ፕሪሚየር ሊግ – ሆሳእና የመጀመርያ የሊግ ድል ሲያስመዘግብ አዳማ በአሸናፊነቱ ቀጥሏል

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9፡00 ላይ ተካሂደው ሁሉም ጨዋታ በመሸናነፍ ተጠናቋል፡፡

ወደ ሀዋሳ የተጓዘው የውድድር አመቱ አስደናቂ ቡድን አዳማ ከነማ 2-1 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ሀዋሳ ከነማ በደስታ ዮሃንስ የ45ኛ ደቂቃ ግብ 1-0 መርቶ ወደ መልበሻ ክፍል ቢያመራም ዘንድሮ ሀዋሳን ለቆ አዳማን የተቀላቀለው ታፈሰ ተስፋዬ በ49ኛው እና 80ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ግቦች አዳማ ከነማን ለአሸናፊነት አብቅቷል፡፡ አንጋፋው አጥቂ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በቀድሞ ክለቡ ደጋፊ ፊት ያሳየው የደስታ አገላለፅ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ታፈሰ የግቦቹን ቁጥር 6 በማድረስ የሊጉን የከፍተኛ ግብ አግቢነት ከሳሚ ሳኑሚ ተረክቧል፡፡

ሀዲያ ሆሳእና ዘንድሮ ወደ ሊጉ ካደገ ወዲህ በ7ኛ ሙከራው ድል አድርጓል፡፡በአቢዮ አርሳሞ ስታድየም በቅርብ ሳምንታት ውጤት የከዳው ወላይታ ድቻን 5-1 አሸንፏል፡፡ በድቻ እና ሆሳእና ደጋፊዎች መካከል በተነሳ ግጭት ጨዋታው ሊጀመር ከታሰበበት ሰአት ዘግይቶ በተጀመረው ጨዋታ እንዳለ ደባልቄ እና አበባየሁ ዮሃንስ (ፍፁም ቅጣት ምት) ባስቆጠሯቸው ግቦች የመጀመርያው አጋማሽ ሲጠናቀቅ በ2ኛው አጋማሽ 47ኛው ደቂቃ ላይ ሆሳእናን ወደ ሊጉ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና የተጫወተው ቴዎድሮስ መንገሻ ወላይታ ድቻን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ አስቆጥሯል፡፡ ቴዎድሮስ ቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ ቢያስቆጥርም ደስታውን አልገለጸም፡፡ በአምረላ ፣ አበባው ታምሩ እና ዱላ ሙላቱ በተከታታይ ያስቆጠሯቸው ግቦች ሆሳእናን ለጣፋች የ5-1 ድል አብቅቷል፡፡

ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና መከላከያን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል፡፡ የመከላከያው ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ ጨዋታው በተጀመረ በበ3ኛው ደቂቃ በራሱ ላይ ያስቆጠረው ግብ ሲዳማ ቡናን ባለድል አድርጓል፡፡

በድሬዳዋ ዛሬም አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ ተስተናግዷል፡፡ ድሬዳዋ የሊጉ 3ኛ ተከታታይ ድሉን ባንክ ላይ ባስመዘገበበት ጨዋታ የመስመር አማካዩ ሱራፌል ዳንኤል የብርቱካናማዎቹን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጨዋታው ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ፊሊፕ ዳውዚ ግብ አስቆጥሮ ዳኛው ቢያፀድቁትም ረዳት ዳኛው ከግቡ መቆጠር በፊት ግብ ጠባቂው ላይ ጥፋት ተሰርቷል በሚል ግቡ ተሽሯል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ ንግድ ባንክ ክስ ያስመገበ ሲሆን ጨዋታውም ለረጅም ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዶ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ከፍተኛ ውጥረት እና በርካታ የማስጠንቀቂያ ካርዶች በታዩበት ጨዋታ የአርባምንጭ ከነማን የድል ግቦች ከመረብ ያሳረፉት አጥቂዎቹ ተሸመ ታደሰ እና በረከት ወልደፃዲቅ በመጀመርያው አጋማሽ ነው፡፡

ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ኤሌክሪክን ያስተናገደው ዳሽን ቢራ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ የጎንደሩን ክለብ ብቸኛ የማሸነፍያ ግብ  ሸሪፍ ዲን በ71ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል፡፡ የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ ከዳኛው ጋር በፈጠሩት አለመግባባት በቀይ ካርድ ከቦታቸው ተወግደዋል፡፡

ሊጉን አዳማ ከነማ በ19 ነጥብ ሲመራ በአሁኑ ሰአት ጨዋታውን እደረገ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13 ነጥብ ይከተለላል፡፡ ታፈሰ ተስፋዬ በ6 ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት ይመራል፡፡

የ7ኛው ሳምንት ቀሪ ጨዋታ በአሁኑ ሰአት በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት መካከል በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *