የሴካፋ ካጋሜ የክለቦች ውድድር ከሰኔ መጨረሻ ጀምሮ ይካሄዳል

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ማኅበራት ካውንስል (ሴካፋ) የሚያዘጋጀው የ2019 ሴካፋ ካጋሜ የክለቦች ዋንጫ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 7 በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

ተወዳዳሪ ክለቦች ባልታወቁበት በዚህ ውድድር ከአዘጋጇ ሩዋንዳ ራዮን ስፖርትስ፣ ኤፒአር እና ሙኩራ ይሳተፋሉ ተብሏል። ሆኖም ውድድሩ የሚካሄድበት ወቅት ከአፍሪካ ዋንጫው ጋር የሚጋጭ በመሆኑ (የአፍሪካ ዋንጫ ካለቀ ከሁለት ቀናት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ይጀምራል) እንዲሁም በአህጉሪቱ ታላቅ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አራት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከመኖራቸው አንፃር ሴካፋ የመረጠው ወቅት ትችት አስከትሎበታል።

ሌላዋ የክፍለ አህጉሩ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ በ2015 አዳማ ከተማ ከተሳተፈ በኋላ በተከታታይ ሁለት ዓመታት ቡድኖቿ ሳይሳተፉ ቀርተዋል። ዓምና እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቦለት የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስም በሀገር ውስጥ ውድድር አለመጠናቀቅ ምክንያት ራሱን ከውድድሩ ማግለሉ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ዓመት የሚሳተፈው ክለብ ባይታወቅም የዓምናው የሊግ ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ጥያቄ ከቀረበለት እንደሚሳፍ ገልጿል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ዛኪር እና የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አጃኢብ አባመጫ ለሶከር ኢትዮጵያ እደተናገሩት ” እስካሁን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ ከአወዳዳሪው አካል የደረሰን መረጃ የለም። እንድንሳተፍ የምንጋበዝ ከሆነ ግን ውድድሩ ላይ እንሳተፋለን።” ብለዋል።

ከ2002 (እኤአ) ጀምሮ በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ስፖንሰር አድራጊነት እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ውድድር አምና ታንዛኒያ ላይ ተካሂዶ የሀገሬው ክለብ አዛም ሌላው የታንዛኒያ ክለብ ሲምባን አሸንፎ የዋንጫው ባለቤት መሆኑ ይታወሳል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2010 (እኤአ) ያሳካው የሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ትልቁ የመድረኩ ውጤት ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡