ፕሪሚየር ሊግ – የዛሬ ጨዋታዎች ተቀያሪዎች ልዩነት የፈጠሩበት ሆኗል 

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው አዳማ ከነማ መሪነቱን አስጠብቋል፡፡ መከላከያ እና ደደቢትም ድል ቀንቷቸዋል፡፡

9፡00 ላይ ዳሽን ቢራን ያስተናገደው አዳማ ከነማ 2-1 አሸንፎ መሪነቱን አስጠብቋል፡፡ አዳማ በመስመር አማካዩ ታከለ አለማየሁ የ32ኛ ደቂ ግብ መሪ መሆን ሲችል በ78ኛው ደቂቃ ዳሽኖች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ኤዶም ሆውሶሮቪ ወደ ግብነት ቀይሮ ዳሽንን አቻ አድርጓል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ተቀይሮ የገባው ወንድሜነህ ዘሪሁን በ83ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ቀያይ ለባሾቹን ለድል አብቅቷቸዋል፡፡

አዳማ ከነማ ድሉን ተከትሎ ከ6 ጨዋታ 16 ነጥብ በመሰብሰብ የሊጉን አናት ከቅዱስ ጊዮርጊስ በ3 ነጥቦች ርቆ መምራቱን ቀጥሏል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መከላከያ ሀዋሳ ከነማን 3-0 አሸንፎ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል፡፡ አማካዩ ሳሙኤል ታዬ በሀዋሳ ተከላካዮች የተፈጠረችውን ስህተት ተጠቅሞ መከላከያን በ15ኛው ደቂቃ ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከእረፍት መልስ ሀዋሳዎች ተጭነው በመጫወት አቻ ለመሆን ቢጥሩም በ68ኛው ደቂቃ በሳሙኤል ታዬ ተቀይሮ የገባው ባዬ ገዛኸኝ በ74 እና 81ኛው ደቂቃ ያስቆጠራቸው ግቦች ጦሩን ለውድድር ዘመኑ 2ኛ ድል አብቅቶታል፡፡

11፡30 ላይ በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 አሸንፎ መሪዎቹን ተጠግቷል፡፡ በ17ኛው ደቂቃ የብሽሽት ጉዳት ያጋጠመው ዳዊት ፍቃዱን ተክቶ የገባው ሔኖክ መኮንን በ37ኛው ደቂቃ በአስደናቂ የመልሶ ማጥቃት ደደቢትን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ የቡናው እያሱ ታምሩ ግብ ጠባቂውን አልፎ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ያመከነውን ኳስ ደደቢቶች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ግብ አድርገውታል፡፡ ከግቧ መቆጠር መቆጠር በፊት የደደቢት ተከላካዮች የእያሱን ሙከራ በእጃቸው ተጠቅመው አውጥተውታል በሚል ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በ41ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ሽመክት ጉግሳ የደደቢትን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነው የተጫወቱት ቡናዎች በካሜሩናዊው ያቤውን ዊልያም የ79ኛ ደቂቃ ግብ ወደ ጨዋታው ቢመለሱም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በደደቢት 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

 

adama dashen

ዛሬ በተደረጉት 3 ጨዋታዎች ተቀይረው የገቡት ባዬ ገዛኸኝ ፣ ሄኖክ መኮንን እና ወንድሜነህ ዘሪሁን ግቦች በማስቆጠር ለክለቦቻቸው ድል ቁልፍ አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉን አዳማ ከነማ በ16 ነጥቦች ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13 ፣ ደደቢት በ11 ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ደግሞ የደደቢቱ ሳሚ ሳኑሚ በ5 ግብ ሲመራ የቡናው ያቤውን ዊልያም እና የአዳማው ታፈሰ ተስፋዬ በ4 ግ ይከተላሉ፡፡

የ6ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ነገ በ11፡30 በኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ መካከል አዲ አበባ ስታየም ላይ ይደረጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *