የኢትዮጵያ ቡና እና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ በድጋሚ ተራዘመ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ትላንት ያልተካሄደውና ነገ አዳማ ላይ በዝግ ይካሄዳል የተባለው የቡና እና መቐለ ጨዋታ ወደ ሐሙስ መሸጋገሩን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

በፌዴሬሽኑ መግለጫ መሠረት ጨዋታው የቀን ለውጥ ሲደረግበት በአዳማ አበበ ቢቂላ በዝግ እንዲደረግ የተወሰነው ውሳኔ ግን ፀንቷል።

የፌዴሬሽኑ መግለጫ ይህንን ይመስላል:-

በ27ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ግንቦት 25/2011ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ጨዋታው መሰረዙ ይታወቃል፤ የሊግ ኮሚቴ ጨዋታው በጸጥታ ስጋት ምክንያት አለመካሄዱን ተከትሎ ግንቦት 27/2011ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያለ ተመልካች /በዝግ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል፤ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ውሳኔውን በመቃወም ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን ጉዳዩን የተመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል የተሰረዘው ጨዋታ ከመንግስት ጸጥታ ኃይል በደረሰ መረጃ የደህንነት ስጋት በስታዲየም እንዳለ በማሳወቁ በመሆኑ እና አሁንም በድጋሚ በተደረገው ውይይት ይህ ጉዳይ በጥብቅ ሊታይ የሚገባው በመሆኑ እና የመንግስት የጸጥታ ኃይልም የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ባሉበት ጨዋታው መካሄድ የሌለበት መሆኑን በጥብቅ አስገንዝቦናል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን ግንቦት 27/2011ዓ.ም ለማካሄድ የዒድ አል ፈጥር በዓል ስለሆነ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሐሙስ ግንቦት 29/2011 ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በ9 ሰዓት ያለ ተመልካች በዝግ ይካሄዳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡