” የቻን ግባችን ካለፈው ውድድር የተሻለ ውጤት ማምጣት ነው ” አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በቻን 2016 ዙርያ ዛሬ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

 

የቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ …

‹‹ እንደሚታወቀው ቡድኑ ልምምድ ጀምሯል፡፡ ከመረጥናቸው 30 ተጫዋቾች መካከል ዳዊት ፍቃዱ እና ለአለም ብርሃኑ በጉዳት ራሳቸውን ከቡድኑ ውጪ አድርገዋል፡፡ በለአለም ምትክም በአስቸኳይ በአሊ ረዲ አማካኝነት የዳሽን ቢራውን ደረጄ አለሙ መርጠናል፡፡ ከአጠቃላይ 29 ተጫዋቾች ውስጥ ሞገስ ፣ አስቻለው እና ታሪክ በሀኪም ፍቃድ ተሰጥቷቸው ለጥቂት ጊዜ እረፍት ይወስዳሉ፡፡ በሂደት ካላገገሙ ሊቀነሱ ይችላሉ፡፡ ስዩም ተስፋዬ በግል ጉዳይ ምክንያት ፍቃድ ተሰጥቶት ትላንት ልምምድ አልሰራም፡፡ ነገር ግን ማታ ሆቴል ገብቶ ቡድኑን ተቀላሏል፡፡

‹‹ ወደ ውድድሩ ከመሄዳችን በፊት 7 ተጫዋቾች መቀነስ ስላለብን እያንዳንዳቸው ያላቸውንአቋም ለማወቅ የአካል ብቃት ፍተሻ በዶ/ር ኤልያስ አማካኝነት እየተደረገ ነው፡፡ ፍተሸውን ጠዋት የጀመርን ሲሆን የስብ መጠናቸውን ለክተናል፡፡ ከሰአት በኋላ ደግሞ ሌላ ፍተሻ እናደርጋለን፡፡ ነገ ተጨማሪ ቴስት ወስደን የተጫዋቾቻችንን ደረጃ እናውቃለን፡፡

‹‹ ዘመኑ የሳይንስ ነው፡፡ ስለዚህ መሸዋወድ አይቻልም፡፡ አንድ ናጄርያዊ ተጫዋች በሰአት 17 ኪሜ የሚሮጥ ከሆነ የኛ ለምን አይሮጥም? የኢንዱራንስ ችግር ካለባቸው አልተሰራባቸውም ማለት ነው፡፡ በኢንዱራንስ ደረጃ በአትሌቲክሱ ከአለም አንደኛ ነን፡፡ ስለዚህ የተጫዋቾቻችን ደረጃ እንዲሻሻል ማድረግ አለብን፡፡

‹‹ የወዳጅነት ጨዋታ አንድ ሃገራችን ላይ አንድ ደግሞ ከሃገር ውጪ ለመጫወት ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡ እስካሁን ግን የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ አልቻልንም፡፡ ሌላው የጠየቅነው የህክምና ባለሙያ እንዲሟላልን ነበር ተሟልቶልናል፡፡ ››

 

ስለ ምርጫው

‹‹ በዚህ ስብስብ ከሴካፋው ውድድር ያመጣነው 8 እና 9 ተጫዋቾን ነው፡፡ በዚህ አመት ብዙ ጨዋታ ያላደረጉ ፣ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ ያላቸው እና ወቅታዊ አቋማቸው ጥሩ የሆኑ ተጫዋቾችን ነው የመረጥነው፡፡ ከቡልቻ ውጪ ሁሉም የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ አላቸው፡፡ ከሴካፋ አንፃር 23 ተጫዋቾች መመረጣቸው አድቫንቴጅ አለው፡፡ ከ23 ውስጥ ደግሞ አብዛኛዎቹ በሴካፋ ያልተጫወቱ ናቸው፡፡ በአመራረጥ ደረጃ በእያንዳንዱ ቦታ 2 ተጫዋች ይዘናል፡፡ የድካም እና የጉዳት ችግር ቢመጣ በአንደኛው ምትክ ሌላኛው እንዲሰለፍ እናደርጋለን፡፡ ››

 

የብሄራዊ ቡድኑ የቻን ግብ

‹‹ ካለው ጊዜ አንጻር ልምድ ያላቸው እና በጥሩ አቋም ላይ ያሉ ተጫዋቾችን የመረጥነው፡፡ 90 በመቶ አሉ የሚባሉ ተጫዋቾችን መርጠናል፡፡ ፍፁም ስላልሆንን በመቶ መርጠናል ልንል አንችልም፡፡ ያልመረጥነው ሊኖር ይችላል፡፡  ተጫዋቾቹ ብዙ የመጫወት ልምድ እስካላቸው ድረስ ለተሳትፎ ብቻ አይደለም የምንሄደው፡፡ በምንም መንገድ ካለፈው የተሻለ ነገር ይዘን መምጣት አለብን የሚለው ግባችን ነው፡፡ ››

 

ዲሲፕሊን

‹‹ በዲሲፕሊን ጉዳይ ከኛ የበለጠ እናንተ መመስከር ትችላላችሁ፡፡ በእኔ ዘመን በተጫወትነው 18 እና 19 ጨዋታ 1 ቀይ ብቻ ነው ያየነው፡፡ ስለዚህ በዲሲፕሊን ደረጃ ጥሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ዲሲፕሊን ወሳኝ ነው፡፡ እንደውም በሴካፋ ውድድር በፌይር ፕሌይ ኢትዮጵያ አንደኛ ነበረች፡፡ በውድድሩ ጠቅላላ 5 ቢጫ ብቻ ነበር ያየነው፡፡ የመጀመርያው ጨዋታ ላይ 3 ሲመለከቱ በቀሩት 5 ጨዋታ 2 ብቻ ነው ያየነው፡፡ ከተጫዋቾቼ ጋር በዲሲፕሊን ጉዳይ ትላንትም ተወያይተንበታል፡፡ ማሸነፍ እና መሸነፍ የሚመጣው በመረበሽ ወይም ስርአት በማጉደል እንዳልሆነ ተነጋግረናል፡፡ የያዝናቸው ተጫዋቾችም ልምድ አላቸው፡፡ የተሻለ ያገናዝባሉ ብለን እናምናለን፡፡››

 

ጊዜ

‹‹ የጊዜው ጉዳይ ምክንያት እንዲሆን አንፈልግም፡፡ ከሌሎች አንፃር ስናወዳድር እኛ ወደኋላ ቀርተናል፡፡ እነ ናይጄርያ ከ20 ቀን በፊት ነው የጀመሩት፡፡ መርጠው ጨርሰው የወዳጅነት ጨዋታ አድርገዋል፡፡ የጊዜው ጉዳይ ከፌዴሬሽኑ የካላንደር አሰራር ጋር ሊሆን ይችላል፡፡ ያለን አማራጭ እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ማድረግ ያለብንን ነገር ማድረግ ነው፡፡ የፊትነስ ቴስት ያስፈለገውም በጥሩ አካል ብቃት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን ለመውሰድ በማሰብ ነው፡፡ ካለበለዚያ ችግር ውስጥ እንዳንገባ ፡፡ በክለቦቻችን የተጫዋቾች የፊትነስ ደረጃ ዳታ የለም፡፡ ያ ቢኖር ኖሮ አንጨነቅም ነበር፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ሜዳ ላይ ብቻ አይቶ መምረጥ ነው፡፡ ሜዳ ላይ ደግሞ በእለቱ ጥሩ የሆነው ተጫዋች ይሸውድሃል፡፡ ሌላው ቀርቶ በብሄራዊ ቡድን የፊትነስ አሰልጣኝ ራሱ የለም፡፡ ስለዚህ ክፍተቶች አሉ፡፡ ክለቦች በሚልዮን ብር ይመድባሉ፡፡ የተጫዋቾቹ ደረጃ ግን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አይቀመጥም፡፡ አሰራሮች እስካልተቀየሩ ድረስ ችግሮች መኖራቸው አይቀርም፡፡››

 

በየጊዜው ስለሚመረጡ ተጫዋቾች

‹‹ እንደምንወዳደርባቸው ጨዋታዎች የምንመርጣቸውም ተጫዋቾች ይለያያሉ፡፡ በቻን የሚጫወት እና በአፍሪካ እና አለም ዋንጫ ማጣርያ የሚጫወት ይለያያል፡፡ ሴካፋ ላይ ደግሞ ለወጣቶች እድል መስጠት ነበር እቅዳችን፡፡ ከዚህ በፊት በብሄራዊ ቡድኑ ከነበሩት ውስጥ ጀማል ተመርጦ ነበር ፡፡ ጀማል በአንድ ልምምድ ሲጎዳ በእነ አቤል እና ታሪክ አዲስ ትውልድ መስርተናል፡፡ ተከላካይ ስፍራ ላይ ደጉ ሳላዲን እና አይናለም ነበሩ፡፡ ሁለቱ (ደጉ እና አይናለም) ሲያቆሙ እነ አስቻለውን ማምጣት አለብን፡፡ ስለዚህ ሁኔታው ነው አዳዲስ ተጫዋች እንድትመርጥ የሚያስገድደው፡፡ መስመር ተከላካይ ላይ ስዩም ጥሩ ስለሆነ እስካሁን ቦታው ላይ ይጫወታል፡፡ አበባው እና ብርሃኑ በጉዳት እና አቋም መውረድ ምክንያት አሁን ልመርጣቸው አልችልም፡፡ ስለዚህ ከተካልኝ እና ዘካርያስ ውጪ ማንን ላሰልፍ?  አማካይ ላይ አዲስ ህንፃ በአቋም መውረድ ምክያት ከኔ በፊት የነበሩትም አልመረጡትም፡፡ አስራት ደግሞ ተመርጦ በጉዳት ተቀነሰ፡፡ ስለዚህ በነሱ ምትክ ተጫዋች ማምጣት አለብህ፡፡ ጌታነህ እና ሳላዲን ጥሩ ቢሆኑ እንኳን ቻን ላይ አይሰለፉም፡፡ ስለዚህ እነሱን የሚተካ ተጫዋች ያስፈልጋል፡፡

‹‹ ስለዚህ ምን ማድረግ ነበረብኝ? ሴካፋን ብዙ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ ለሌላቸው ተጫዋቾች እንዲዘጋጁበት አደርገናል፡፡ በሃገር ውስጥ ከሚጫወቱ የሽመልስን ቦታ የሚተካው ኤልያስ ነው፡፡ አሁን ካሉት ውጪ ለብሄራዊ ቡድኑ ጥሩ ናቸው የሚባሉ ሌሎች ግብ ጠባቂዎች እንማን ናቸው? በተከላካይ ስፍራ እነ ተካልኝ እና አስቻለውን ካልመረጥኩ ማን ነው የሚመረጠው? ››

 

ቋሚ 11 አለመኖሩ

‹‹ ቤስት 11 የሚባል ነገር አይገባኝም፡፡ ቤስት 11 ማለት ውድድር ሰጠናቀቅ የምንመርጠው ምርጥ ስብስብ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የአለም ዋንጫ ውድደር ሲጠናቀቅ በየቦታቸው ጥሩ የተንቀሳቀሱ ተጫዋቾች ከየሃገራቱ ተመርጠው ቤስት 11 ይባላሉ፡፡

‹‹ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ቤስት 11 ይሁን ማለት እኮ በፕሮሰስ አናምንም ማለት ነው፡፡ ለምትጋጠመው ቡድን ሲስተም የሚጠቅመኝ ማን ነው ፣ የጨዋታው ደረጃ (ወሳኝነቱ) ጉዳት እና ቅጣት ቋሚ 11 ተጫዋቾችን ለመምረጥ ወሳኝ ነው፡፡ ሁልጊዜ ቤስት 11 ይኑር ማለት እኮ 11 ተጫዋቾች አይነኬ ሆኑ ማለት ነው፡፡እንዲህ ከሆነ ቤንች ላይ ያለው መቼ ሊጫወት ነው፡፡ ››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *