ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አምስት – ክፍል ሁለት)

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics በሶከር ኢትዮጵያ በአማርኛ መቅረብ ከጀመረ 16 ሳምንታትን አስቆጥሯል፡፡ በዛሬው መሠናዶም የምዕራፍ አምስት ሁለተኛ ክፍልን አቅርበንላችኋል።

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

በ1899 በፒተርስበርግ የተወለደው አርካዲዬቭ ከሩሲያ አብዮት በኋላ ወደ ሞስኮ አቀና፡፡ በከተማዋ የተሳካ የተጫዋችነት ህይወት እያሳለፈ በተጓዳኝ በሚኻይል ፍሬንዝ የጦር መኮንኖች ማሰልጠኛ የሻቦላ ግጥሚያ ስፖርትን ተማረ፡፡ አርካዲዬቭ በእግርኳስ የመልሶ-ማጥቃት አጨዋወትን (Counter-Attacking Football) ለመተግበር የተነሳሳው ወደ ባላጋራ ጥቃት ካደረሱ በኋላ በፍጥነት መልሶ የመመከት ዘዴ  (Parry-Reposte) ላይ ከፍተኛ አጽንዖት ከሚሰጠው የሻቦላ ፍልሚያ (Fencing) እንደሆነ ከጊዜያት በኋላ ገልጿል፡፡ ከቀድሞ የሃገሪቱ ርዕሰ መዲና ትንንሽ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነውን <ሜታሉር ሞስኮ> እየመራ በ1936ቱ የከፍተኛ ሊግ መክፈቻ ውድድር ሶስተኛ ደረጃ ካደረሳቸው በኋላ ዳይናሞ ሞስኮን ተረከበና የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫ አሸነፈ፡፡ በአዲሱ ክለቡ ተጫዋቾቹን ከትልልቅ ጨዋታዎች በፊት የስዕል አውደ ርዕዮችን እንዲጎበኙ ከሚያደርግበት ልምዱ ባለፈ የተለዩ ሐሳቦችን ለማመንጨት የማያርፈው ምጡቅ አዕምሮውና ሰፊ ምናባዊ እይታው ከፍተኛ ከበሬታ አተረፉለት፡፡ በክለቡ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው የሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ቢያነሳም ባስካውያኑ የሶቭየት እግርኳስ አጨዋወት ላይ በፈጠሩት ተጽእኖ ምክንያት እርሱም ታክቲካዊ አቀራረቡን እንደገና መከለስ ተጠበቀበት፡፡  

” ከባስኮቹ ጉብኝት በኋላ መላው የሶቪየት ትልልቅ ክለቦች በአዲሱ የአጨዋወት ስርዓት መቅረብ ጀመሩ፡፡ ቶርፒዶዎችም በዚሁ መንገድ ተጉዘው ሌሎች ተቀናቃኞቻቸውን ልቀው ተገኙ፤ ታክቲካዊ አቅማቸውን አጎልብተውም በ1938ቱ የመጀመሪያ ግማሽ የውድድር ዘመን የተለየ ብቃት አሳዩ፡፡ በ1939 ደግሞ በሁሉም የሃገሪቱ ቡድኖች የነበርን የእግርኳስ ባለሙያዎች እንግዳውን የጨዋታ ዘይቤ መከተል መረጥን፤ በታክቲካዊ አብዮት ማዕበል በተቃኘ መንፈስ መንሳፈፋችንንም ተያያዝነው፡፡” በማለት አርካዲዬቭ ጽፏል፡፡ ይሁን እንጂ መጤው የአጨዋወት ስርዓት ከቀደመው ጊዜ አንጻር ዳይናሞዎች ላይ የፈጠረው አሉታዊ ምዕራፍ የከፋ ሆነ፡፡ 1938ን በሊጉ አምስተኛ ሆነው ጨረሱ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ በተካሄደው የ1939ኙ የውድድር ዘመን ደግሞ ዘጠነኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ፡፡ የቡድኑንን የቁልቁለት ጉዞ ለመታደግ በተሰማራበት የስራ መስክ ሁሉ ስኬታማ ለመሆን የማይፈነቅለው ድንጋይ ያልነበረው በጥባጩ የKGB መሪ እና የክለቡ የበላይ ጠባቂ ላቭሬንቲ ቤርያ ቆራጥ ውሳኔ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ፡፡ 

በጊዜው ውጤታማነት የከዳቸው ሌሎች አሰልጣኞች ምናልባት ወደ ኋላ ተመልሰው መሰረታዊዎቹ የእግርኳስ መርሆዎች ላይ ያጠነጠነ ጥገናዊ ለውጥ ከውነው ይሆናል፥ አርካዲዬቭ ግን እንደዚያ አላደረገም፤ ይልቁንም ሁኔታውን በተለየ መንገድ ቃኘው፤ የውድቀቱን ሰበቦች ያሰላስል ያዘ፤ መፍትሄዎቹ ላይም ጥልቅ ምርምር አካሄደባቸው፡፡ ከተጫዋቾቹ የተናጠል የሜዳ ብቃት በላቀ እንደ ቡድን ለጨዋታ የሚቀርቡበት መንገድ ቁልፉ ጉዳይ እንደሆነም አመነ፡፡ ስለዚህም በየካቲት ወር 1940 ጥቁር ባህር አካባቢ በሚገኘው የ<ጃግሪ> መዝናኛ ስፍራ ከተለመደው የአሰልጣኞች የየዕለት ተግባር ወጣ ያለ ነገር ይዞ ብቅ አለ፡፡ የቅድመ- ውድድር ልምምድ ማድረጊያ ስፍራ ጎን የሚገኙ ክፍሎች ውስጥ ከዚያ ቀደም አድርጎት በማያውቀው መልኩ የእግርኳስ ታክቲካዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚዳስስ የሁለት ሰዓት ትምህርታዊ ገለጻ (Lecture) ማድረግ ጀመረ፡፡ እርሱ እንደሚለው የዚህ ውሳኔው ዋነኛ አላማ W-M ፎርሜሽንን በተለያዩ መዋቅራዊ አውታሮች (Variants) ማሻሻል ነበር፡፡ “ብዙዎቹ የኛና የሌሎች ሃገራት ክለቦች ሶስተኛውን ተከላካይ (Third-Back) በማካተት በጨዋታ የማጥቃት ሒደት ውስጥ ከቦታ ቦታ የሚሯሯጡ ተጫዋቾችን ማሰለፍ ቀጠሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ጥናት ላይ የተመሰረተ ግኝት ረዘም ላለ ጊዜ ባይዘልቅም ቅሉ ለአጠቃላዩ ስርነቀል የሩሲያ እግርኳስ ታክቲክ-ተሃድሶ (Football Perestroika) መጀመሩን የሚያበስር ማንቂያ ደውል መሆን ችሏል፡፡ እውነቱን ለመናገር በጨዋታ ወቅት አንዳንድ ተጫዋቾች ፍጹም ታክቲካዊ ተልዕኮ በሌላቸው ምክንያቶች የማያቋርጥ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ይደርሳቸው ጀመር፡፡ አልፎ አልፎም አንድ ተጫዋች አመዛኝ ከሆነ የሜዳ ላይ ቦታው ውጪ እንዲገኝ የሚያስችል አካላዊ ጥንካሬ፣ ብርታት አልያም ተፈጥሮአዊ ፍጥነት ከያዘ ሆን ተብሎ በሰፊው የሜዳ ክልል ውል-አልባ እንቅስቃሴ በመከወን እንዲባዝን ይደረጋል፡፡ ስለዚህም ከአምስቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ውስጥ በሜዳ ላይ በሚወጡት ሚና መሰረት በተሰጣቸው ቦታ ላይ የሚገኙና በማጥቃት ሲሶው (Attacking Third) ክፍት መስመሮች (Channels) ወዲያ ወዲህ የሚሉ ተጫዋቾች አራት ብቻ ሆኑ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ በድንገት የቡድን አጋሮቹን መደበኛ እንቅስቃሴ የሚረብሽ፣ በሜዳው ቁመት ተቃራኒ ማዕዘናትን በሚያገናኝ የአግድሞሽ መስመር (Diagonal Sprint) የሚያፈተልክ ፣ በሜዳው ስፋት ደግሞ ወደ ቀኝ አልያም ወደ ግራ (Lateral Running) የሚሮጥ አንድ ተጫዋች እናያለን፡፡ ይህን አካሄድ የሚተገብር አጥቂ ለመከታተልና ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ በሚከላከለው ቡድን የሚገኙ ተጫዋቾች እጅግ አዳጋች ስለሚሆንባቸው ሌሎቹ አጥቂዎች ቀጥተኛ ቅብብሎችን ሊፈጽሙ የሚችሉለት የቡድን አጋር ስለሚኖራቸው የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡” ሲል አርካዲዬቭ ታክቲካዊ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ 

የ1941 የዳይናሞ ሞስኮዎች የውድድር ዘመን በመጥፎ ሁኔታ ተጀመረ፤ <ኪሪያላ ሶቬቶቭ ሞስኮ> እና <ትራክተር ስታሊንግራድ> ከተባሉ ክለቦች ጋር አቻ ወጥተው በ<ዳይናሞ ቲቢሊሲ> ደግሞ ተሸነፉ፡፡ እንዲያም ሆኖ አርካዲዬቭ አልተሸበረም፤ ከቲቢሊሲው ሽንፈት በኋላ ተጫዋቾቹን ሰብስቦ አንድ ላይ እንዲቀመጡ አደረገ፤ ለእያንዳንዳቸውም ግላዊና የቡድን ጓደኞቻቸውን ብቃት የሚገመግም በጽሁፍ የታገዘ ዘገባ እንዲያቀርቡለት አዘዛቸው፡፡ ከዚያማ በቡድኑ ሰማይ ላይ ያንዣበበው ደመና ተገፈፈ፤ ሁኔታዎች ይበልጡን ግልጽ ሆኑ፤ በአጋጣሚው ተጫዋቾቹ  የአሰልጣኛቸውን ሩቅ አሳቢነትና ውስጣዊ ፍላጎት ተረዱ፡፡ ሰኔ 4 ቀን ዳይናሞ ሞስኮዎች የቅርብ ርቀት ቅብብሎችን ማዕከል ያደረገ ፈጣን ጨዋታ (Rapid-Close Passing Style) በመከወን ዳይናሞ ኪዬቮችን 8-5 ረቱ፡፡ በዩክሬን በተደረገው የመልሱ ግጥሚያ ደግሞ የተሻለ ተጠናክረው ቀረቡ፤ ተጋጣሚያቸው ላይ ከፍተኛ ብልጫ ወስደው በሰፋ የግብ ልዩነት 7-0 አሸነፉ፡፡ ከዚያም በነሃሴ ወር የሊጉ አሸናፊ ስፓርታ ላይ የ5-1 ድል ተጎናጸፉ፡፡ ከውድድር ዓመቱ የመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ሃያ ስድስት ግብ አስቆጥረውና ሶስት ግብ ብቻ ገብቶባቸው ሁሉንም ጨዋታዎች በድል ተወጡ፡፡ “ተጫዋቾቻችን ከግትሩ የW-M ፎርሜሽን ውጪ በሌላ እንቅስቃሴያዊ የተጫዋቾች አቋቋም (Fluid Positioning ) ለመጫወት ፈለጉ፤ የእንግሊዛውያን የፈጠራ ውጤት በሆነው የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር (Formation) የሩሲያውያንን አሻራ ለማሳረፍ ሻቱ፤ ቸል የተባለውን ቀኖናዊ ስርዓትም በፎርሜሽኑ ውስጥ ለማስረጽ ሞከሩ፡፡ በውጤቱ ባላንጣዎቻችን ግራ ተጋቡ፤ ድንገታዊው የማጥቃት እንቅስቃሴያችን ዱብ እዳ ሆነባቸው፡፡ ተቀናቃኞቻችን የማክሸፊያ እቅድ ሳያዘጋጁ ግራ አጋቢው ስልታችን ድቅን አለባቸው፡፡ የግራ መስመር አማካያችን ሰርጂ ኤይን አንድ የመሐል አጥቂ ከሚያዘወትረው ቦታ እየተነሳ በርካታ ግቦችን አመረተልን፡፡ የቀኝ መስመር አማካያችን ሚክሃይል ሴሚሻስትኒ ከግራ መስመር፥ የመሃል አጥቂያችን ሰርጂ ሶሎቪዮቭ ደግሞ በሁለቱም የጎንዮሽ መስመሮች እየተጫወቱ ተመሳሳዩን አደረጉ፡፡” በማለት አርካዲዬቭ የለውጡን ትሩፋቶች ይተነትናል፡፡ 

ጋዜጦች በጨዋታ ወቅት በዳይናሞ ኪዬቮች ሆን ተብሎ ለታቀደው የተደራጀ ትርምስ ታክቲካዊ ብልሃት (Organized Disorder) አድናቆት ቸሩ፤ ተጋጣሚ ቡድኖች ደግሞ የስልቱን ማርከሻ መፍትሄ ፍለጋ ይታትሩ ጀመር፡፡ በሁሉም ዘንድ እየተለመደ የመጣው መፍትሄ ጥብቅ የሆነው ተጫዋችን-በ-ተጫዋች የማስያዝ ዘዴ (Man- Marking System) ነበር፡፡ አርካዲዬቭ ለዚህ አጸፋ አላጣም፤ ተጫዋቾቹ በፊት ከሚከውኑት የበለጠ ፈጣን በሆነ ድግግሞሽ ቦታቸውን እንዲለዋውጡ አደረገ፡፡ “የተከላካይ መስመራችን ይጠቀምበት የነበረውን በቀጠና የመከላከል ዘዴ (Zonal Marking System) ወደ ተናጠል ሰውን-በ-ሰው የመቆጣጠር ስርዓት (Specific Man-Marking) አሸጋገርን፡፡ ሁሉም ተከላካዮቻችን የተጋጣሚዎቻችንን አጥቂዎች እየተከታተሉ የሚሄዱበት የሜዳ ክፍል ድረስ አብረዋቸው ስለሚዘዋወሩ የአጨዋወት ዘይቤአቸንን ተለዋዋጭ ወደ ሆነ የሚዋልል ስልት ቀየርን፤ ከዚህ አንጻር የፊት መስመር ተሰላፊዎችና አማካዮች በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሆኑ ማስገደድ በታክቲካዊ ምልከታ ስንገመግመው ተገቢና ምክንያታዊ ሆኖ ታየን፡፡” ይላል ለተቀናቃኞቹ አሰልጣኞች ያበጀውን መላ ሲያብራራ፡፡

እዚህ ጋር አርካዲዬቭ የ<ቀጠና ጨዋታ/Zonal Game> ሲል ምን ለማለት እንደሆነ በአግባቡ ማብራራት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ የእርሱ ቀጠናዊ አቀራረብ (Zonal Game) ለመጀመሪያ ጊዜ በ1950ዎቹ ዜዜ ሞሬይራ በብራዚል ካስተዋወቀው በኋላ ቪክቶር ማስሎቭ በዳይናሞ ኪዬቭ ተግብሮት አመርቂ ስኬት ያስመዘገበበት በቀጠና መከላከልን (Zonal Marking) የሚያካትተው ጨዋታ ማለቱ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አርካዲዬቭ የሚተነትነው ‘ሲስተም’ ሁለቱ የመስመር ተመላላሽ ተከላካዮች(Full-Backs) በሜዳው ቁመት ግራና ቀኙን ጠርዝ (Line) ይዘው እንዳ’ስፈላጊነቱ ተለዋዋጭ የሆነውን 2-3-5 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር በመጠቀም ከሚከወነው ቀላሉ በቀጠና የመጫወት ዘዴ (Zonal Game) ወደ ግትሩ (Rigid) የW-M ፎርሜሽን አተገባበር የተደረገውን ሽግግር (Transition) ነው፡፡ በዚህ የአጨዋወት ስርዓት (System) እያንዳንዱ ተጫዋች የትኛው ባላጋራ ላይ ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንዳለበት ጠንቅቆ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡ (በተለምዷዊው መንገድ ስንዘረዝረውም፦ የቀኙ መስመር ተከላካይ (Right-Back)፥ የተጋጣሚን የግራ መስመር አማካይ (Left Wing)፣ በመሃለኛው የሜዳ ክፍል የግራውን መስመር ተጠግቶ የሚጫወተው የግራ መስመር አማካይ (Left-Half)፥ በተቃራኒ ቡድን ውስጥ ከመሃል አጥቂው በስተቀኝ የሚቆመውን የፊት መስመር ተሰላፊ (Inside-Right) ፣ የመሃል ተከላካዩ (Centre-Back)፥ የባላንጣውን የመሃል አጥቂ (Center-Forward)…ወዘተረፈ……ላይ ዓይናቸውን ተክለው እንቅስቃሴያቸውን የመግታት ሒደት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡) ከላይ የተጠቀሰው የተጫዋቾች የሜዳ ላይ ኃላፊነት ዝርዝር ማሳያ በእንግሊዝ ከW-M ፎርሜሽን ጋር አብሮ የተፈጠረ እና ከመነሻው ጀምሮ ሒደታዊ እድገት እያሳየ የመጣ ነው፡፡ በአንጻሩ በሩሲያ ፎርሜሽኑ ሙሉ በሙሉ ተበጃጅቶ ካበቃ በኋላ ጥቅም ላይ መዋል ስለጀመረ በጨዋታ የመከላከል ዑደት (Defending Cycle) ላይ የሚታዩ እንቅስቃሴያዊ የቅርጽ ክፍፍሎችን ስዕላዊ በሆነ መልኩ ለማሳየት ግርታን መፍጠሩ አይቀሬ ነበር፡፡

ከጊዜያት በኋላ በW-M ፎርሜሽን ከሁለቱ የመሃል ተከላካይ-አማካዮች (Halves) አንደኛው ይበልጡን በመከላከል ሚናው ላይ ማተኮር ጀመረ፤ በስሶት ተከላካዮች ለተዋቀረው የመከላከል መስመርም (Defensive Line) ተጨማሪ ሽፋን መስጠት ተጠበቀበት፡፡ ይህም አንድ ከመሃል አጥቂ ጎን የሚጫወት የፊት መስመር ተሰላፊ (Inside-Forward) ለቀረው ብቸኛ የመሃል-ተከላካይ አማካይ (Centre-Half) የጎንዮሽ ድጋፍ ለማድረግ ወደ ኋላ እንዲሳብ አስገደደ፡፡ መዋቅራዊ ማሻሻያው (Positional Rearrangement) በተፈጠረበት ሃገር ሒደቱ አዝጋሚ ቢሆንም ለተቀረው ዓለም በፍጥነት ማድረስ ይቻል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ 3-2-2-3 ፎርሜሽን (W-M) ብዙም ሳይቆይ 4-2-4 ወደ መሆን እየተንደረደረ በመሄዱ ሌሎች ሃገራት ከተለመዱት የW-M ትግበራዎች ውጪ የተሞከሩትን አማራጭ ቅርጾች (Variants) ሳያዩ ቀሩ፡፡ የሶቭየትን እግርኳስ ታሪክ በመጻፍ ትልቅ ከበሬታ ያተረፈው አክዜል ቫርታኒያን ከዚሁ ፈጣን የፎርሜሽን ለውጥ ጋር በተያያዘ በአራት ተጫዋቾች ጥምረት የሚሰራውን ዝርግ የመከላከል መስመር (Flat Back-Four) በመጠቀም ምናልባት የመጀመሪያው አሰልጣኝ ቦሪስ አርካዲዬቭ ሳይሆን እንደማይቀር ያምናል፡፡ 

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)