የአሰልጣኞች ገፅ፡ ቆይታ ከፋሲል ተካልኝ እና ዕድሉ ደረጄ ጋር (ክፍል አንድ)

ፋሲል ተካልኝ እና ዕድሉ ደረጄ በቅርቡ በውጭ ሀገር ተከታትለውት ስለመጡት ትምህርት እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረጉትን ቆይታ በዩቲዩብ ቻነላችን ላይ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ይህንን ቆይታ በፅሁፍ ማግኘት ለምትፈልጉ በሚከተለው መልኩ አዘጋጅተዋል፡፡ 


ቃለ-ምልልሱን በቪድዮ ለመመልከት፡ YOUTUBE


ከአሰልጣኝነት ትምህርት ጋር በሚገናኝ በሃንጋሪ እና ስፔን የነበራችሁ ቆይታ ምን ይመስል ነበር? ተመክሮዎቻችሁን እንቃኝ…

ፋሲል ተካልኝ፦ ትምህርቱን ያገኘሁት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሰጠኝ እድል ነው፡፡ በሃንጋሪ በነበረኝ ቆይታ ትምህርቱ በሁለት መንገዶች የተከፋፈለ ነበር፡፡ አንደኛው <General Subject> ነው፡፡ ከስፖርቱ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ርዕሶች ላይ ያተኩራል፤ ከተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የተውጣጡ አሰልጣኞች ተሳትፈውበታል፤ ኮርሱን ሁላችንም ወስደነዋል፡፡ ሌላኛው ደግሞ <Sport Specialization> ነው፡፡ እኔ በዋነኝነት የሄድኩበት <Football Coaching>ን የሚመለከተው ክፍል የዚህኛው ዘርፍ ንዑስ ክፍል ነው፡፡ እግርኳስን ብቻ በሚያጠናው ይህኛው ኮርስ ረዘም ያለ ጊዜ ወስጄ ጥሩ ትምህርት አግኝቼበታለሁ፡፡ እንግዲህ በዚህ መንገድ ነው ተምሬ የመጣሁት፡፡

+ ከነበረህ ነገር ላይ ምን ጨመርክ?

★ ፋሲል ተካልኝ፦ ትምህርት ሰዎችን ያሻሽላል፤ ሰዎች ለውጥ እንዲኖራቸው ያደርጋል፤ ምንም ጥያቄ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ተጫዋቾች ከልጅነታቸው ጀምሮ በምን መልኩ እንደሚያዙ፣ በየጊዜው ተገቢ የሆነ ልምምድ እንዴት እንደሚሰጣቸው፣ በወጣቶች ላይ ትልቅ ትኩረት ለምን እንደሚኖር፣… በ<Senior Teams> ደግሞ አሰልጣኞች ተጫዋቾቻቸውን ስለሚያስተዳድሩበት መንገድ፣ የልምምድ አሰጣጥ ሥርዓትን፣ …እነዚህንና ሌሎችንም ተምሬያለሁ፡፡ ‘ይሆኑኛል፡፡’ ብዬ የማስባቸውን፣ ‘በሃገሬ እግርኳስ ላይ ስሰራ ይጠቅሙኛል፡፡’ የምላቸውን፣ ‘እኔንም ያሻሽሉኛል፡፡’ ያልኳቸውን ትምህርቶች ቀስሜያለሁ፡፡

★ ዕድሉ ደረጀ፦ እኔ ኮርሱን የወሰድኩት <ኢሙኒዢ> በሚባል የአሰልጣኞች ትምህርት ቤት ሲሆን ትምህርቱም በወጣቶች ላይ የሚያተኩር <Youth Soccer Expert Coarse> ነው፡፡ ኮርሱ ከስድስት ዓመት ጀምሮ እስከ አስራ ዘጠኝ ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ እና <Perfection Stage> ብለው የሚጠሩት ደረጃ ድረስ በእያንዳንዱ የእድሜ እርከኖች በተከፋፈሉ ምድቦች ማለትም ከ0-6፣ ከ6-13፣ ከ13-17 እና ከ17 ዓመት በላይ ደግሞ <High Performance Level> የሚሉትን ክፍሎች ያጠቃልላል፡፡ እኔ ከመጨረሻው እርከን ውጪ (High Performance Level) ያሉትን ሶስቱን በወጣቶች ደረጃ የሚሰጠውን <Adaptation>, <Youth Development> እና <Technic> ትምህርት ተምሬ ነው የመጣሁት፡፡ እነርሱ እድሜን ብቻ ሳይሆን ስልጠናውንም <Egocentric>, <Somatics> እና <Collective> በማለት ይከፋፍሏቸዋል፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ደግሞ የየራሳቸው ንዑሳን አርዕስቶችን አካተዋል፡፡ ተጫዋቾች ከመጀመሪያው እርከን ተነስተው እንደ ሆላንድ፣ ቤልጂየምና ጀርመን ባሉ ሃገራት <Perfection Stage> አልያም የላይኛው ደረጃ  ተብሎ ለሚጠራው እርከን እስከሚበቁ ድረስ ለልምምዶች እንዴት እቅድ እንደሚወጣ፣ የአንድን ተጫዋች የግል ብቃት አገማገም፣ የቡድን ጨዋታ ትንተናዎች አዘገጃጀትን የሚያሳይ… በአጠቃላይ አንድ መቶ ሰላሳ የሚጠጋ <Credit Hours> የወሰደና አንድ ወር የፈጀ የእግርኳስ ስልጠና ትምህርት ነበር፡፡

በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም አንጋፎቹ አሰልጣኞችም በሃንጋሪ፣ ቡልጋሪያ፣ ምስራቅና ምዕራብ ጀርመን ተምረዋል፡፡ የእናንተ ቆይታ ከቀደሙት አሰልጣኞች አንጻር ምን የተለየ ነገር ይኖረው ይሆን?

★ ፋሲል ተካልኝ፦ ይህን ለማነጻጸር እንኳ ይከብዳል፡፡ እኛ በእነርሱ ቦታ ሆነን አልተማርንም፤ እኔ በበኩሌ አንጋፎቹ ምን እንደተማሩ መረጃው የለኝም፡፡

+ በተጫዋችነት ዘመናችሁ ግን አብራችሁ ሰርታችኋል፡፡

★ ፋሲል ተካልኝ፦ በእርግጥ በተጫዋችነት ጊዜዬ ትልልቆቹን አሰልጣኞች አይቻለሁ፤ በአብዛኛው ሲኒየሮቹ አሰልጥነውኛል፡፡ ነገር ግን እኔ የተማርኩትን ከእነርሱ ጋር ለማነጻጸር የቀደሙት አሰልጣኞች የተማሩትን በትክክል ማወቅ አለብኝ ለማለት ነው፡፡ ጊዜው ረዘም ብሏል፤ በዚያ ላይ እግርኳስ በየጊዜው ይቀያየራል፡፡ <Dynamic> ባህርይ አለው፤ እየተሻሻሉ የሚመጡ ብዙ ነገሮች ይኖሩታል፡፡ ለማነጻጸር ቢከብድም እነርሱ ትልልቅ አሰልጣኞች ናቸው፤ የተማሩትንም ወደ እኛ ለማስተላለፍ ጥረዋል፡፡ በነገራችን ላይ እኛ በጣም እድለኞች ነን፤ እግርኳስን ልንማርበት እንዲሁም ራሳችንን የምናሻሽልባቸው ብዙ መንገዶች አሉን፡፡ እነርሱ ግን ጠባብ በሆነ እድል ውስጥ ሰርተዋል፤ በጣም ጠንካሮች ነበሩ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደተማርኩባቸውም እርግጠኛ ነኝ፡፡

 ★ ዕድሉ ደረጀ፦ እኔም ከፋሲል የተለየ ሃሳብ የለኝም፡፡ እግርኳስ ተለዋዋጭ በመሆኑ ታላላቆቹ አሰልጣኞች በዚያ ዘመን ያገኙትና እኛ ተምረን የመጣነው ሙሉ በሙሉ ይለያያል፡፡ ዘመኑን ስታስበውም የተራራቀ ነው፡፡ በእነርሱም ጊዜ የመማር እድሉን ያገኙት በጣም ጥቂቶች ነበሩ፡፡ በእኛም ጊዜ ያው ጥቂት ነን፡፡ በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ያሉ ሃገራት በ<High Level> ያላቸው የአሰልጣኞች ጥራትን ስታስበውና ከእኛ ሃገር ጋር ስታስተያየው የሆነ ወጥነት ያለው ነገር አይታይም፡፡ ወጥ የሆነ አሰራር ለማግኘት ወይ ኤክስፐርቶችን ወደ እዚህ ማምጣት አልያም አሰልጣኞችን በዛ አድርጎ ወደ ውጪ በመላክ ማስተማር ነው፡፡ አንጋፎቹ ብዙ ደክመዋል፤ ከምንም ተነስተው የሆነ ደረጃ ደርሰዋል፡፡

 ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም ነባሮቹ አሰልጣኞች ወደ ውጪ ወጥተው ተምረዋል፡፤ መሃለኞቹም እንዲሁ መጠነኛ እድል አግኝተዋል፤ እናንተም በጥረታችሁ እየወጣችሁ እየተማራችሁ ነው፡፡ በተገኘው የመማር አጋጣሚ ልክ ትምህርቱን ወደ ተግባር ቀይሮ ለውጥ ለማምጣት ያሉት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ትምህርቱን በተግባር ወደ ተጫዋቾች የማስረጽ የአሰልጣኞች ድክመት፣ የተጫዋቾች የመቀበል አቅም ችግር ወይስ ሌላ…

★ ፋሲል ተካልኝ፦ ችግሩን አንድ ቦታ ላይ ብቻ ማሳረፍ በጣም ያስቸግራል፡፡ ሁሉም ሰው ትምህርት ይማራል፤ በእግርኳሱ ብቻ ሳይሆን በሌላም ሙያ ይማራል፡፡ ነገር ግን ትምህርትን ተግባራዊ የማድረግ አቅም እንደየሰዉ ይለያያል፡፡ ተጫዋቾቹ ጋርም ያለው ተመሳሳይ ነው፡፡ እንደ ግል አቅማቸው አሰልጣኛቸው የሚያስተምራቸውን የመረዳት ልዩነት መኖሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እግርኳሱ እንዲያድግ አሰልጣኞች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ እንደሚታየው በሃገራችን ለፍቶ ራስን ማስተማር ካልተቻለ ብዙ እድሎች አይገኙም፤ እንደሚታወቀው የእያንዳንዱን አሰልጣኝ ብቃት ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ኮርሶች በሃገራችን የሉም፡፡ <Football Coaching>ን ብቻ የሚሰጡ ትምህርት ቤቶችም አልተመሰረቱም፡፡ ስለዚህ ያለው የመማር እድል እጅጉን ጠባብ ነው፡፡ እኔ ባገኘሁት የመማር አጋጣሚ ራሴን እድለኛ አድርጌ ላስብ እችላለሁ፤ ውጪ ሄጄ ‘ከእኛ የተለየ ነገር ያላቸው ምንድን ነው?፤ ለእኛስ ሃገር ተጫዋቾች ምን የሚጠቅም ነገር እቀስማለሁ? ካነበረኝ ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሻግረኝስ ምንድን ነው?’ የሚለውን ለማየት ችያለሁ፡፡ እድሉም እንደዚያው እድለኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎች መዓት አሰልጣኞች ግን ይህ ሁኔታ አልተፈጠረላቸውም፡፡ የአንዳንድ ሃገራትን ተመክሮዎች ብንቃኝ ሰባ፣ ሰማኒያና ከዚያም በላይ የሚሆኑ በርካታ አሰልጣኞቻቸውን ወደ ውጪ ልከው የሃገራቸውን እግርኳስ ለመለወጥ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ሁለት-ሶስት ሰው ሄዶ ስለተማረ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ትልቅ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ መሻሻሎችን ለማስመዝገብ ሁሉንም አሰልጣኞች ባለ እውቀት ማድረግ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

 ★ ዕድሉ ደረጀ፦ በአሰልጣኝነት ደረጃ ተጫዋቾችን ማብቃት እጅግ በጣም ወሳኝነት አለው፡፡ ከምንም በላይ በየትኛውም መስክ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊው ዘርፍ ብንሄድ ትውልድን ለማነጽ ጥርጊያው የሚጀመረው ከዩኒቨርሲቲዎች ነው፡፡ ልክ እንደዚያው በእግርኳሱም ተጫዋቾችን ሊቀርጹ የሚችሉት አሰልጣኞች ናቸው፡፡ መፍትሄው እነዚህን ብቁ አሰልጣኞች ማፍራቱ ላይ ነው፡፡ ያለፈው የአንጋፎቹ አሰልጣኞቻችን ተመክሮዎች ምናልባት ለዚህኛው ትውልድ ብዙ እገዛ ሊያደርግ ይችላል፡፡ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በፊት ከነበረው አንጻር ሰፊ ልዩነቶች ይኖሩታል፡፡ ፋሲሊቲዎችን ብናይ ድሮ አዲስ አበባ ብዙ ለእግርኳስ ተጫዋቾች የሚበቁ ሜዳዎች ነበሯት፡፡ አሁን ግን ህዝብ በዝቶ ሜዳ የለም፤ ባለፈው ዘመን ደግሞ ከነበረው ህዝብ አንጻር ተመጣጣኝ ሜዳዎች ነበሩ፡፡ አያሌ ጉዳዮችን ማንሳት ብንችልም እንደ መፍትሄ ወጥነት ያለውን ነገር በኤክስፐርቶች መጀመር አለብን፡፡ የሃገሪቱን እግርኳስ ለማሳደግ በጣም ብዙ የመፍትሄ መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካኖች አሰልጣኞቻቸው እዚያው የሚሰጣቸው ትምህርት በጥራቱ ላቅ ያለና ትልቅ ደረጃ የሚያደርሳቸው ሆኖ እንኳ የ<ላሊጋ ሜትዶሎጂ> መዋቅርን በሃገራቸው ዘርግተው በብዙ ሁኔታዎች አሰልጣኞቻቸውን እያበቁ ይገኛሉ፡፡ ካሉበት የእድገት ደረጃ በጣም ከፍ ለማለት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እጅግ ያደጉትን የእግርኳስ ሃገራት ተመክሮ ወደ ሃገራቸው አምጥተው የበለጠ ለማደግ ይታትራሉ፤ ሁሉም አሰልጣኞች በአንድ ቋንቋ የሚናገሩበትን የስልጠና <Methodology> እየሰሩበት ይገኛሉ፡፡ ፊፋ ለአለም የእግርኳስ ታዳጊ ሃገራት በየዓመቱ ወደ ሃያ አምስት ቢሊየን ዶላር ይበጅታል፡፡ ያን በጀት የሚጠቀሙ ሃገራት ጥሩ <Proposal> አቅርበው፣ የሚያድግ እቅድ አዘጋጅተውና ተግባራዊ መሻሻል አሳይተው የበጀቱ ክፍልፋይ ድርሻ ለሃገራቸው እንዲመጣና ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋሉ፡፡ የእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ የሚፈልገው የየሃገራቱ እግርኳስ እንዲያድግ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እንዲህ አይነት ሃገራዊ ትልም ሊኖረን ይገባል፡፡ ካልሆነም በየጊዜው የተወሰኑ አሰልጣኞች ወደ ውጪ እየተላኩ መማር አለባቸው፡፡ በግል የሚደረገው ጥረት ከውቅያኖስ ውሃ ውስጥ ጠብታ የመውሰድ ያህል ነው፡፡ ባለው ሁኔታ ደግሞ ተምረው የመጡት አሰልጣኞች የሚጨምሩት አበርክቶ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም፡፡ ትልልቆቹን የእግርኳስ ሃገራት እንተውና በአፍሪካ ደረጃ እንኳ ኡጋንዳን በመሳሰሉ ሃገራት አሰልጣኞቻቸው ያላቸውን <Licence> ስናይ በብዛትም በጥራትም የትናየት ርቀውን እንደሄዱ እንገነዘባለን፡፡ እኛ እኮ የሌለብን ችግር አይገኝም፡፡ አንዱ <Access> ነው፡፡ አንድ መጽሐፍ ለመግዛት እኮ የ<ቪዛ ካርድ አክሰስ> ያስፈልጋል፤ የምንፈልገውን በቀላሉ ለመገበያየት የሚያስችል ሥርዓት (System) ስላልተዘረጋ ለማንበብ የምንሻውን መጽሃፍ እንኳ መሸመት አንችልም፡፡ ለአሰልጣኞች የተደራጀና አመቺ መዋቅር ፈጥሮ የእውቀት ሽግግሮችን፣ የልምድ ልውውጦችን፣ ጥናትና ምርምሮችን፣ ግምገማዎችን የማከናወን ሥራዎች በመስራት የሃገርን እግርኳስ መታደግ ይኖርብናል፡፡ እንደ መነሻ መልካም አካሄዶችን መኮረጅ ይቻላል፤ የሆነ ቦታ ሲደረስ ግን በቀጥታ የመገልበጡ ሒደት ይቆምና የራስን ነገር ወደ መፍጠር ደረጃ መተላለፍ ይጠበቅብናል፡፡ ፈጠራ ደግሞ ከአንድ ሃገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚደጋገፍ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ የእግርኳስ ትምህርት ተቋማት የግድ ያስፈልጉናል፡፡ እድገቱ በአጭር ጊዜ እቅድ የለብለብና የአንድ ወቅት የዘመቻ ሥራ መሆን የለበትም፤ ይልቁንም ረጋ ባለና በሰከነ መንፈስ በጥልቁ በተጠና ሁኔታ ከሃገሪቱ ሌሎች የልማት እቅዶች ጋር በሰንሰለት መልክ የተያያዘ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በቃ’ኮ በርካታ ብቁ አሰልጣኞችን ማፍራት ማለት ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን መፍጠር ማለት ነው፡፡

 በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጡት አጫጭር የአሰልጣኝነት ኮርሶች እና ውጪ የምትማሯቸው ትምህርቶች ለየቅል መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ የይዘቶቹን የጥራት ልዩነት በጥቂቱ ብትዘረዝሯቸው…

★ ፋሲል ተካልኝ፦ ልዩነቱ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ እኔ ሄጄ የተማርኩት ትልቅ የ<Physical Education> ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው፡፡ ሁለት ወር ከሃያ ቀናት ለሚሆን ጊዜ ነው በዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ የቆየሁት፡፡ መምህራኖቹ በስፖርቱ ያለፉ እጅግ አንጋፎች ናቸው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት ትምህርቱን ያመቻቸው <IOC/ (International Olympic Committee)> ስለሆነ ከኦሎምፒክ ስፖርቶች ጋር ቁርኝት ያላቸው አሰልጣኞች ናቸው የመማር እድሉን የሚያገኙት፡፡ በእያንዳንዱ ኮርስ የነበሩ አስተማሪዎች በሚሰጡት ኮርስ ላይ <Spcialize> ያደረጉና አስገራሚ እውቀት ያካበቱ ነበሩ፡፡ ካስተማሩኝ ስምንት አልያም ዘጠኝ የሚሆኑ መምህራን መካከል አራቱ ወይም አምስቱ የራሳቸውን መጻህፍት የጻፉ ናቸው፡፡ በኦሎምፒክ ውድድር የተካፈሉና ስፖርቱን በአግባቡ የሚያውቁ ምሁራኖችም ይገኙበታል፡፡ በዚያ ላይ በደንብ የተደራጀና ሰፊ ጊዜ የሚወስድ ትምህርት ነበር፡፡ ለምሳሌ እኔ የ<ካፍ ኤ ላይሰንስ> ኮርስ ወስጃለሁ፤ ሆኖም የተለያዩ እርከኖች (C,B,A) ኖረውት እንኳ ከአንድ ወር በላይ አልፈጀም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ <Refreshment Coarse> ለማግኘት ብዙ ጊዜ ትጠብቃለህ፡፡ እኔ ራሴ <ኤ ላይሰንስ> ከወሰድኩ በኋላ <Refreshment Coarse> አንዴ ብቻ ነው ያገኘሁት፤ ከዚያ በኋላ የለም፤ እዚህ ኮርስ በቀላሉ አይገኝም፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው እግርኳስ በየጊዜው ይሻሻላል፤ ያድጋል፡፡ አውሮፓ ውስጥ የውድድር ዓመታቸውን ሲያገባድዱ አሰልጣኞቹ ተሰብስበው ልምዳቸውን ይጋራሉ፤ ተመክሮዎቻቸውን ይለዋወጣሉ፤ ይማማራሉ፡፡ ስኬታማዎቹ አሰልጣኞች እንዴት ባለ ድል እንደ ሆኑ ትምህርታዊ ገለጻዎችና ማብራሪያዎችን (Presentations) ያቀርባሉ፤ ትልልቅ አሰልጣኞች ተጋባዥ ሆነው ይገኛሉ፤ ሃሳቦቻቸውን ያሰማሉ፡፡ እኛ ለዚህ አልታደልንም፤ ልምዱም የለንም፡፡ ሰፊው ልዩነት ከዚህ ይጀምራል፡፡ በሙያው ውስጥ የተሰማራን አሰልጣኞችም ለዚህ ጉዳይ እምብዛም ግድ አይኖረንም፡፡ ከእነዚህ ውይይቶች መማር እንደሚቻል፣ በልምድ ልውውጡ የሃገራችንን እግርኳስ ማሻሻል እንደምንችል አልተገነዘብንም፡፡ ለምሳሌ፦ ጓርዲዮላ ከባርሴሎና ጋር ሻምፒየንስ ሊግ ካነሳ በኋላ መድረክ ይዘጋጅለትና ልምዱን ለሌሎች እንዲያጋራ ይደረጋል፤ ጥያቄና መልሶቹ በራሱ በየጊዜው ስለተፈጠሩ አዳዲስ ነገሮች መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ትምህርት በተለያዩ መንገዶች ይኖራል፤ እኛ ጋር ግን ይህ አይነቱ ሥርዓት አልተለመደም፤ ከዚህ አንጻር ትርምህርት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋለው ልዩነት እጅግ የሰፋ ነው፡፡ ለዚህ’ኮ ነው ሁሉም ሰው ውጪ ሃገር <ስኮላር> ማግኘትህን ሲያውቅ ቀድሞ ” እንኳን ደስ ያለህ!” የሚልህ፡፡ እዚያ ሄደህ የተሻለ ነገር ስለማግኘትህ እርግጠኝነትን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ ይህን ስል ግን ‘በሃገራችን የነበሩ አሰልጣኞች አላስተማሩንም፡፡’ እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ የነበረውን አስቸጋሪ የእግርኳስ ሥርዓትና በስፋት የተንሰራፋውን ችግር እየታገሉ እኛን ጥሩ አሰልጣኝ ለማድረግ ጥረዋል፤ ሁሉጊዜም የተሻለ አሰልጣኝ እንድንሆንና የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረን የአቅማቸውን አሻራ ጥለዋል፡፡ ስለዚህ ያሉት ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ መታገልን ይጠይቃል እንጂ ልዩነቶቹ በጣም ሰፋፊ ናቸው፡፡

+ ወደ ወጪ እየላኩ ማስተማሩ ከባድ ከሆነ እዚሁ የሚሰጡትን ትምህርቶች የጥራት ደረጃ ለመጨመር እንዲሁም ያለውን የትምህርት አሰጣጥ ሒደት ለማዘመን የሚመቻቹት ግብዓቶች ምንድን መሆን አለባቸው?

★ ዕድሉ ደረጀ፦ ሁሉም ነገር መነሻ ያስፈልገዋል፡፡ መጀመሪያ ችግራችንን እንለይ፤ እንወቅ፤ (Problem Identification) የሚሉትን ማለቴ ነው፡፡ የችግሩን መጠንና በእግርኳሱ እኛ ያለንበትን ደረጃ እንመርምር፤ ጊዜ ተወስዶ በጥልቀት ጥናት ይደረግ፡፡ የአንድን ችግር መንስዔ ማግኘት ማለት ለመፍትሄው ሃምሳ በመቶ ቀረብን ማለት ነው፡፡ ከዚያ የመፍትሔ አማራጮችን ወደ ማጤን እንሄዳለን፡፡ አሰልጣኞችን ወደ ውጪ ልኮ ማስተማር አልያም ብቁ የማስተማር ባለሙያዎችን እያስመጡ ትምህርቱን መስጠት ላይ ብቻ ሳይሆን ተገቢ የስልጠና ሜትዶሎጂ መከተል፣ በእድሜ እርከን የሚከፋፈሉ ልምምዶችን መጀመር፣ ፋሲሊቲዎችን ማዘገጃጀት፣ ብቁ አሰልጣኞች የሚፈሩባቸው መንገዶችን ማመቻቸት፣… ወዘተ የአጭር ፣ መካከለኛ እና ረጅም እቅዶችን እያረቀቅን መስራት ይኖርብናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን መጀመር ነው፡፡ የሚጀምረውን አካል ደግሞ <Seriously> ችግሩን ለይቶ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ እኔ በተማርኩበት ት/ቤት የፔሩን እግርኳስ ማህበር አጠቃላይ የ<Licencing System> መዋቅር ዘርግተው የሃገሪቱ አሰልጣኞች በተነደፈው እቅድ መሰረት እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡ የሚገርመው አሰልጣኞቹ በ<UEFA Licence> ውስጥም የሚታገዙበት ሥርዓት ይመቻችላቸዋል፡፡ ባለሙያዎች የሚበቁበትን ሥርዓት የመፍጠር ድርሻ የተቋም፣ የፌዴሬሽን፣ የዩኒቨርሲቲ አልያም የሌላ አካል ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላማ አሰልጣኞች በሚዘረጋው ሲስተም ውስጥ ራሳቸውን በእውቀት የማጎልበት ሥራ ይሰራሉ፡፡ እውቀት ብዙ ቦታ ይገኛል፡፡ ነገርግን <Structured> በሆነ ደረጃ መስራት ይገባናል፡፡ የመማማሪያ መድረኮች ማዘጋጀት እና የአሰልጣኞች ውይይት መልመድ አለብን፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ ከመሰባሰብና መቀራረብ ይጀምራል፡፡ የሌሉን ነገሮች ላይ እንመክርና ወጥነት ወዳለው ስራ መግባት እንችላለን ማለት ነው፡፡

ይህን ሥራ የመጀመር ተነሳሽነት ማን ይውሰድ? የእግርኳስ ማህበሩ? አሰልጣኞች?… እስካሁን እነዚህ ሁኔታዎች አልተመቻቹ ይሆናል፤ ኃላፊነቱን ወስዶ እንዲሰራ የሚጠበቀው ከየትኛው አካል ነው?

★ ፋሲል ተካልኝ፦ እኔ ማንም ቢጀምረው ግድ የለኝም፤ ዋናው መጀመሩ እስከሆነ ድረስ፡፡ ሥራው ግን በትልቁ <Organized> መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡ አንድ-ሁለት ሰው ተነስቶ ሊያዘጋጀው የሚችለው ነገር አይደለም፡፡ እያወራን ያለነው ስለ ትምህርት፣ እውቀትና አሰልጣኞች አንድ ማህበር መስርተው ስለሚማማሩበት ሒደት ነው፡፡ ለእኔ በተቋም ደረጃ የዚህ ሃገር እግርኳስ የመጀመሪያ ባለቤት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ በዚያ ውስጥ የተለያዩ ክፍሎች አሉ፤ ቴክኒክንና አስተዳደሩን የሚመለከቱ ክፍሎች፡፡ የሚመለከታቸው ክፍሎች ይህን ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም የአሰልጣኝነት ኮርሶች በፌዴሬሽኑ በኩል የሚመጡ ናቸው፡፡ አሰልጣኞችን አስተባብሮ ራሳቸው የሚማማሩበትን መንገድ መፍጠር የግድ ነው፡፡ እድሉ እንደገለጸው በሌሉን ነገሮች ላይ ለመወያየት እንኳ መሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ ኮርሶችን ማዘጋጀትና ባለሙያዎችን አሰባስቦ ማስተማር በተቋም ደረጃ ቢሆን የበለጠ የተደራጀ ቅርጽና ይዘት ይኖረዋል ፤ ስለዚህ ይህን ኃላፊነት ፌዴሬሽኑ በአግባቡ ቢወጣው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ በኢንስትራክተር አብርሃም መብራህቱ አማካኝነት ከጥቂት ጊዜያት በፊት የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞችን በመጥራት የሆነ ነገር ለመስራት አስበን ነበር፡፡ እድሉም ተሳትፎበታል፡፡ ቀደም ሲል ለብሄራዊ ቡድን ተጫውተው ያሳለፉ ተጫዋቾች እግርኳሳችን ምን እንደሚፈልግ በደንብ ያውቁታል፡፡ እነርሱንም ጠርተን ውይይት አደረግን፡፡ የምንፈልገውን ያህል ባይመጡም ለመጀመር ያህል ውይይት ማድረጉን ጀምረነዋል፡፡ ነገርግን ጠንካራ አቅም የሚጠይቅና የተደራጀ መሆንን የሚፈልግ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

★ ዕድሉ ደረጀ፦ አዎ ፌዴሬሽኑ መነሻ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የእግርኳስ ማህበራት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና መንግስት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለአብነት እንኳ ብጠቅስ አሁን ተምሬ የመጣሁበት ት/ቤት ተጫዋቾች የመጨረሻው ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የሚያልፉበትን የሥልጠና ሜትዶሎጂ ለማዘጋጀት አንድ ሰው ነው ያስፈለገው፡፡ አልበርት ሩድ የተባለው ይህ ግለሰብ ሰፊ ጥናት አድርጎ በእግርኳሱ ውስጥ ያሉትን Concepts /ጽንሰ-ሐሳቦች/ ሰብስቦ በይዘታቸው /Contents/ ለማስቀመጥ አስር ዓመት ሙሉ ፈጅቶበታል፡፡ ሰውየው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (Physical Exercise) ምርምሩን የድግግሞሽ ሙከራ (Trial-And-Error) ታላላቅ የ<Physiology> ምሁራኖችን ባፈራው የሊቨርፑሉ ጆርጅ ሙር ዩኒቨርሲቲ ገብቶ እስከመማር ደርሷል፡፡ እንግዲህ አልበርት ሩድ አንድ ግለሰብ ነው፡፡ የሚደንቀው ግን He changed the world. ከስፔን ቆይታዬ ካገኘሁት ልምድ ኢስፓኞል የራሱ የሆነ <Academic Methodology> አለው፤ ባርሴሎናም እንደዚያው፡፡ ከተማው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የእግርኳስ ት/ቤቶችም እንደዚሁ የራሳቸው የተደራጀ መዋቅራዊ እቅድ አላቸው፡፡ በመንግስት ሥር ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቻቸውም የተለያዩ የሥልጠና እቅዶችን እያዘጋጁ ለክለቦችና አካዳሚዎች በመስጠት ገንዘብ ይሰራሉ፡፡  ማን ያውቃል ነገ ፋሲል የሆነ ነገር ቢፈጥር? የእግርኳስ ማህበሩ አንድ <Association> ስለሆነ እንደ ትልቅ መፍትሄ ሰጪ ተቋም ልናየው አይገባም እላለሁ፡፡ ፌዴሬሽኑ የክልል ፌዴሬሽኖችን፣ የመንግስትንና የዩኒቨርስቲዎችን አስተዋጽኦ በሰፊው ማካተት አለበት፡፡ አሁን እግርኳሱን በማስተዳደር ላይ ያለው አካል ካልሰራ የአሰልጣኞች ማህበር አልያም የቀድም ተጫዋቾች ማህበር መጥቶ መስራት መጀመር ይኖርበታል፡፡ የማስጀመሩን ሚና ለሆነ አንድ አካል ሰጥተን ማስቀመጥ የለብንም፤ በእርግጥ ያ ተቋም ኃላፊነትና ግዴታ ሊኖርበት ይችል ይሆናል፤ ነገርግን የሚጠበቅበትን መወጣት ካልቻለ <Passion> ኖሮት የሃገሩ እግርኳስ እድገት የሚያስቆጨው አካል ቀረብ ብሎ የበኩሉን ማበርከት ይችላል፡፡ ተስፋ ቆርጠንና ተነሳሽነትን ለሌሎች ሰጥተን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን እኛም የየግላችንን አበርክቶ ማቅረብ ይኖርብናል፡፡


ቃለ-ምልልሱን በቪድዮ ለመመልከት፡ YOUTUBE