​ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ የውድድር አመቱን በድል ጀምሯል

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ አመቱን በድል ጀምሯል፡፡

ጨዋታው ይጀመራል ተብሎ መርሀ ግብር የወጣለት 10:00 የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል የቀኑ ጊዜ አጥሮ ምሽቱ የሚረዝምበት በመሆኑ ከእረፍት መልስ በሚኖረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሜዳው ሊጨልም ስለሚችል ይህን ከግምት በማስገባት ጨዋታው በ30 ደቂቃ ቀደም ብሎ 09:30 ሊጀምር ችሏል። ሆኖም የሰአት ለውጡን ካለማወቅ ጋር በተያያዘ በስታድየሙ የተመልካች ቁጥር እየጨመረ የመጣው ጨዋታው ከጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ሲሆን ቀድሞ የነበረው የስታዲየም መግቢያ ዋጋ ዘንድሮ በእጥፍ መጨመሩም የስፖርት ቤተሰቡን ቅር እንዳሰኘ ታዝበናል፡፡

ከ1968 የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የድሬዳዋ ስታዲየምን በማስፋፊያ ግንባታ የተመልካች ቁጥሩን ለመጨመር በማሰብ ረጅም አመት አገልግሎት የሰጠው የካታንጋ ክፍል ሙሉ ለሙሉ የፈረሰ ሲሆን ወደ ፊት ከላይኛው የካታንጋ ክፍል ጋር የሚገናኝ ክፍል አዲስ ሊሰራ እንደሚችል ሰምተናል። ከዚህ ቀደም ባዶ ስፍራ የነበረው በተለምዶ አጠራር ከማን አንሼ በሚባለው ስፍራም አዲስ የስቴድየም ክፍል አግኝቷል።

ለረጅም አመት በዳኝነት እንዲሁም በጨዋታ ኮሚሽነርነት ያገለገሉትና ዛሬ ስርአተ ቀብራቸው የተፈፀመው አቶ ለማ ግዛውን በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማሰብ በተጀመረው ጨዋታ ጅማ አባጅፋር በሊጉ ባሳለፍነው ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታውን ሀዋሳ ከተማን 2-0 አሸንፎ በመምጣት በጥሩ ስነ ልቦና ወደ ሜዳ ሲገባ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ በመተላለፉ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

ከጅማሬው አንስቶ እልህ የተቀላቀለበት እና ጉሽሚያ የዛበት ይህ ጨዋታ ለኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰም ፈተና ሆኖበት ውሏል፡፡

እንዳለ ደባልቄ ጨዋታው በጀመረ ገና በ3ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ የሳምሶን አሰፋን አቋቋም አይቶ በጥሩ ሁኔታ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ የመለሰበት አጋጣሚ የሚያስቆጭ የጎል እድል ሆኖ አልፏል። እስከ 7ኛው ደቂቃ ድረስም እንግዶቹ ጅማ አባጅፋር ወደ ጎል በመድረስ ከድሬደዋ ከተማ የተሻሉ የነበረ ሲሆን በ7 ደቂቃ ውስጥ 5 የማዕዘን ምት ማግኘት ችለው ነበር።

8ኛው ደቂቃ ላይ ዘነበ ከበደ ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ያሻገረውን እና ሀብታሙ ወልዴ በአግባቡ ሳይጠቀምበት የተቆረጠውን ኳስ በግራ መስመር ሳጥን ውስጥ ብቻውን የነበረው አህመድ ረሺድ ተቆጣጥሮ አገባው ሲባል ወደላይ የሰደደው ኳስ ለድሬዎች የመጀመርያ ሙከራ ነበር። ይህ ኳስ በተሳተበት ቅፅበት የድሬዳዋ ተከላካዮችን ትኩረት ማጣት ተከትሎ ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ በፍጥነት ኳሱን በመልስ ምት ጨዋታውን አስጀምሮ ለናይጄርያዊው አጥቂው ኦኪኪ አፎላቢ የሰጠውን ኳስ ብቻውን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ጎል ሊሆን የሚችለውን አጋጣሚ ሳምሶን አሰፋ እንደምንም ያዳነበት አጋጣሚ ጅማ አባጅፋርን በጨዋታው መሪ ልታደርግ የምትችል ነበረች።

ጨዋታው አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ ሲቀጥል አልፎ አልፎ በሁለቱም በኩል ወደ የጎል እድል የመፍጠር አጋጣሚ ይታይ ነበር። በተለይ የቀኝ መስመር የሜዳ ክፍል ለማጥቃት እና የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ሲጠቀሙበት ተስተውሏል። ባለሜዳዎቹ ድሬዎች በሱራፌል ዳንኤል እና በዘነበ ከበደ አማካኝነት ጫና ሲፈጥሩ አባ ጅፋሮች በተለይ ፈጣን እና ጉልበተኛ የሆነው እንዳለ ደባልቄን በመጠቀም አህመድ ረሺድን ሲረብሸው ተመልክተናል። 27ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳንኤል የግብ ጠባቂውን ዳንኤል አጄን ከግብ ክልሉ መውጣቱን ተከትሎ ወደ ግብ የመታው ኳስ ቢኒያም ሲራጅ እንደምንም ሲያወጣው እንግዶቹ አባ ጅፋሮች በ30 ኛው ደቂቃ ኄኖክ ኢሳይያስ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ወደ ጎል በግንባሩ ቢገጨውም ለጥቂት ወጥቶበታል።

41ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሺድ በእንዳለ ደባልቄ ጥፋት ተሰርቶበት ዳኛው ጥፋቱን አስቁመው ለድሬዳዋ ቅጣት ምት ሲሰጡ  አህመድ  ከቅጣት ምቱ በተጨማሪ የማስጠንቀቂያ ካርድ ሊሰጡ ይገባል በማለት ተቃውሞውን ዳኛው ፊት ኳስን በማንጠር በመግለፁ በሁለት ቢጫ (ቀይ ካርድ) ከሜዳ ተወግዷል። ይህም ቀይ ካርድ በኢትዮዽያ ፕሪሚምየር ሊግ የ2010 የውድድር አመት የመጀመርያው ቀይ ካርድ ሆኖ ተመዝግቧል።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የግራ መስመር የተከላካይ ስፍራው ቦታ ክፍተት እንዳይኖረው በማሰብ ወሰኑ ማዜን በዘላለም ኢሳያስ ቀይረው አስገብተዋል ። የመጀመርያው አጋማሽም ምንም ጎል ሳይስተናገድበት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ገና በ47ኛው ደቂቃ ላይ ወሰኑ ማዜ ከግራ መሰመር ባሻገረው እና ሀብታሙ ወልዴ በግንባሩ መትቶ ለጥቂት በቋሚው ስር በወጣበት ሙከራ ተጋግሎ የጀመረ ሲሆን 51ኛው ደቂቃ ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዘነበ ከበደ ሲያሻግርለት በዘንድሮ አመት ድሬዎችን የተቀላቀለው ጋናዊ አጥቂ ከዋሜ አትራም በግንባሩ ገጭቶ ጎል በማስቆጠር ድሬዳዋን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

60ኛው ላይ እንዳለ ደባልቄ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ በግንባሩ በመምታት ጎል አስቆጥሮ ደስታውን እየገለፀ ባለበት ወቅት ኢ/ዳኛ በላይ ታደሰ አስቀድሞ የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ነው የሚል ምልክት ሰጥተዋል በሚል ጎሉን ሊሽሩት ችለዋል። የዳኛው ውሳኔ ያልተወጠላቸው ጅማዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተቋሟቸውን ሲያሰሙ ተመልክተናል። ከዚህ በኋላ በነበረው ቀሪ 30 ደቂቃ የአቻነት ጎል ፍለጋ አባጅፋሮች ጫና ቢፈጥሩም በመከላከል ጠንካራ የነበረውን የድሬደዋን የኃላ ክፍል ሰብረው ጎል ለማስቆጠር ተቸግረው ታይተዋል። ቢሆንም ግን እንዳለ ደባልቄ እና ኦኪኪ አፎላቢ ሁለት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።

ባለሜዳዎቹ ድሬዎች የተወሰደባቸውን የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ከግምት በማስገባትና የአጥቂ ቁጥራቸውን በመቀነስ እና የተከላካይ ተጨዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት አጥብቀው የተከላከሉ ሲሆን አልፎ አልፎ በሚገኙ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው ጋናዊ አጥቂ ክዋሜ አትራም አማካኝነት ጫና ሲፈጥሩ ተመልክተናል።

እምብዛም የተሳካ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባልተመለከትንበት በሁለተኛው አጋማሽ በተጨዋቾች ለውጥ እና ድሬዳዋዎች ውጤት ለማስጠበቅ ሰአት ሲያባክኑም አይተናል። እንዳለ ደባልቄም በተደጋጋሚ ግልፅ ጥፋት ተጨዋቾች ላይ እየሰራ ዳኛው በዝምታ ማለፋቸውን በመቃውም ከድሬዳዋ ተጨዋቾች በኩል ተቃውሞ ይቀርብባቸው ነበር። የጨዋታው ጭማሪ 6 ደቂቃዎች ደጋፊው በጭንቀት ቁጭ ብድግ እያለ የተመለከተባቸው ሲሆኑ ጅማ አባ ጅፋሮች በረጃጅም ኳስ ወደ ጎል ለመድረስ ቢሞክሩም አቻ መሆን ሳይችሉ ጨዋታው በድሬደዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ድሬደዋ ከተማ

” ጨዋታውን በሁለት መልክ ከፍሎ ማየት ይቻላል። በመጀመርያው አጋማሽ ጅማዎች ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። የእኛም ቡድን ወደ ጨዋታው ለመግባት ትንሽ ተቸግሮ ነበር። ምክንያቱም ገና የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታችን በመሆኑ። ሆኖም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ገብተን ባለንበት ሰአት ተጫዋች በቀይ ካርድ ወጣብን። ከእረፍት መልስ በቁጥር ብናንስም በእንቅስቃሴ የተሻልን ነበርን። ጎል ማስቆጠራችን ብቻ ሳይሆን ባሉንም ልጆች ጨዋታውን ተቆጣጥረን አሸንፈን ወተናል። ”

አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር 

” መጥፎ ጨዋታ ነበር። ተጫወትን ሳይሆን ገብተን ወጣን ነው የሚባለው። ብዙ ክፍተቶች ነበሩ። ጨዋታው አስደሳች አልነበረም። እግርኳስ እንዲህ ከሆነ ጥሩ አይደለም። አንድ ዳኛ አምኖበት ቀይ ካርድ ከሰጠ ለምንድነው ለማካካስ እያለ ሌላ ስህተት የሚሰራው? ወይ ቀይ ካርዱን አለመስጠት ነው ከሰጠ ደግሞ እኛ ላይ ጫና መፍጠር አልነበረበትም፡፡ የመጫወት ፍላጎታችንን አጥፍቶታል። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *