የእለቱ ዜናዎች፡ ሰኞ ህዳር 4 ቀን 2010 

አስመራጭ ኮሚቴ 

ከ42 ቀናት በኋላ የሚደረገው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫን ለማካሄድ በሚሰየመው የአስመራጭ ኮሚቴ እና የምርጫ እንቅስቀቃሴን በሚመለከት በቅርቡ የፊፋ ተወካዮች አዲስ አበባ እንደሚገቡ ታውቋል፡፡ ተወካዮቹ በምርጫው ዙርያ ከፌዴሬሽኑ ጋር ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን እስከ ምርጫው ድረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ላይም ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡ [በዳንኤል መስፍን]


አቶ ተክለወይኒ ይቅርታ ጠይቀዋል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር መነጋገርያ ሆነው መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡ አቶ ተክለወይኒ ዛሬ በመቀለ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ላደረጉት ያልተገባ ንግግር ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

” ባለፉት ግዜያት በትግራይ እና በ ሃገር ደረጃ በነበሩት የስፖርት እንቅስቃሴዎች በተለይም በትግራይ ስቴድየም ፕሮጅክት እና በ የደረጃው ያሉ ክለቦችን ለማጠናከር በተሰሩት ስራዎች በግሌም ድርጅቴን ወክዬም ትልቅ አስተዋፅኦ አርግያለው፡፡ በ4 ኣመት የፌደሬሽኑ ቆይታዬም በፌደሬሽኑ የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት የበኩሌን ተወጥቻለው፡፡ ዘመናዊ ያልነበረው የተጫዋቾች የዝውውር ስርአት ለማስተካከል እና በፋይናንሱ በኩልም እኔ በቆየሁባቸው 4 አመታት ፌደሬሽኑ 300 ሚልየን የሚጠጋ ብር እንዲያገኝ የበኩሌን ኣስተዋፅኦ ኣበርክቻለሁ:: 

” ሆኖም በ10ኛው የፌደሬሽኑ ጉባኤ መቀለ እንዲካሄድ ከነበረኝ ፍላጎት ተነስቼ የሰጠሁት አስተያየት ተሳታፊዎቹ መቀለ ና ወልዋሎ ወደ ፕሪምየር ሊግ በማለፋቸው በክልሉ ያለው የስፖርት መነቃቃት እንዲታዘቡና የትግራይ ስቴድዬም እንዲጎበኙ በማሰብ ነበር፡፡ 

“መቀለ የቆነጃጅት ሀገር መሆንዋን ለመግለፅ ፈልጌ በሌላ መልኩ ስለተተረጎመ እና እኔው ራሴ በፈጠርኩት ኣላስፈላጊ ነገር የትግራይ ክልል ሴቶች በተለይም የመቀለ ሴቶችን በይፋ ይቅርታ እጠይቃለሁ::” ብለዋል፡፡ [በማትያስ ኃይለማርያም]


ድቻ እና አርባምንጭ 

ወላይታ ድቻ እና አርባምንጭ ከተማ በክረምቱ ካስፈረሙዋቸው ሁለት የውጭ ተጫዋቾች ጋር  ተለያይተዋል፡፡ 

ወላይታ ድቻ ክለቡ በክረምቱ ካስፈረማቸው 4 የውጭ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ናይጄሪያዊው አማካይ ሂላሪ ኢኬና ጋር ተለያይቷል፡፡ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው ተጫዋቹን የተጫዋቹን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቪድዮ ተመልክተው በአንድ አመት የውል ኮንትራት እና 4500 ዶላር ወርሀዊ ክፍያ ለማስፈረም ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በልምምድ ወቅት አጥጋቢ እንቅስቃሴ ባለማሳየቱ እንደተለያየ ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ አርባምንጭ ከተማ ካስመጣቸው 3 ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ጋናዊው አጥቂ ሰይዱ ባንሴ ጋር ተለያይቷል፡፡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ተጫዋቹ ወደ ሀገር ውስጥ የመጣ ቢሆንም አስቀድሞ የተጎተቱ የተጫዋቹ ጉዳዮች በክለቡ የዝግጅት እና የቅድመ ውድድር ወቅት አብሮ ያልነበረ ከመሆኑም ባለፈ ጉዳት እንዳለበት ከመግለፁ ጋር ተደማምሮ ለመለያየት እንዳበቃቸው ተገልጿል፡፡

ከውጪ የሚመጡ ተጫዋቾች አንድም ጨዋታ ሳያደርጉ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ አዳማ ከተማ ከደቡብ ሱዳናዊው ፒተር ዱስማን ጋር መለያየቱ ሲነገር ጅማ አባ ጅፋር አስመጥቶት የነበረው ናይጄርያዊ ግብ ጠባቂ በሀገሩ ኮንትራቱን ሳያጠናቅቅ መምጣቱ በመረጋገጡ ወደ ሀገሩ መመለሱ ይታወሳል፡፡ [በቴዎድሮስ ታከለ]ቅሬታ

እሁድ እለት የተደረገው የሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ላይ ሲዳማ ቡና በመጀመርያ 11 ላይ 4 የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን መጠቀሙን ተከትሎ አርባምንጭ ” የፌዴሬሽኑ ህግ በአንድ ጨዋታ ላይ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት 3 ተጫዋቾች ብቻ ናቸው” በሚል ቅሬታ አቅርበው የነበረ ቢሆንም በተሻሻለው የፌዴሬሽኑ ደንብ መሰረት 5 የውጪ ተጫዋቾች በአንድ ጨዋታ መሰለፍ እንደሚችሉ በመግለፅ ቅሬታው ውድቅ ተደርጓል፡፡ [በዳንኤል መስፍን]


ከ17 አመት በታች ሴቾች 

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከናይጄርያ ጋር ለሚያደርገው የአለም ዋንጫ ማጣርያ ነገ ዝግጅት እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ አሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ በቅድሚያ ከጠሯቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን የጠሩ ሲሆን ነገ 04:00 በአአ ስታድየም ልምምድ ይጀምራሉ ተብሏል፡፡ [በዳንኤል መስፍን]


አክሊሉ አያናው 

የአክሊሉ አያናው ጉዳይ እስካሁን እልባት አላገኘም፡፡ ተጫዋቹ ለሁለት ክለብ ፈርሟል በሚል ለፋሲል ከተማ 600ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኖበት የነበረ ቢሆንም ባቀረበው ይግባኝ ቅጣቱ ወደ 20ሺህ ብር ቀሎለት ለኢትዮጵያ ቡና እንዲጫወት ተወስኖ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ደግሞ ጉዳዩ በስራ አስፈፃሚ ውሳኔ እንደገና እንዲታይ ተወስኖ እስካሁን እልባት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ተጫዋቹም በቀጣይ ሳምንሃት ጨዋታዎች የማድረጉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ [በዳንኤል መስፍን]መሰረት ማኒ 

በ2008 ድሬዳዋ ከተማን በመምራት በታሪክ ብቸኛዋ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሴት አሰልጣኝ ለመሆን የበቃችው አሰልጣእ መሰረት ማኒ በግል ህይወቷ ዙርያ መፅሀፍ ልታሳትም ነው፡፡ አሰልጣኝ መሰረት ግለ ታሪኳን ራሷ ያዘጋጀችው ሲሆን በቅርቡ ታትሞ ለገበያ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

የእግርኳስ ሰዎች ግለ ታሪክ በኢትዮጵያ እምብዛም ባይለመድም በቅርብ አመታት አሸናፊ ግርማ እና አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው መፅሀፍ ማሳተማቸው የሚታወስ ነው፡፡ [በዳንኤል መስፍን]ከፍተኛ ሊግ 

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አስቀድሞ ከወጣለት መርሀ ግብር በሁለት ሳምንት ተገፍቶ ህዳር 9 እንዲጀመር መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ክለቦች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ከፍለው ባለማጠናቀቃቸው ውድድሩ በድጋሚ ሊራዘም እንደሚችል ተሰምቷል፡፡ አሁን ባገኘነው መረጃ መሰረት ደግሞ በርካታ ክለቦች ገንዘብ ከፍለው ያላጠናቀቁ በመሆኑ ውድድሩ በከፈሉት መካከል ብቻ ሊደረግ እንደሚችል ታውቋል፡፡ [በዳንኤል መስፍን]ሰናይ ተግባር

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ” ደማችንን ለወገናችን ” በሚል መርህ ትላንት በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተገኝተው የደም ልገሳ አከናውነዋል፡፡ የክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ እንዳስታወቀውም ከ850 በላይ ደጋፊዎች ደም በመለገስ የማህበሩን ሪኮርድ ሰብሯል፡፡ ከዚህ ቀደም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የደም ልገሳ ላይ መሳተፋቸው የሚታወስ ነው፡፡ድጋፍ 

በሀገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ለቀድሞ ክለቦቻቸው ድጋፍ የማድረግ ልማድ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ በቅርቡ አስቻለው ታመነ ለዲላ ከተማ የወንድ እና የሴት ቡድኖች የትጥቅ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ሌሎች ተጫዋቾችም የትጥቅ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ የሆነው ለዐለም ብርሀኑ ከቀድሞ የእግርኳስ ተጫዋች ግሩም ባሻዬ እና በጀርመን ዝቅተኛ ዲቪዝዮን እየተጫወተ የሚገኘው ወንድሙ አማኑኤል ባሻዬ ጋር በጋራ ለደቡብ ፖሊስ ስፖርት ክለብ ቡድኑ በውድድር አመቱ የሚጠቀምበት ማልያ እና የልምምድ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በዘንድሮው ክረምት አዲስ አበባ ከተማን የተቀላቀለው ግብ ጠባቂው ሀብቶም ቢሰጠኝ ሌላው ለቀድሞ ክለቡ ድጋፍ ያደረገ ተጫዋች ነው፡፡ ሀብቶም ለቀድሞ ክለቡ ሽረ እንዳስላሴ የማልያ ድጋፍ አድርጓል፡፡ [በቴዎድሮስ ታከለ እና አምሀ ተስፋዬ]የአማራ ዋንጫ 

የአማራ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሚያዘጋጀው የአማራ ዋንጫ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
ከጥቅምት 5 ጀምሮ በደብረ ማርቆስ ከተማ ሲደረግ የነበረው ውድድር ለ11 ክለቦች ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበረ ቢሆንም የጁ ፍሬ ወልድያ፣ ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን፣ ዳሞት ከተማ፣ መርሳ ከተማ እና ላስታ ላሊበላ ጥሪውን ባለመቀበላቸው  በውድድሩ ያልተሳተፉ ክለቦች ናቸው፡፡
ጎጃም ደብረ ማርቆስ፣ አዊ እምፒልታቅ፣ አማራ ፖሊስ፣ ደባርቅ ከተማ፣ ዳባት ከተማ እና አምባ ጊዮርጊስ የተሳተፉበት ውድድር ቅዳሜ ፍፃሜውን ሲያገኝ አማራ ፖሊስ እና አምባ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ በአማራ ፖሊስ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አምባ ጊዮርጊስ ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ያሉትን አራት ጨዋታዎች በማሸነፉ በ12 ነጥብ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ አዊ እምፒልታቅ ከደባርቅ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአዊ 1-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን አዊዎች ሁለተኛ ደረጃን ያዘው ማጠናቀቃቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ዳባት ከተማን 2-1 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ [በሚካኤል ለገሰ]


ቀጣይ መርሀ ግብር

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – 3ኛ ሳምንት 

ቅዳሜ ህዳር 9 ቀን 2010

09:00 ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ሲዳማ ቡና (አዲግራት)

09:00 ወልዲያ ከ ድሬዳዋ ከተማ (ወልዲያ)

11:30 ኢትዮጵያ ቡና ከ መከላከያ (አአ)


እሁድ ህዳር 10 ቀን 2010

09:00 አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (አርባምንጭ)

09:00 ጅማ አባ ጅፋር ከ ፋሲል ከተማ (ጅማ)

09:00 ደደቢት ከ ሀዋሳ ከተማ (አአ)

09:00 ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ (ሶዶ)

11:30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቀለ ከተማ (አአ)


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *