳለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሁሉ አዲስ ጥምረት ያሳያሉ ተብሎ ሲጠበቅ ባለፈው ሳምንት ሸገር ደርቢ ላይ ከተከተሉት በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መጠነኛ ለውጥ ያደርጋሉም ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ አማካዩ አልሃሰን ካሉሻ በጉዳት ማጣቱ እና አህመድ ረሺድ ከጉዳት መልስ ማግኘቱን ተከትሎ መጠነኛ የአጨዋወት እና የተጫዋቾች ለውጥ ማድረጉ አይቀሪ ነው። ከዚህ ባለፈም ባለፈው ጨዋታ መሀል ሜዳ ላይ ብልጫ ከመውሰድ ባሻገር በተደጋጋሚ የተጋጣሚ ግብ ክልል ሲደርሱ ያልታዩት ቡናዎች ዛሬም ከተጋጣምያቸው አንፃር የመሃል ሜዳ ብልጫ ለመውሰድ እንደማይቸገሩ ቢታሰብም ከሳጥኑ ርቆ የሚከላከለውን የስሑል ሽረ የተከላካይ ክፍል ዒላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች የመጠቀም አዝማምያ ሊያሳዩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። አልሀሰን ካሉሻ ፣ ሚኪያስ መኮንን ፣ ተመስገን ካስትሮ እና ሱለይማን ሎክዋ በጉዳት አቡበከር ናስር እና ወንድወሰን አሸናፊ ደግሞ በቅጣት በዛሬው ጨዋታ ቡድናቸውን እንደማያገለግሉ ታውቋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ያገናኛው የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ግቧን አቡበከር ናስር በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ነበር።

– ስሑል ሽረዎች በሜዳቸው በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ አንዴ የተሸነፉ ሲሆን ባህር ዳርን እና ሀዋሳ ከተማን ባስተናገዱባቸው ጨዋታዎች ድል ቀንቷቸዋል።

– ለአስረኛ ጊዜ ከአዲስ አበባ ስታድየም ውጪ የሚጫወተው  ኢትዮጵያ ቡና ሁለት የድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ አምስት ጊዜ ተሸንፏል።

ዳኛ

– እስካሁን በመሀል ዳኝነት በመራቸው አራት ጨዋታዎች 17 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመዘዘው ባህሩ ተካ ይህን ጨዋታ ይመራዋል። አርቢትሩ ከዚህ ቀደም ስሑል ሽረን ከመቐለ ኢትዮጵያ ቡናን ደግሞ ከደደቢት ማጫወቱ ይታውሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ 

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ዳዊት አሰፋ

ዓብዱሰላም አማን – ክብሮም ብርሃነ– ዲሜጥሮስ ወ\ስላሴ – ረመዳን ናስር

ብሩክ ተሾመ – ደሳለኝ ደባሽ 

ቢስማርክ አፖንግ – ያስር ሙገርዋ   ቢስማርክ አፕያ

ሳሊፉ ፎፋና

ኢትዮጵያ ቡና (4-2-3-1)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ቶማስ ስምረቱ – ተካልኝ ደጀኔ

አማኑኤል ዮሀንስ – ኄኖክ ካሳሁን

እያሱ ታምሩ – ሳምሶን ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ሁሴን ሻቫኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡