ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ

ከዚህ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በ21ኛው ሳምንት  ባህርዳር ከተማ ላይ ካስመዘገቡት ድል በኃላ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት የተሳናቸው ኢትዮጽያ ቡናዎች ከመውረድ አደጋ እና ከዋንጫ ፉክክር ውጪ ሆነው ጨዋታው እንደማድረጋቸው  ጨዋታው ከመርሃ ግብር ማሟያ ባለፈ ለቡድኑ ትርጉም ይኖረዋል ተብሎ ባይታሰብም ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች በደጋፊዎች መሀል ያለው ቅራኔ ለጨዋታው የሚሰጡትን ግምት ከፍ እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው ነው። ባለፉት ጨዋታዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ለመጫወት ሲሞክሩ የነበሩት ቡናማዎቹ በነገው ጨዋታ አጨዋወታቸው ይቀይራሉ ተብሎ ባይጠበቅም የቋሚ ተሰላፊዎቻቸው ጉዳት  አስገዳጅ የተጨዋቾች ለውጥ እንዲታደርጉ ያስደርጋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ካሉሻ አልሀሰን ከጉዳት የተመለሰለት ቡድኑ ክሪዚስቶም ንታምቢ እና ሑሴን ሻባኒን በብሄራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት የሚያጣ ሲሆን ተመስገን ካስትሮ ፣ ሚኪያስ መኮንን ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ወንድወሰን አሸናፊ ደግሞ በጉዳት ጨዋታው ያልፋቸዋል።   

በጣሏቸው ተደጋጋሚ ነጥቦች ምክንያት የሊጉን መሪነት አሳልፈው የሰጡት መቐለዎች ጨዋታው ከበርካታ ውጤት ማጣት በኃላ በተወሰነ መልኩ ባገገሙበት  ወቅት የሚደረግ እንደመሆኑ ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። በተለይም በሁለተኛው ዙር ከሜዳቸው ውጪ መጥፎ ክብረ ወሰን ያላቸው መቐለዎች የባለፈው ሳምንት የአቻ ውጤት እና የበርካታ ተጫዋቾች ከጉዳት መልስ ማግኘታቸውን ተከትሎ ጥሩ ፋታ ይሰጣቸዋል ተብሎ ቢታሰብም ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ያለው የውጤታማነት ደረጃ ግን አሁንም ደካማ ጎኑ ሆኖ ቀጥሏል። እስካሁን የተጫዋቾችም የአቀራረብም ለውጥ በማድረግ ጨዋታዎቻቸውን ሲያደርጉ የቆዩት ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታ የሚከተሉትን አጨዋወት በእርግጠኝነት ለመገመት ቢያዳግትም ከረጅሙ አጥቂያቸው መመለስ በኃላ እንደተከተሉት አጨዋወት ረጃጅም ኳስ ላይ ያነጣጠረ የማጥቃት አማራጭን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ባለፉት ጨዋታዎች በመስመር ተከላካዮች ጉዳት እና የአቋም መውረድ ምክንያት ውጤታማው የመስመር አጨዋወታቸው ለመቀየር የተገደዱት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የነገው ጨዋታ የሚመርጧቸው የመስመር ተከላካዮች አጨዋወቱን የመወሰን አቅም ይኖራቸዋል ተብሎም ይገመታል። መቐለዎች በነገው ጨዋታ በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– መቐለ ሊጉን በተቀላቀለበት የአምናው የውድድር ዓመት ጅምሮ በተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና የ3-1 መቐለ ደግሞ የ1-0 ውጤት ሲቀናቸው አንድ ጊዜ ያለግብ ተለያይተዋል።

– 15 ጨዋታቸውን በሜዳቸው ያሚያከናወኑት ኢትዮጵያ ቡናዎች እስካሁን ስድስት ጊዜ ድል ሲያደርጉ አምስት የአቻ እና አራት የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበዋል።
                                                                             

– እስካሁን 11 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ያከናወነው መቐለ 70 እንደርታ ስድስት ጨዋታዎችን ሲሸነፍ ሁለቴ ነጥብ ተጋርቶ ሦስት ድሎችን አሳክቷል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል። አርቢትሩ በእስካሁኖቹ 13 ጨዋታዎች 61 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲያሳይ አንድ ጊዜ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሦስት ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተጫዋቾችን ከሜዳ አሰናብቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-2-3-1)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ቶማስ ስምረቱ – ተካልኝ ደጀኔ

 አማኑኤል ዮሃንስ – ዳንኤል ደምሴ

እያሱ ታምሩ – ካሉሻ አልሀሰን – አስራት ቱንጆ

አቡበከር ናስር 
  

መቐለ70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፍሊፕ ኦቮኖ

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተስማ – ክዌኩ አንዶህ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ

ያሬድ ከበደ – ሀይደር ሸረፋ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

 ኦሴይ ማውሊ