የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

ሁሉም የፕሪምየር ሊግ አላፊዎች ነገ ሊታወቁ ይችላሉ

የከፍተኛ ሊጉ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ከሦስቱም ምድቦች ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያድጉ ክለቦችም ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሊለዩ ይችላሉ። በምድብ ሀ ወደ ለገጣፎ የሚያመራው ሰበታ ከተማ ከለገጣፎ ለገዳዲ በሚያደርገው ጨዋታ ቢያንስ አቻ መለያየት ከ2003 በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ በቂው ነው። በምድብ ለ ወልቂጤ ከተማ ወደ አርሲ ነገሌ የሚያመራ ሲሆን በጨዋታው አቻ መውጣት ወይም የመድን ነጥብ መጣል በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ትኬትን እንዲቆርጥ ያስችለዋል። በምድብ ሐ ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕና በሜዳው ሺንሺቾን ማሸነፍ ከ3 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመልሰው ይሆናል።

ቅሬታ

– በዚህ ሳምንት ሌሎች ምድቦች መደበኛ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲከናወኑ በምድብ ሐ ባለፈው ሳምንት ያልተደረጉት የ20ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች እና የ21ኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በዚህም መሠረት ነቀምት ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ከ ከንባታ ሺንሺቾ ይጫታሉ። ይህን ተከትሎ የአርባምንጭ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ አበራ ወደ ነቀምት አምርተው የሚያደርጉት ጨዋታ ከፀጥታ አንፃር አስጊ መሆኑን ገልፀው የውድድር ኮሚቴ ውድድሩን እንዲለወጥ ቢጠይቁም የእምቢታ ምላሽ እንደተሰጣቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም አህመድ በበኩላቸው ” የአርባምንጭ ጥያቄ ተስተካካዩን በይድር እናስቀምጠውና የ21ኛ ሳምንት ጨዋታን ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር እናከናውን የሚል ነው። በዚህ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ስናከናወን ማንኛውንም ተስተካካይ ጨዋታ ቅድሚያ እየሰጠን ነው። ውድድሩ ከመቼውም
ጊዚ በላይ በሠላም እና በታሰበለት ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ነው የቀረው። ለማንም ቡድን ያልተደረገ ነገር ለአንድ ቡድን አይደረግም። ጨዋታውን በወጣለት ሰዓት እና ቦታ በመገኘት ማከናወን አለባቸው። ውድድሩ በህግ እና በደንብ ነው የሚመራው። ” ሲሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጥተዋል።

– ሀዲያ ሳዕና በዚህ ሳምንት ለሚያደርገው ጨዋታ ከፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አንድ ሰው እንዲገኙለት መጥራቱን ተከትሎ አቶ
ኢብራሂም አህመድ ወደ ቦታው ጉዞ ሊያድርጉ ቢታሰብም በቦታው ላይ መገኘት እንደማይችሉ ታውቋል። በዚህም ምክንያት ቅር የተሰኙት የሆሳዕና ኃላፊዎች “የሥራ አስፈፃሚው ይህን ለምን እንዳደረገ ግልፅ አይደለም። እኛ ይህን ጥሪ ለማድረስ ከሆሳዕና አዲስ አበባ በመምጣት በደብዳቤ የሰጠን ሲሆን ከዚህ ቀደም በመቐለ፣ ባህርዳር፣ ፋሲል፣ ጅማ እንዲሁም በሌሎች የክልል ከተሞች ይገኙ ነበር። ለምን ዛሬ እንዳተገኙ ግልፅ አይደለም።” ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል።

የማጠቃለያ ውድድር

የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ድሬዳዋ ላይ እንደሚከናወን አስታውቋል። ምድባቸውን በአንደኝነት የሚጠናቅቁት ቡድኖች ወደ ድሬዳዋ ከማሩ በኋላም እርስ በእርስ ጨዋታ አድርገው ከፍተኛ ነጥብ የሰበሰበው ቡድን የከፍተኛ ሊጉ አጠቃላይ አሸናፊ ይሆናል። ውድድሩ በ2008 ሲጀመር አዲስ አበባ (አበበ ቢቂላ)፣ በ2009 ድሬዳዋ፣ በ2010 ደግሞ አዳማ ላይ የፍፃሜ ጨዋታ መከናወኑ የሚታወስ ነው።

የሳምንቱ ጨዋታዎች
(ሁሉም ጨዋታዎች እሁድ ይደረጋሉ)

ምድብ ሀ (21ኛ ሳምንት)

አክሱም ከተማ (9:00) አውስኮድ
ወሎ ኮምቦልቻ (9:00) ፌዴራል ፓሊስ
ወልዲያ (9:00) ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ለገጣፎ ለገዳዲ (9:00) ሰበታ ከተማ
ደሴ ከተማ (9:00) አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ
ቡራየለ ከተማ (9:00) ገላን ከተማ

ምድብ ለ (21ኛ ሳምንት)

ኢትዮጵያ መድን (9:00) ድሬዳዋ ፓሊስ
የካ ክ/ከተማ (9:00) ዲላ ከተማ
አዲስአበባ ከተማ (9:00) ናሽናል ሲሚንቶ
ሶዶ ከተማ (9:00) ኢኮስኮ
ነገሌ አርሲ (9:00) ወልቂጤ ከተማ
ሀላባ ከተማ (9:00) ሀምበሪቾ

ምድብ ሐ (20ኛ ሳምንት ተስተካካይ እና 21ኛ ሳምንት)

ሀዲያ ሆሳዕና (9:00) ከምባታ ሺንሺቾ
ነቀምት ከተማ (9:00) አርባምንጭ ከተማ

ቡታጅራ ከተማ (9:00) ካፋ ቡና
ስልጤ ወራቤ (9:00) ነገሌ ቦረና
ቤንች ማጂ ቡና (9:00) ሻሸመኔ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡