​አንዳንድ ነጥቦች በአዳማ ከተማ እና በደደቢት ጨዋታ ዙሪያ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት በተለያዩ የክልል ከተሞች ተደርገዋል። ተጠባቂ ከነበሩ ጨዋታዎች መካከልም አምና ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት አዳማ ከተማ እና ደደቢትን አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ያገናኘው ጨዋታ ይገኝበታል። ጥሩ ፉክክር በታየበት እና ያለግብ በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ላይ ከነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በመነሳትም የሚከተሉትን ነጥቦች ለማንሳት ወደድን።

ደደቢት 4-4-2 Vs. 4-2-3-1

አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ አምና በተጫዋች ስብስብ ጥልቀት እምብዛም ያልነበረው ወልድያን ይዘው በሊጉ እንዲቆይ ማስቻላቸው የሚታወስ ነው።  በአመቱ የሊግ ጉዞው ጥቂት ተጫዋቾችን የተጠቀመውና 7ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ይህ ቡድን በዋነኝነት በጠንካራ የመከላከል መሠረት ላይ የተገነባ እና በአንጋፋው አጥቂ አንዷለም ንጉሴ ጎሎች ላይ የተመረኮዘ ነበር። በዚህም ወልድያ  ዝቅተኛ ግብ ካስተናገዱ ሶስት ክለቦች መሀል አንዱ መሆን ሲችል በአመቱ ካስቆጠራቸው 18 ግቦች መሀከልም አስሩን ያገኘው ከአንዷለም ንጉሴ ነበር።

አሰልጣኙ ዘንድሮ የያዙት ደደቢትም በስብስብ ጥልቀት ረገድ ከአምናው ክለባቸው ጋር ከመመሳሰሉ ባሻገር የቡድኑ ዋነኛ የግብ ምንጭም ጌታነህ ከበደ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት አሰልጣኙ በ2009 የውድድር ዐመት በወልድያ ከገነቡት ቡድን ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ቡድን በደደቢት ሊያሳዩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።
የደደቢት የሊጉ አጀማመርም ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ነበር። በድቻው ጨዋታ በ4-4-2 ቅርፅ ከፊት ጌታነህ እና ኤቤል ያለውን ያጣመረው ደደቢት ግብ ሳያስተናግድ ከመውጣቱ ባሻገር ከሞከራቸው ሙከራዎች አብዛኞቹ የተገኙት ከጌታነህ ከበደ ነበር። ሆኖም በፊትም ይታማ የነበረው የአማካይ ክፍል በድቻ የቁጥር ብልጫ ተወስዶበት ሁለቱ አጥቂዎች ከፊት ለብቻቸው ተነጥለው የሚታዩበት አጋጣሚ በርካታ ነበር። በትላንቱ የአዳማ ጨዋታ ግን ደደቢት የጌታነህን ወደ ብሔራዊ ቡድን ማምራት ተከትሎ ከፊት አቤል ያለውን በብቸኛ አጥቂነት በመጠቀም እና የአማካይ ክፍሉን ቁጥር ከፍ በማድረግ ወደ 4-2-3-1 አሰላለፍ መጥቷል። ከመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች በኋላም መሀል ላይ የተሻለ የኳስ ብልጫ ያገኘባቸው አጋጣሚዎች ከመኖራቸውም ባለፈ ቡድኑ በጥሩ የጨዋታ ፍሰት እስከተጋጣሚው ሳጥን ድረስ በመድረሱ በኩል ከመጀመሪያው ጨዋታ የተሻለ ሆኖ ታይቷል። ይህ ሁኔታ ምናልባት ከጌታነህ መመለስ በኃላም በተመሳሳይ አጨዋወት ይቀጥላል ወይስ የቡድኑ የመጀመሪያ ዕቅድ ወደሚመስለው 4-4-2 ይመለሳል የሚል ጥያቄን ያስነሳ ሆኖ አልፏል።

የሙጂብ ቃሲም ጉዳይ

አዳማ ከተማ አምና በሶስተኝነት ሊጉን ሲያጠናቅቅ  በተከላካይ መስመር እና በፊት አጥቂነት ሚናዎች ያገለገለው የሙጂብ ቃሲም አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነበር። ሙጂብ አምና በአምስት ግቦች ከሌላኛው የቡድኑ አጥቂ ዳዋ ሁቴሳ ጋር የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ መጨረሱ የሚታወስ ነው። አዳማ ትላንት ደደቢትን ባስተናገደበት ጨዋታም ከአራት አማካዮች ፊት በብቸኛ አጥቂነት ተሰልፎ ሙሉ 90 ደቂቃውን ጨርሷል። የተጫዋቹ ፍጥነት እና ተክለሰውነት በተለይ ከኳስ ጋር በሚሆንበት አጋጣሚዎች ከፊት ለብቻው ከደደቢት የመሀል ተከላካዮች ደስታ ደሙ እና ካድር ኩሊባሊ ጋር እንዲፋለም አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነበር። ሆኖም ግን ከኳስ ውጪ የነበረው እንቅስቃሴ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ አልቀረም።

በጨዋታው 10ኛ እና 13ኛ ደቂቃዎች ላይ ሱራፌል ዳኛቸው እና በረከት ደስታ ባደረጓቸው ሙከራዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበረው ሙጂብ በጨዋታው አብዛኞቹ ደቂቃዎች ላይ ግን ወደ ደደቢት የመሀል ተከላካዮች የተጠጋ አቋቋምን ይዞ ተመልክተነዋል። ተጫዋቹ በእንቅስቃሴ ወደ አማካይ ክፍሉ በመሳብ እንዲሁም የጎንዮች ሩጫዎችን በማድረግ በተለይ ከመስመር ለሚነሱት ሁለቱ አማካዮች እና በቴክኒክ ብቃታቸው ከፍ ላሉት ከንአን ማርክነህ እና ሱራፌል ዳኛቸው በተከላካዮች መሀል እንዲገቡ ክፍተትን በመፍጠሩ በኩል ደክሞ ታይቷል። ይህም በመሆኑ አብዛኞቹ የቡድኑ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች የሞከሯቸው ሙከራዎች ከሳጥን ውጪ የተገኙ ነበሩ።  ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በሙጂብ ዙሪያ ጥያቄ ያነሳንላቸው አሰልጣኝ ተገኔ ሌሎች አጥቂዎቻቸው ጉዳት ላይ በመሆናቸው እና ዳዋ ሆቴሳም ለብሔራዊ ቡድን በመጠራቱ ሙጂብ ካለው ልምድ አኳያ በአጥቂነት እንደተጠቀሙበት ነግረውናል።

የአዳማ ከተማ የተከላካይ መስመር
በተለምዶው ግቦች ባልተቆጠሩባቸው አጋጣሚዎች የቡድኖች የተከላካይ መስመር ምስጋናውን ይወስዳል። በተለይ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ባለቤት የሆነው አዳማ ከተማ በሜዳው ላይ በቀላሉ ግብ የሚቆጠርበት አለመሆኑ በተከታታይ አመታት ላስመዘገበው ውጤት የነበረው አስተዋፅኦም እጅግ ከፍተኛ ነበር። የመሀል ተከላካዮቹ ተስፋዬ በቀለ እና ምኞት ደበበ በልምድም ሆነ አብሮ ብዙ በመጫወት ከሊጉ ሌሎች ተመሳሳይ ሚና ካላቸው ተጨዋቾች ጋር ሲነፃፀር በጥንካሬው የሚነሳ ጥምረት አላቸው። ሆኖም የትላንትናው የቡድኑ የኃላ ክፍል የመከላከል ብቃት ግን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነበር።

ምንአልባት በተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ የብሩክ ቃልቦሬ ክለቡን መልቀቅ እና የደሳለኝ ደባሽ አለመኖርን ተከትሎ ቡድኑ አዲስ ህንፃን መጠቀሙ ይበልጥ ያጋለጠው ቢመስልም የአዳማዎች የተከላካይ መስመር ተደጋጋሚ ስህተቶችን ሲሰራ ተስተውሏል። በጨዋታው ከኳስ ጋር ባለ አንድ የተጋጣሚ ተጨዋች ላይ ተደራርቦ በመሄድ በሌላኛው የሜዳ ክፍል ላይ ለሚገኝ ተጨዋች ሰፊ ክፍተት ሲተው የታዩት የአዳማ ተከላካዮች የደደቢት ተጨዋቾች ደካማ አጨራረስ እንደታደጋቸው ማሰብ ይቻላል። በተለይ 31ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ የመስመር አማካይ አቤል እንዳለ በቁጥር ተበራክተው የመጡትን የአዳማ ተከላካዮች አታሎ በማለፍ በግራ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ነፃ ለነበረው ሽመክት ያሳለፈለት እና ሽመክት ያመከነው ኳስ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነበር። ይህ የተከላካይ ክፍሉ የመናበብ ችግር በጊዜ ተቀርፎ ወደ ቀደመ ጥንካሬው ካልተመለሰ ግን ቡድኑ በሊጉ ጉዞው ላይ ሊቸገር እንደሚችል ከወዲሁ መጠቆም ይቻላል።

ደደቢት በተጋጣሚ ሳጥን ዙሪያ

አቤል እንዳለ እና ያብስራ ተስፋዬን በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ይዞ የገባው የደደቢት የአማካይ ክፍል ከፋሲካ አስፋው ፣ አስራት መገርሳ እና ሽመክት ጉግሳ ልምድ ጋር ተዳምሮ የተሻለ ውህደት ታይቶበታል። ከኳስ ቁጥጥሩ ባለፈም የአዳማዎችን ደካማ የመከላከል ሽግግርን ተከትሎ የፊት አጥቂው አቤል ያለው እና የአጥቂ አማካዮቹ ከጃኮ ፔንዜ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል አቅራቢያ ኳስ ይዘው እና በቁጥር ተበራክተው የገቡበት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ሆኖም በአንዳንድ አጋጣሚዎች የተሻለ አቋቋም ላይ ላለ ተጫዋች ሊያሳልፉ የሚገባቸውን ኳሶች ወደግብ ሲሞክሩ በሌላ ጊዚያት ደግሞ ጥሩ ቦታን ይዘው ሳለ ነገር ግን ችኮላ የተሞላበት ውሳኔ በማሳለፍ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተመልከተናል።
ምንአልባት ጌታነህ በጨዋታው ላይ ቢኖር በእነዚህ አጋጣሚዎች የተገኙት ኳሶች ወደ እርሱ እንዲደርሱ መደረጉ የማይቀር ነበር። በወላይታ ድቻው የመጀመሪያ የክለቡ የሊግ ጨዋታ ላይም ይህን ማስተዋል ችለናል። ጌታነህ ባልተሰለፈበት በዚህ ጨዋታ ላይ ግን ቡድኑ ከወገብ በላይ የያዛቸው ተጨዋቾች ከግቡ አቅራቢያ በሚወስኗቸው ውሳኔዎች ላይ ያላቸው በራስ መተማመን በጥርጣሬ የሚታይ ነው። ጌታነህ ዘንድሮ አምና በነበረበት የብቃት ደረጃ ላይ የማይገኝ ከሆነም ደደቢት ግቦችን የሚያገኝበት ሁለተኛ አማራጭ እንዲኖረው በአማካይ ክፍሉ የተቃራኒ ቡድን ሳጥን አካባቢ ውሳኔዎች ላይ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *