“ብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ምጥጥን ያስፈልጋል” የሱፍ ሳሌህ

ኢትዮጵያዊው የመስመር አማካይ የሱፍ ሳሌህ ለስዊድኑ አንደኛ ዲቪዚዮን ክለብ ኤኤፍሲ ዩናይትድ በመጫወት የውድድር ዓመቱን አሳልፏል፡፡ 15 ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ግብ ማስቆጠር የቻለው የሱፍ በአሁኑ ወቅት ለዕረፍት አዲስ አበባ ይገኛል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው ተጫዋቹ አሁን ስላለበት ሁኔታ እንዲሁም ስለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና መሰል ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ 

 

ስለኤኤፍሲ ዩናይትድ የ2015 የውድድር ዘመን ቆይታው

‹‹ ኤኤፍሲ ዩናይትድን የተቀላቀልኩት በአጭር ጊዜ ውል ነበር፡፡ በመጀመሪያ ጉዳት ላይ ስለነበርኩ ጨዋታዎችን ማድረግ አልቻልኩም ነበር፡፡ ከጉዳቴ ካገገምኩ በኃላ ጥቂት ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችዬ ነበር ነገር ግን አሁንም ጉዳት አጋጥሞኝ ጉዳቴን ማስታመም ነበረብኝ፡፡ ሊጉ ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት ሲቀሩት ግን ወደ ሜዳ ተመልሼ አብዛኛው ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችያለው፡፡

‹‹ አሁን ከክለቡ ጋር የነበረኝ ውል በመጠናቀቁ ከክለቡ ለቅቄያለው፡፡ ባጠቃላይ በክለቡ ጥሩ ጊዜ አሳልፊያለው፡፡ ሰዎች አንደኛ ዲቪዚዮን ስለሆነ ቀላል ውድድር ነው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ እውነታው ግን ሊጉ ፉክክር የበዛበት እና ፈታኝ ነው፡፡ ››

 

ለ ዝውውር መስኮቱ

‹‹ የዝውውር መስኮቱ ተከፍቷል፡፡ ወኪሌ ማድረግ ያለበትን ነገር ያውቃል፡፡ አሁን አዲስ አበባ ለዕረፍት ስለመጣው ምንም ዓይነት ከእግርኳስ ጋር የተገናኘ ነገር መስማት እንደማልሻ ለወኪሌ ነግሬዋለሁ፡፡ ከዕረፍቴ ተመልሼ ወደ ስዊድን ስሄድ ነው ቀጣዩ ክለቤን የማውቀው፡፡ አሁን ለውሳኔ አልፈጥንም፡፡ 

‹‹ እስካሁን በስዊድን እና በሌሎች የአውሮፓ ክለቦች የተጫወትልን ጥያቄ ቀርቦልኛል፡፡ ሁሉንም ነገር ከዕረፍቴ በኃላ እወስናለው፡፡ ››

 

በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብዙ ክለቦችን ስለመቀያየሩ

‹‹ አዎ ክለቦችን እቀያይራለው፡፡ ምክንያቴ ደግሞ አብኛውን ግዜ የአጭር ጊዜ ውል ስለምፈርም ነው፡፡ የአጭር ጊዜ ውል የምፈርመው የተሻለ ነገር ካገኘሁ ክለቡን ለመልቀቅ እንዲሁም የማያስማማኝ ነገር ከገጠመኝ ከክለቡ ለመለያየት ነው፡፡ አዳዲስ አሰልጣኞች ሲቀጠሩ የጨዋታ ፍልስፍናቸው ላይመቸኝ ይችላል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች የአጭር ጊዜ ውል ነው የምፈርመው፡፡ ሰዎች የአጭር ጊዜ ውል መፈረም በጣም ጉዳት አለው ይሉኛል ነገር ግን ውሉን በመፈረሜ እኔን ያጋጠመኝ ችግር የለም፡፡ የምጫወትበት ክለብ አግኝቻለው፡፡ በሚገርም ሁኔታ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጫወቴ እና ስዊድን ውስጥ ባለኝ ጥሩ ስም ምክንያት የምጫወትበት ክለብ አጥቼ አላውቅም፡፡ አንዳንድ የሰዊድን ሊግ ክለቦች የሶስት ዓመት ውል እንድፈርም ያነጋግሩኛል ነገርግን ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጊያለው፡፡ ››

 

በቱርክ ለመጫወት ስለነበረው ዕድል

‹‹ በቱርክ ሊግ ዋሊድ ይጫወትበት ለነበረው ገንሰልበርሊጊ ለመጫወት ከጫፍ ደርሼ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ጥር ላይ እኔን እና ዋሊድን በስዊድን ኤአይኬ ያሰለጠነን ስዊድናዊ አሰልጣኝ ገንሰልበርሊጊን ሰኔ ላይ ለማስልጠን ተስማምቶ ስለነበር ወደ ቱርክ ሊያመጣን እንደሚፈልግ ገልፆልን ነበር፡፡ እስከዛ ድረስ ክለብ መፈለግ ስለነበረብኝ አይኬ ሲሪስን በ6 ወር ውል ተቀላቀልኩ፡፡ የስዊድን አንደኛ ዲቪዚዮን የውድድር ዓመት የሚጀምረው ጥር ላይ ስለሆነ ውሌ ሰኔ ላይ ሳይጠናቀቅ በመቅረቱ እንዲሁም አሰልጣኙ በክለቡ ባለመቀጠሩ ሳልፈርም ቀርቻለው፡፡ ዋሊድ ከቤኬ ሃከን ጋር ውሉን በመጨረሱ ወደ ቱርክ ሊጓዝ ችሏል፡፡ ››

 

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን ከማላዊው ጨዋታ ወዲህ ስላለመጠራቱ

‹‹ አሁን አዲስ አሰልጣኝ ነው ያለው ስለዚህ አለመጠራቴ አልገረመኝም፡፡ በጣም የገረመኝ አሰልጣኙ ስለኔ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው መግለፃቸው ነው፡፡ እኔ እና ዋሊድ በስዊድን አንድ ላይ ስለነበርን የዋሊድን ወቅታዊ አቋም የት አይተው እንደጠሩት ባውቅ ጥሩ ነበር፡፡ ትንሽ የሚያደናግር ነገር ነበር፡፡

‹‹ አሰልጣኙ ከያዙት በኃላ የብሄራዊ ቡድኑን ጨዋታዎች ለማየት አልቻልኩም፡፡ ዋሊድ እንደነገረኝ ከሆነ ብሄራዊ ቡድኑ አሁን አዲስ ዘመን ላይ ይገኛል፡፡ አሰልጣኙ ወጣት ተጫዋቾች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ዋሊድ ጨምሮ ነግሮኛል፡፡ አዳዲስ ፊቶች በብሄራዊ ቡድኑ መታየታቸው መልካም ሆኖ ሳላ ቡድኑ ምጥጥን ያስፈልገዋል፡፡ ነባሮቹ በሙሉ በአንድ ጊዜ ከቡድን ማግለል ተገቢ አይደልም፡፡ አዳዲሶቹን ከልምድ ካላቸው ጋር ማቀናጀት ትክክለኛው አካሄድ ይመስለኛል፡፡ ››

 

በማሪያኖ ባሬቶ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝነት ዘመን ብዙ ጨዋታዎችን ስለማድረጉ

‹‹ ባሬቶ በአውሮፓ ያሰለጠነ እና ልምድ ያለው አሰልጣኝ ነው፡፡ የአውሮፓ እግርኳስን ጠንቅቆ ማወቁ ያለኝን ብቃት እንዲረዳ አድርጎታል፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ዘመን ዕምብዛም የመሰለፍ ዕድል አልተሰጠኝም ነበር፡፡ ምክንያቱን ደግሞ እኔ ሳልሆን አሰልጣኝ ሰውነት ነው የሚያውቀው ስለዚህ እሱን ብትጠይቁት ይሻላል፡፡ ››

 

ስለቀጣዩ ዕቅዱ

‹‹ 31 ዓመቴ ነው፡፡ ያለኝ ጉልበት እና ተክለ ሰውነቴ ለዓመታት እግርኳስን ሊያጫውተኝ ይችላል፡፡ ያረጀው አይመስለኝም፡፡ አንዳንድ አሰልጣኞች ለቀጣዮች 5 እና 6 ዓመታት መጫወት ትችላለህ ይሉኛል፡፡ ስለዚህ እግርኳስን ሳቆም ስለምሰራውን ነገር ዕቅድ አላወጣሁም፡፡ ››

 

ስለዋሊድ አታ 

‹‹ ዋሊድ እና እኔ ኤአይኬ ነው የምንተዋወቀው፡፡ በኤአይኬ የስዊድን ሊግ ሻምፒዮን መሆን ችለን ነበር፡፡ የመኖሪያ አፓርትመንታችን ቅርብ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜ አብረን ነበር የምናሳልፈው፡፡ የሱ ቤተሰቦች እና የኔ ቤተሰቦች የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ ዋሊድ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲጫወት የገፋፋሁት እና የመከርኩት እኔ ነበርኩ፡፡

‹‹ ዋሊድ ከገንሰልበርሊጊ ጋር መለያየቱ አልገረመኝም፡፡ እንዲቆይ ፈልገው እንደነበር ነግሮኛል፡፡ ነገርግን ቢቆይ የመሰለፍ ዕድሉን ማግኘቱን እጠራጠራለው፡፡ ››

 

ስለትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች 

‹‹ ጥሩ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በስዊድን ሊግ ከጨዋታ በኃላ ያነጋግሩኛል፡፡ ለዋሊያዎቹ የመጫወት ያላቸውን ጉጉት ይነግሩኛል ፤  እንዲሁም ብዙ ጥያቄዎችን ስለብሄራዊ ቡድኑ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ እነዚህን ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ መሳብ የሚቻለው ውጤት ሲኖር ነው፡፡ ውጤት ካለ ብዙ ተጫዋቾችን እንዲጫወቱልህ ልታደርግ ትችላለህ፡፡ አገር በቀሎቹ ጋር በማዋሃድ ብዙ ስራ መስራት ይቻላል፡፡ በብሄራዊ ቡድን የተጫወትነውም ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ሌሎች እንዲጫወቱ ማግባባት አለብን፡፡ ለምሳሌ እኔ ዋሊድን እንዳግባባሁት ሌሎችንም ማግባባት ቢቻል መልካም ነው እላለው፡፡ ››

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን መለያ መልበስ ስለፈጠረበት ስሜት

‹‹ በጣም የተለየ ስሜት ነበር የፈረብኝ፡፡ በስዊድን ወጣት ብሄራዊ ቡድን ስጫወት ጥቁሮችን ማግኘት በጣም ያስቸግር ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ነጭ መሆናቸው ትንሽ የመገለል ስሜት እንዲሰማህ ያደርገሃል፡፡ ስዊድን ብወለድም ቤተሰቦቼ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ስጫወት ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የቆዳ ቀለም፣ ባህል እና አመጋገብ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር ነው የተጫወትኩት፡፡ ይህ ደግሞ የተለየ ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡ ቤቴ መሆኑ ያኔ ነበር የተሰማኝ፡፡ የደጋፊው ድባብ በጣም ደስ ይላል፡፡ ስሜቱ ልዩ ነው፡፡ ››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *