አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በአዲስ አበባ የሚገኝ አካዳሚን ጎበኙ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቀጨኔ አካባቢ የሚገኘውና ከተመሰረተ ገና የሁለት ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው ጌታቸው ቀጨኔ አካዳሚን ዛሬ ቀትር ላይ በስፍራው በመገኘት ነበር ጉብኝት አድርገዋል።

ቀጨኔ አካባቢ ያሉትን ትውልድ በእግርኳሱ ክህሎታቸው የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ በማሰብ አቶ ጌታቸው ኪሩቤል በተሰኙ ግለሰብ አማካኝነት ነው አካዳሚው የተቋቋመው አካዳሚው በወንድ እና በሴቶች ከ100 በላይ ታዳጊዎች አቅፎ የያዘ ሲሆን በተለይ በወንዶቹ ከ13 ፣ ከ15 እና ከ17 ዓመት ታዳጊዎችን አቅፎ ይዟል።

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በጉብኝት ወቅት ከአካዳሚው የአስተዳደር ክፍል ኃላፊዎች ሰፊ ማብራሪያ የተደረገላቸው ሲሆን አሰልጣኙ በበኩላቸው ለታዳጊዎቹ ጠቃሚ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመጨረሻም ለአሰልጣኝ አብርሃም አካዳሚው ስጦታ ካበረከተላቸው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል “እዚህ አካባቢ ላይ እንደዚህ ዓይነት ሜዳ እና በደንብ የተደራጀ አካዳሚ ይኖራል ብዬ በግሌ አልጠበኩም፤ ከግምቴ በላይ ነው። በአካዳሚው ውስጥ 120 የሚሆኑ ህፃናቶችን አቅፎ ይዟል። ከሁሉም በላይ ደስ የሚለው ነገር በየዕድሜው እርከን ከ13 ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች አካዳሚው ታዳጊዎችን አቅፎ መያዙ ተከታታይነት ያለው ስራ ለመስራት ተቋሙ ማቀዱን የሚያሳይ መሆኑ እጅግ በጣም ጥሩ ነው። 

” ሌላው ሜዳው አካባቢ የሚገኙ ክፍለ ከተማው አመራሮች ለአካዳሚው የሰጡት ትኩረት በጣም ጥሩ ነው፤ በሌሎች አካባቢዎችም መለመድ አለበት። ከዚህ በተረፈ ቀጨኔ መድኃኒዓለም አካባቢ እንደ በላያ (በኢትዮጵያ መድን እና ብሔራዊ ቡድን የተጫወተ) ዓይነት ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቅ ሲሆን አሁንም ተጫዋቾችን ማፍራት ይችላል። መስተካከል አለበት የምለው ያሉት አሰልጣኞች ያላቸው የማሰልጠን አቅም በተለያዩ ስልጠናዎች መዳበር፣ መደገፍ አለበት። አሰልጣኞቹ በሙያ ካልታገዙ እነዚህ 120 ህፃናቶች ወደ ፍሬ ለመቀየር ያስቸግራል። እኔም ሆንኩ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ ልንሰጥ የምንችልበትን መንገድ እናመቻቻለን። በተረፈ በግል ተነሳሽነት ይህን በጎ ሀሳብ ላቀናው እና ላስጀመረው ለአቶ ጌታቸው ኪሩቤል ያለኝን አድናቆት እየገለፅኩ ላበረከቱልኝም ስጦታ ከልብ አመሰግናለው። ” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡