ቅዱስ ጊዮርጊስ ያዘጋጀው ሲምፖዚየም ተካሄደ 

የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማክበር ላይ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን በሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ ያዘጋጀው ሲምፖዚየም ተካሂዷል፡፡ 

የክለቡ የቦርድ ፕሬዝደንት አብነት ገብረመስቀል ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ጁነይዲ ባሻ ፣ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት ብርሃነ ኪዳነማርያም እና የክለቡ የቀድሞ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እና ደጋፊዎች በተገኙበት መድረክ ፈረሰኞቹ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት ስላበረከቱት አስተዋፅኦ እና ስለታሪካዊ ተጫዋቾቹ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ የቀድሞ ዕውቁ ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ በመሩት ውይይት ላይ የክለቡ ደጋፊዎች ስለስታዲየም ግንባታው መጓተት ጥያቄ አንስተዋል፡፡

 

በስምፖዚየሙ ላይ የተነሱ ወሳኝ ነጥቦችን እነሆ ብለናል፡፡

 

አቶ አብነት ገብረመስቀል

” በታሪክ ልንኖር አንችልም፡፡ ታሪክ የሰሩትን እናመሰግናለን፡፡ እና ደግሞ ታሪክ መስራት መቻል አለብን፡፡ ምኞታችን ተጫዋቾቻን ከክለብም አልፎ የሃገራቸውን ስም እዲያስጠሩ ነው፡፡ ብቻችንን መፎካከር አንችልም፡፡ እኛ የምንፈልገው 1 እና 2 ጠንካራ የህዝብ ክለቦች እንዲኖሩ ሳይሆን 5 እና 10 ከተቻለም ከዛ በላይ እንዲኖር ነው፡፡ ጉድለታችንን ስትነግሩን አሜን ብለን መቀበል መቻል አለብን፡፡ የስታዲየሙ ግንባታ ተቋረጠ እንጂ አልቆመም፡፡ ግንባታው ይጀመራል፡፡ የክለቡም አንድ ራዕይ ይህ ስታዲየም ተጨርሶ መመልከት ነው፡፡ ”

 

አቶ ጁነይዲ ባሻ

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፋና ወጊ እና ጅማሬ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ግዜ ላደረገው ሁሉ ክለቡ ምስጋና እና ክብር ይገባዋል፡፡ ክለቡ ለብሄራዊ ቡድን ብዙ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች አፍርቷል፡፡ ክለቡ አፍሪካ መድረክ ተከታታይነት ያለው ውጤት ማስመዝገብ አለበት፡፡ ይህ የኢትዮጵያ እግርኳስ እድገትን የሚጠቅም ነው፡፡ ”

 

ገብረመድህን ሃይሌ

“የቅዱስ ጊዮርጊስ ተፅእኖ ፈጣሪነቱ በሃገር ውስጥ ብቻ መገደብ የለበትም፡፡ በአፍሪካም ላይ መታየት አለበት፡፡ ክለቡ በአፍሪካ መድረክ የሚያስመዘግበው ውጤት ለኢትዮጵያም ወሳኝነት አለው፡፡ እንዲሁም በችግር ላይ የሚገኙትን የቀድሞ ተጫዋቾቹን ቢረዳ ጥሩ ነው እላለው፡፡ ”

 

ፋሲል ተካልኝ

“ጊዮርጊስ ውስጥ በመጫወቴ እና በመስራቴ ክብር እና ኩራት ይሰማኛል፡፡ ጊዮርጊስ ልክ እንደትምህርት ቤት ዓይነት ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን ተምሬበታለው፡፡ የማንነት መገለጫ ነው፡፡ ከህይወታችን ጋር የተቆራኘ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል፡፡ በነዚህም ችግሮች መሃል የአፍሪካ ታላቅ ይሆናል ማለት ይከብዳል ነው፡፡ ጊዮርጊስ ልክ እንደነ አል-አሃሊ፣ ዛማሌክ እና ቲፒ ማዜምቤ በአፍሪካ ሃያል የሚሆንበት ግዜ ሩቅ አይደለም፡፡”

 

ፍቅሩ ኪዳኔ

” አንድ ተጫዋች ኳስ ካቆመ በኃላ ስራ ፈት ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህም ተጫዋቾቻችን መማር መቻል አለባቸው፡፡ ኳስ ካቆሙ በኃላ ሊሰሩት የሚችሉት ነገር መኖር አለበት፡፡ በትምህርቱ ዓለም ከገፉ ደግሞ ይህንን ማሳካት ይችላሉ፡፡ አብዛኞው የጊዮርጊስ ተጫዋች ስለተማረ እራሱን የቻለ ነበር፡፡ ለምሳሌ ተቀዳ አለሙን ተመልከቱ፤ ተቀዳ ለጊዮርጊስ ተጫውቶ በመማሩ ሃገሩን እስከሚንስትርነት ማገልገል የቻለ ሰው ነው፡፡ ስፖርት ሊለማ የሚችለው በትምህርት ቤቶች ሲስፋፋ ነው፡፡ በቀደምት ግዜያት የጊዮርጊስ አብዛኞቹ ተሰላፊዎች ከትምህርት ቤት ውድድሮች የተገኙ ናቸው፡፡ በትምህርት ቤቶች ስፖርት ከሌለ ስለስፖርት ዕድገት ማሰብ ፈፅሞ የማይቻል ነው፡፡ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ የጋራ መኖርያ ቤቶች ሲገነቡ ለህፃናት ኳስ የሚጫወቱበት ስፍራ ተብሎ የተዘጋጀ ሜዳ የለም፡፡ ህፃናት በየባቡር ሃዲዱ ኳስ ለመጫወት እየተገደዱ ነው፡፡ ይህ ችግር መቀረፍ አለበት”

IMG_9688

 

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል እስከ ሚያዚያ 30 የሚቆይ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ዕሁድ ጥር 1 በአዲስ አበባ ስታዲየም የክብረ በዓሉ ማድመቂያ የሆነውን የወዳጅነት ጨዋታ ከሱዳኑ አል-ሜሪክ ጋር በ10፡00 ያደርጋል፡፡ ፈረሰኞቹ ጥር 5 ቀን ከኬኒያው ሻምፒዮን ጎር ማሂያ ጋር በሁለተኛው የወዳጅነት ጨዋታ የሚገናኝ ይሆናል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *