የተጫዋቾች ደሞዝ ገደብ እንዲኖረው ተወሰነ (ዝርዝር ዘገባ)

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የስፖርት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን የተጫዋቾች የደሞዝ ጣራን ለመወሰን የተጠራው የውይይት መድረክ ዛሬ ረፋድ በቢሾፍቱ ሊሳቅ ሪዞርት ተካሂዷል፡፡

ከተያዘለት ሰዓት እጅጉን ዘግይቶና ከጠበቀው በታች ተሳታፊ የተገኘበትን የዛሬው የምክክር መድረክ የስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ከፍተኛ አመራሮች፣ የክለብና የክልል ፌዴሬሽን አመራሮች የታደሙበት ሲሆን የምክክር መድረኩት የከፈቱት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ምንም እንኳ ይህ ጉዳይ በቀጥታ ፌደሬሽኑን የሚመለከት ጉዳይ ባይሆንም አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ይህንን የምክክር መድረክ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም አጀንዳው ለፌዴሪሽኑ አዲስ አለመሆኑን አውስተው ከዚህ ቀደም ብሎ በሦስት አጋጣሚዎች ለማካሄድ ታስቦ መክሸፉን አስረድተዋል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው በሀገራችን ክለቦች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣውን ጤናማ ያልሆነ የፋይናንስ አጠቃቀም ሂደትን በዘላቂነት ለመፍታት በሰከነ መልኩ ሀሳቦችን ለማንሸራሸርና በቀጣይ የጠራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተጠራ ታሪካዊ የውይይት መድረክ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ይህ በየወቅቱ ያለበቂ ምክንያት እየጨመረ የመጣው አካሄድን በዘላቂነት በመቅረፍ በሂደት ጤናማ የሆነ የመፎካከርያ ሜዳ ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ሲሉ አደራ አዘል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመቀጠል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ማናጀር የሆኑት ተድላ ዳኛቸው ለውይይት መነሻ የሚሆን የተጫዋቾች የክፍያ ጣሪያ ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎችና በሀገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በጥቅል ሊያሳይ የሚችል የመነሻ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡

በተጫዋቾች የደሞዝ ጣሪያ ምንነትና አጠቃላይ ሂደት ዙሪያ ያጠነጠነው የመጀመሪያ የፅሁፍ ክፍል በጥቅሉ የቀደሙ ፅሁፎች ዳሰሳ ላይ ያተኮረ ነበር፤ በመቀጠልም በዓለም አቀፍ እንዲሁም በአህጉራችን ደረጃ ያለውን የደሞዝ ጣሪያ የሚያሳይ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም ዳሰሳ እንደተገለፀው በአሁኑ ወቅት በአህጉራችን አፍሪካ በአመዛኙ በሚገኙ ሊጎች የሚካፈሉ ቡድኖች በአማካይ ለአንድ ተጫዋች በወር ዝቅ ሲል 100 የአሜሪካ ዶላር በአማካይ ደግሞ 600-1000 የአሜሪካ ዶላር በደሞዝ መልክ የሚከፍሉ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

በማስከተልም የጥናቱን ሰፋ ያለውን ክፍል የያዘው በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታና የደሞዝ አከፋፈል ሂደትና የክለቦች የገንዘብ አቅም ዙሪያ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡ በዚህ የዳሰሳ ጥናት ላይ እንደቀረበውም ከ1980ዎቹ በፊት ከ400-500 ብር የወቅቱ ከፍተኛ ክፍያ የነበረ ሲሆን በ1990 ጀምሮ መካሄድ ከጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውልደት ጀምሮ ክፍያው ወደ 1000 ብር ማደጉ ተገልጿል፤ ከ2003 ጀምሮ ደግሞ ወርሃዊ የደሞዝ ክፍያ 3550 ብር ያሻቀበ ሲሆን ከዚህ ወቅት አንስቶ የፊርማ ክፍያም በከፍተኛ ሁኔታ ስለመጨመሩም ተነግሯል። በተመሳሳይ እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጠናቀቅያ ድረስ ከፍተኛው የደሞዝ ክፍያ 304,000 ብር ስለመድረሱም ተገልጿል፡፡

በጥናቱም እንደማሳያነት በ2010 የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ሦስቱ ከፍተኛ የሊግ እርከኖች የሚከፈለው አማካይ ወርሃዊ የደሞዝ ክፍያም ተገልጿል።

*በፕሪምየር ሊግ
-ዝቅተኛ – 43,000ብር
-ከፍተኛ – 304,000ብር

*በከፍተኛ ሊግ
-ዝቅተኛ – 5,000ብር
-ከፍተኛ – 20,000ብር

*በአንደኛ ሊግ
-ዝቅተኛ – 2,500ብር
-ከፍተኛ – 3,500ብር

በ2010 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ከፍተኛና ዝቅተኛ ደሞዝ ይፋ ሆኗል። በዚህም መሠረት:-

(ዝ-ዝቅተኛ / ከ-ከፍተኛ)

ጅማ አባ ጅፋር: ዝ-15,000 ከ-304,000

ፋሲል ከነማ: ዝ-5000 ከ-189,000

ሲዳማ ቡና: ዝ-74,000 ከ-213,000

ሀዋሳ ከተማ: ዝ-150,000 ከ-166,000

ቅዱስ ጊዮርጊስ: ዝ-3,000 ከ-100,000

አዳማ ከተማ: ዝ-3000 ከ-228,000

መከላከያ: ዝ-3,100 ከ-182,000

ደደቢት: ዝ-10,000 ከ-25,000

ወላይታ ድቻ: ዝ-5,000 ከ-155,000

ድሬዳዋ ከተማ: ዝ-5000 ከ-175,000

ወልዋሎ: ዝ-15,000 ከ-166,000

መቐለ 70 እንደርታ: ዝ-73,000 ከ-190,000

ደቡብ ፖሊስ: ዝ-6,000 ከ-27,000

ስሁል ሽረ: ዝ-10,000 ከ-105,000

ባህር ዳር ከተማ: ዝ-45,000 ከ-151,000

* ኢትዮጵያ ቡና – አልተጠቀሰም

በጥናቱ በሊጉ ከሚካፈሉት ክለቦች 75% የሚሆኑት ክለቦች ቀጥተኛ የመንግስት እገዛ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ተገልጿል። በከፍተኛ ሊግ(98%) ፣ አንደኛ ሊግ(98%) ክለቦቹ በመንግስት መደገፋቸው ለመንግስት ከፍተኛ የበጀት ጫና መፍጠራቸውም ተገልጿል፡፡

አቶ ተድላ ይህ ጉዳይ በዚህ ወቅት መነሳቱ ለምን እንዳስፈለገ ሲያስረዱ

– በክለቦች መካከል ያለው ያልተመጣጠነ የደሞዝ ክፍያ
-በአጠቃላይ በሚያስብል መልኩ ከተወሰኑ ክለቦች ውጭ በመንግስት ድጎማ ላይ ጥገኛ መሆናቸው
-በዝውውር ወቅት የሚፈፀሙ ብልሹ አሰራሮች
-ክለቦች ያለ በቂ ገቢ ከፍተኛ ወጪ ላይ መጠመዳቸው
-ክለቦች በወጣት ተጫዋች ልማት ላይ እየተንቀሳቀሱ ስለማይገኝ
-ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት አንጻር ከከፍተኛ ከፋዮች ዝርዝር ውስጥ በመሪነት ደረጃ መሰለፋችን በዋነኝነት ለዚህ የደሞዝ ጣሪያ መወሰን አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡

በፅሁፍም የመጨረሻ ክፍል ላይ ለጥናቱ ምቹ ሁኔታዎና ተግዳሮቶች ከማጠቃለያ ጋር ቀርበዋል፡፡

አቶ ተድላ በጥናታዊ ፅሁፋቸው በግልጽ እንዳስቀመጡት ይህ የደሞዝ ጣሪያ በተናጥል ተጫዋቾች ደሞዝን የሚወስን ሳይሆን ክለቡ በአጠቃላይ በጀት ውስጥ ለደሞዝ የመደበው የገንዘብ ድርሻ በአጠቃላይ ላስመዘገበው የክለቡ ተጫዋቾች ዝርዝር በምን መልኩ ማከፋፈል ይኖርበታል የሚለውን የሚወስን ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በመቀጠልም ከሻይ እረፍት መልስ ተሰብሳቢዎች በ4 ቡድኖች ተከፍለው በተናጥል በቀረበው የመነሻ ፅሁፍ ላይ የቡድን ውይይት ተካሂዷል። የቡድን ውይይቱም የተጫዋቾች ደሞዝ ጣሪያ ማስቀመጥ አስፈላጊነቱ፣ ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችና አማራጭ ሀሳቦች ላይ በማተኮር በሦስት ተከፍሎ ተካሂዷል፡፡

በመቀጠል ከምሳ እረፍት መልስ አራቱ ቡድኖች የተወያዩበትን ነጥቦች በዝርዝር ለተሰብሳቢዎች ቀርበዋል፡፡ በቅድሚያም በአራቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ደሞዝ ጣራ ማስቀመጥ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያቶች በሚል ከቀረቡበት መካከል

-የስፖርት መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር
-ለሌሎች ስፖርቶች በተሻለ መልኩ እንዲያብቡ ይረዳል
-ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ
-ስፖርታዊ ጨዋነት ለማስፈን
-ጠንካራ ብሔራዊ ቡድንና ተጫዋቾች እንዲፈጠር
-ህዝባዊ መሠረት ያላቸው ክለቦች ለመፍጠር የሚደረገውን ሽግግር ያግዛል
-በሀገር ደረጃ ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲሰፍን ያግዛል

በመቀጠልም የደሞዝ ጣራው ተግባራዊ ቢሆን ሊገጥሙ ይችላሉ ተብለው በቡድን ውይይት የተነሱ ተግዳሮቶች መካከል

-ጥቅማቸው የተነኩ አካላት ዘመቻ በመክፈት ጫና ሊያሳድሩ ይችላል
-በተጫዋቾች ዘንድ ውሳኔውን ለመቀበል መቸገር (እስከ አመፅ የሚደርስ)
-መንግስታዊ ያልሆኑ ክለቦች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላል የሚል ስጋት
-የደሞዝ ተመሣሣይነት በሚተገበርበት ወቅት ተጫዋቾች ከአካባቢያቸው ርቀው ላለመጫወት መፈለግ
-የተሻለ ክፍያን ፍለጋ የሚደረግ የተጫዋቾች ፍልሰት

በስተመጨረሻም እያንዳንዱ ቡድን የክፍያ ጣራ መሆን አለበት የሚሉትን ሀሳብ አቀርበዋል ፤ በዚህም ከፍተኛው ከ50-75ሺህ ከታክስ በፊት ቢሆን እንዲሁም ዝቅተኛው 5000 መሆን ይገባዋል የሚል የመፍትሔ ሀሳብን አቅርበዋል ። አንደኛው ቡድን ግን ብዙ ነገሮች ከግምት ገብተው ወደፊት ጊዜ ተወስዶ በጥልቀት ተጠንቶ የደሞዝ ጣርያው መቀመጥ ይገባዋል የሚልን ሀሳብ በልዩነት አንፀባርቋል፡፡

በመቀጠልም ከተሰብሳቢዎች ሌሎች አልተነሱም ባሉት ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ሀሳብ ሰጥተዋል ከእነዚህም መካከል፡-

በለጠ ዘውዴ- አ.አ.እ.ፌ ተወካይ

-በጥናቱ ውስጥ ከፕሪምየር ሊጉ በታች የሚገኙ የሊግ እርከኖች መካተት አለባቸው።

– የአሰልጣኞች ደሞዝም ጣራ ሊበጅለት ይገባል

የድሬዳዋ ከተማና የጅማ አባጅፋር ተወካዮች

-በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለም
-በመንግስት በጀት ከመንቀሳቀስ ወጥተን እግርኳሱ በራሱ ገንዘብ ማመንጨት ሲጀምር ክፍያው አብሮ እያደገ መሄድ ይችላል

አሰፋ ሀሲሶ – ወላይታ ድቻ
-ይህ አጀንዳ በጣም ሲንከባለል የከረመ ጉዳይ ነው። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ በድፍረት ቁርጠኛ ሆነን ወስነን መውጣት ይኖርብናል፤ አሁን ላይ እልባት ካላገኘ በቀደመው የተበላሸ አሰራር ከመቀጠል ሊጉን ማቆም የተሻለ አማራጭ ነው

ኮማንደር ዳንኤል – ደቡብ ፖሊስ

-ስፖርቱን ልንታደግ ይገባል ፤ 50,000 ብር በጣም ይበዛል ባይ ነኝ። ይህም ሆኖ ውሳኔው ከዛሬ ማለፍ የለበትም

ዮሀንስ ሳህሌ- የኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ማኅበር ተወካይ

-400 ብር የነበረን ክፍያ 304ሺህ ብር ያደረሰው ማንም አይደለም ፤ ክለቦችና ክለቦች ናቸው፡፡ ክለቦች ከእግርኳስ መርህ ውጭ በሆነ አካሄድ በአንድ ጊዜ ውጤታማ ለመሆን ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው ፤ በዚህ ሁኔታ ክፍያው ሲንር ተጫዋቾች ክፍያውን አይቀበሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡

-የሊግ አስተዳደር በሌለበት ሁኔታ ላይ እንዴት ነው ቀጥተኛ ባላድርሻዎች የሆኑት ተጫዋቾችን የሚወክለው? የተጫዋቾች ማኅበር ከማን ጋር ነው የደሞዝ ጣራ ለመወሰን የሚደራደረው? ይህ ነገር ከሁሉም መቅደም ይኖርበታል

-ተጫዋቾች ክፍያው ይህ ካልሆነ ብለው አላስገደዱም። ስለዚህ በካፍና በፌፋ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የቡድን አጠቃላይ ለደሞዝ የሚበጅተውን በጀት እንጅ በተናጥል አንድ ተጫዋች ይህ ነው መከፈል አለበት ተብሎ በተናጥል የተጫዋች ደሞዝ መወሰን አይቻልም ፤ ይህ አሰራር በነጻ ገበያ ህግንም የሚፃረር ነው፡፡

መንግስቱ ሳሳሞ – ሲዳማ ቡና
-በዚሁ ጉዳይ ላይ እልባት መስጠት ያስፈለገው ተጫዋቾችን ለመጉዳት ሳይሆን ብዙሀኑን ተጠቃሚ ለማድረግና ኳሱን ለማሳደግ በማሰብ ብቻና ብቻ ነው፤ ክፍያው በሂደት ከእግርኳሱ ጋር ማደግ መቻል አለበት፡፡

-ይህ ጉዳይ መፍትሔ ካላገኘ የዘንድሮው ዓመት የሚደረጉ ዝውውሮች መፅደቅ የለባቸውም።

የአዳማ ተወካይ

– በዚህ ጉዳይ ላይ መወሰን ካልቻልን እግርኳሱ ቢቆም የተሻለ ነው

ኮ/ል ዐወል አብዱራሂም (የኢ.እ.ፌ ምክትል ፕሬዝዳንት)

-ግልፅ መሆን ያለበት ነገር ከእኔ ጭምር የክለብ አመራር በነበርኩበት ወቅት ዋነኛ ተዋንያኖቹ እኛ ነን፤ ግን ያኔ የእኛ ሀሳብ የነበረው እግርኳሱን በበጎ መልኩ በማነቃቃት ለማሳደግ ነበር አላማችን የነበረው። ነገርግን ሁኔታው በዛ መልኩ ሳይቀጥል መስመር ስቶ አሁን የምንገኝበት ደረጃ ላይ አድርሷናል፡፡

-ዋነኞቹ ባለጉዳዮች ክለቦች ስለሆኑና ከ80 በመቶ በላይ ክለቦች እንደመገኘታቸው ውሳኔው ማደር የለበትም፤ አለበለዚያ ውሳኔውን ለማሳደር ማሰብ ግን ገንዘብ ያለአግባብ በክብሪት እንዲነድ እንደመፍቀድ ነው የምንቆጥረው፡፡

-በ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ “በሊግ ኩባንያ” ነው የሚተዳደረው።

-የውጭ ተጫዋቾች ክፍያ ህጋዊና ግልፀኛ በሆነ መልኩ መካሄድ ይኖርበታል፡፡

በመቀጠል መድረኩን የተረከቡት አቶ ርስቱ ይርዳው የ15 ክለብ ተወካዮች ስለተገኙ የሚተላለፈው ውሳኔ ገዢ እንደሚሆን ገልፀው በቀጥታ ወደ ድምፅ አሰጣጥ እንዲገባ አዘዋል። በዚህም መሠረት ክለቦች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ የደሞዝ ጣሪያ መበጀቱን እንደሚደግፉ ገልፀዋል፡፡

በመቀጠልም ከፍተኛ ጣሪያ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ በቡድን ውይይቶች ከተገኙ ግብዓቶች መነሻ በማድረግ በተደረገው የድምፅ አሰጣጥ 50,000 ብር ከታክስ በፊት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛው የደሞዝ ጣሪያ እንዲሆን ከተገኙት 13 ተወካዮች ውስጥ በ10 ድምፅ ሊፀድቅ ችሏል። ቀሪዎቹ 3 ክለቦች ደግም 75 ሺህ እንዲሆን ሀሳብ ቢያቀርቡም በድምፅ ብልጫ የላቀው 50ሺህ ብር ሊጸድቅ ችሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ውል ያላቸው ተጫዋቾች እና ሐምሌ 25 በተከፈተው የዘንድሮው የክረምት የዝውውር መስኮት የፈረሙ ተጫዋቾች ውላቸውን አፍርሰው በአዲሱ ደንብ መሠረት ዳግም ውል እንዲያስሩ ከውሳኔ ተደርሷል፡፡

በመቀጠልም አቶ ርስቱ የማጠቃለያ ንግግራቸውን ሲያደርጉ እንደተናገሩት አሁንም የተቀመጠው የደሞዝ ጣራ በተለይ ለውጭ ተጫዋቾች በሌሎች ሀገሮች ከሚከፈላቸው አንጻር አጓጊ መሆኑን ገልፀው፤ ቁጥራቸውን ወደ 2(3) ለመገደብ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ይህ በፕሪምየር ሊጉ የተጀመረው በጎ ጅምር ወደ ሌሎች እርከኖችም ሊወርድ እንደሚችል ገልፀው ከአሁን ወዲህ መንግስት ከሌላው ጊዜ በተለየ ጠንካራ የወጪ ክትትል (Audit) እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ አሳይያስ ጅራ ይህ ሂደት በሌሎች የሊግ እርከኖችና በሴቶችም እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል፣ በቀጣይም ይህንን ውሳኔ ወደተግባር የሚያስገባ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለክለቦች የሚበተን ይሆናል ብለዋል፡፡

*ከዚህ ጋር በተያያዘ ውሳኔው ስለፊርማ ክፍያና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ምንም ያለው ነገር የለም፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡