የኮተቤ ተማሪዎች ለአስኮ ታዳጊ ፕሮጀክት ድጋፍ የሚውል የፉትሳል ውድድር አዘጋጁ

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ማኔጅመንት የ2ኛ ዓመት ተማሪዎች የአስኮ የታዳጊዎች ፕሮጀክትን ለመደገፍ የፉትሳል ውድድር አዘጋጅተዋል።

በስፖርት ማኔጅመንት የ2ኛ ዓመት ተማሪዎች DTTP Development team training program የማህበረሰቡን ችግሮች ነቅሶ ማውጣት እና ለችግሩ መፍትሄ መስጠትን በተመለከተው የትምህርታቸው ጥናት ዕድሜያቸው ከ10 ዓመታት በላይ የሆኑ ታዳጊዎችን በመያዝ በርካታ እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ መጫወት የቻሉ ስፖርተኞችን እያፈራ በሚገኘው የአሰኮ የእግርኳስ ፕሮጀክት ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል።

የአስኮ ፕሮጀክት በርካታ መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች ቢኖሩበትም እንደ መነሻ የሻወርና የመፀዳጃ ቤት ችግሮችን በማየት ስምንት የመታጠብያ እና ሁለት የመፀዳጃ ቤቶችን ተማሪዎቹ በግላቸው ገንዘብ በማውጣት እና በአከባቢው ያሉ የጤና ቡድኖችን በማስተባበር መሠረቱን ጨምሮ የተወሰናውን የግንባታውን ክፍል ማቆም ችለዋል።

ሆኖም ለጣሪያ እና ለፊኒሽንግ ሥራ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ያልቻሉ በመሆኑ ይህን ትልቅ ሀሳብ ከፍፃሜ ለማድረስ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና እና የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች በሆነው ዕድሉ ደረጄ አስተባባሪነት አስኮ በሚገኝው የፉትሳል ሜዳ ውድድር ተዘጋጅቷል። ይህን በጎ ዓላማ በመደገፍ እገዛ ለማድረግ የሚፈልጉ የቀድሞው እና አሁን በመጫወት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች በሙሉ በቡድን አምስት ሺህ ብር በመክፈል መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን የኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ማኔጅመንት የ2ኛ ዓመት ተማሪዎች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን ወደፊት የሚገለፅ መሆኑን አዘጋጆቹ ተናግረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ