ሪፖርት | በ10 አመት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደው የትግራይ ደርቢ ያለ ግብ ተጠናቋል

መቐለ ላይ ሁለቱን አዲስ አዳጊ ክለቦች መቐለ ከተማን እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ያገናኘው የሁለተኛ ሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በ2000 የውድድር አመት ጉና ንግድ ከወረደ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በሁለት የትግራይ ክለቦች መካከል የተደረገው ጨዋታ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው እና ደማቅ የደጋፊ ድባብ የታየበት ሲሆን ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በቅርቡ ህይወታቸው ላለፈው የወልዋሎ ዓ.ዩ ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገ/ፃዲቅ እና ለኮምሽነር ለማ ግዛው የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

የጨዋታው የመጀመሪያ የጨዋታ አጋማሽ አመርቂ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያልታየበት ነበር፡፡ መቐለ ከተማዋች በረጃጅም በሚላኩ ኳሶች ላይ ተመርኩዘው የተንቀሳቀሱ ሲሆን በተቃራነው ወልዋሎዎች መሀል ሜዳ ላይ በቁጥር በመብዛት እና በመስመር በኩል በተለይ በአዲስ ፈራሚው በፕሪንስ አቅጣጫ የመቐለን ተከላካይ ለመፈተን ሞክረዋል፡፡ 4ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ የማድረግ  ቀዳሚነትን የወሰዱት መቐለ ከተማዋች ሲሆኑ ይኸውም መድህኔ ታደሰ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት አማኑኤል ገ/ሚካኢል በቀጥታ መትቶ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው በረከት አማረ ባዳነበት አጋጣሚ ነበር።

የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ በሌላ አጋጣሚ ባገኙት ዕድል ሚካኤል ደስታ በሁለት ተጨዋቾች መሀል አሳልፎ ያሻገረውን ኳስ አጥቂው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከግብ ጠባቂው በረከት አማረ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በድጋሚ 31ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ገ/ክርስቶስ አክርሮ የመታውን ኳስ የወልዋሎው ግብ ጠባቅ በረከት አማረ መሬት ለመሬት ተሸራንቶ እንደምንም ሊያድንበት ችሏል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ሲቀረው አማኑኤል ገ/ሚካኤል  የወልዋሎን ሁለት ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ አሁንም በረከት አማረ አድኖበታል።

በወልዋሎ በኩል የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ በ10ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ በመቐለ ተጨዋቾች የቅብብል ስህተት የተገኘውን ይህን አጋጣሚ ኤፍሬም ጌታቸው አግኝቶ ወደግብ ሳይቀይረው ቀርቷል፡፡ 38ኛው ደቂቃ ላይ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ማግባት ሙከራ በአብዱራማን ፉሴይኒ አማካይነት ያደረጉት ወልዋሎዎች ፊሊፕ ኢቮና  በቀላሉ አድኖባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ተጠናቆ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ውጤት ይዞ ለመውጣት ተጭነው ሲጫወቱ በነበሩት መቐለ ከተማዋች በኩል በ46ኛው ደቂቃ በግራ ክንፍ የተገኘውን ቅጣት ምት ቢስማርክ አባሜንግ አክርሮ ሲመታ እና የግብ አግዳሚ ሲመልስበት አማኑኤል ገ/ሚካኤል ያገኘውን ነፃ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በተመሳሳይ በ68ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ከበድ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጭ የሞከረውም ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል፡፡ በሌላ የመቐለዎች ሙከራ 75ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ከበደ ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ይለውጠዋል ተብሎ ቢጠበቅም የወልዋሎ ግብ ጠባቂ በረከት አማረ አድኖበታል፡፡ የጨዋታው መጋባደጃ ላይም እንዲሁ ቢስማርክ አባሜንግ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ በረከት አማረ ሲተፋው በነፃ አቆቆም ላይ የነበረው ዱላ ሙላቱ በማይታመን መልኩ ስቶታል፡፡

ከዕረፍት መልስ ወልዋሎዎች መሀል ሜዳ ላይ የተወሰዳባቸውን ብልጫ ለማስመለስ በሚመስል መልኩ ብሩክ አየለን አስወጥተው መኩሪያ ደሱን ወደ ሜዳ አስገብተዋል። በሙከራ ረገድ 65ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተሻማውን ኳስ ሙሉዓለም አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረ ሲሆን በጨዋታ እንቅስቃሴም ቡድኑ የመሀል አማካዮቹን ወደ ኃላ በመሰብ ለተጋጣሚ ክፍተት ላለመስጠት ሲሞክር ተስተውሏል። ወልዋሎዎች ከሜዳቸው ውጪ ላሳኩት ወሳኝ ነጥብም የግብ ጠባቂው በረከት አማረ ድንቅ ብቃት በዋነኝነት ተጠቃሽ ነበር።

በጨዋታው ወልዋሎዎች በተደጋጋሚ በመውደቅ የጨዋታውን ሰዓት ለማበክን መሞከራቸውን ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ የነበሩት ዳዊት አሳምነው በተደጋጋሚ የወልዋሎ ተጫዋቾችን ሲያስጠነቅቁ ታይተዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ 

” ከአስተያያቴ  በፊት የሁለቱንም ክለብ ደጋፊዋች ላመሰግን እወዳለው፡፡ በጨዋታው የተሻልን ነበርን። በጨዋታው ያገኘናቸውን የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ሳንጠቀምበት ቀርተናል። በመጨረስ በኩል ትንሽ ይቅርናል። ብዙ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገን ስላልመጣን እንደዚህ አይነት ክፍተት ይፈጠራል። ጥሩ የተጫወትን ይመስለናል  ፤ ህዝቡ ግን ጎል አለማየቱ ያሳዝነናል። ሆኖም ከጎል ውጭ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገናል፡፡”

አሰልጣኝ ብርሃኔ ገ/እግዚአብሔር – ወልዋሎ ዓ.ዩ

“በመጀመሪያ ትልቅ እድገት አይተናል። ከዚህ በፊት ኳስ ያለ ተመልካች እናይ ነበር። ይህ ስቴድየም ዛሬ ሞልቶ ማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል። ወደ ጨዋታው ስንገባ በእንቅስቃሴ በኩል ተመጣጣኝ ነበርን። የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል እነሱ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ።  በአጠቃላይ ከሜዳችን ውጭ ነጥብ ይዘን በመመለሳችን ደስተኛ ነኝ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *