የ2011 ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ውድድር በአብዲ ቦሩ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

68 ቡድኖችን አሳትፎ ያለፈውን አንድ ወር የተፈጥሮ ክህሎታቸው አስገራሚ የሆኑ ታዳጊዎችን ሲያስመለክተን የቆየው 14ኛው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ የታዳጊዎች ውድድር በአብዲ ቦሩ አሸናፊነት ተጠናቋል።

03:00 በጀመረው የደረጃ ጨዋታ ጫጫን ከአዳማ ብሩህ ተስፋ አገናኝቶ በመደበኛው የጨዋታ 4-4 በሆነ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው አዳማ ብሩህ ተስፋ 6-5 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል። ከቡድን ጨዋታ ይልቅ ሁለቱም ቡድኖች የግል አቅማቸው የተሻሉ ታዳጊዎች ያሉበት ስብስብ በመሆኑ ከቡድን ጨዋታ ይልቅ ታዳጊዎቹ በግል ጥረታቸው በሚያሳዩት እንቅስቃሴ በርከት ያሉ ጎሎችን እንድንመለከት አድርጎናል። ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ጫጫዎች በፍቃዱ ታሪኩ ከርቀት በተቆጠረ ግሩም ጎል ነበር። አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ብዙም ያልዘገዩት አዳማዎች በአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጎል አንድ አቻ መሆን ቸለዋል። በአንድ ሁለት ቅብብል በፍጥነት ወደ ጎል የሚደርሱት ሁለቱም ቡድኖች በቀላሉ ጎል ለማስቆጠር አልተቸገሩም ነበር። የጫጫው በበለጠ አሰፋ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጫጫዎች መምራት ቢችሉም የውድድሩ ክስተት በሆነው ተስፈኛው ታዳጊ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ጎል አዳማዎች ሁለት አቻ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ከእረፍት መልስ ብልጫ ወስደው የተጫወቱት አዳማዎች በጨዋታው ጅማሬ ዮናስ ትዕግስቱ በጥሩ መንገድ የተቀበለውን ወደ ፊት ይዞ በመግባት ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ አዳማዎችን መሪ አድርጓል። ፉክክሩ ቀጥሎ በጫጫ በኩል የወደፊት ተስፈኛ ተጫዋች በሆነው ደርቡ ተስፋዬ አማካኝነት ጫጫዎች ሦስት አቻ መሆን ችለዋል። በዚህ ታዳጊ እድሜው ትክክለኛ የአጥቂ ባህሪ የተላበሰው የአዳማው አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራበትን አራተኛ ጎል አስቆጥሮ በድጋሚ አዳማዎችን መሪ አደረገ። በመጨረሻም ጨዋታው በአዳማዎች አሸነፊነት ተጠናቀቀ ሲባል በፍቃዱ ታሪኩ ለጫጫ አቻ የሚያደርጋቸውን አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው አዳማ ብሩህ ተስፋ 6-5 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

04:30 የቀጠለው የዕለቱ የፍፃሜ ጨዋታ አብዲ ቦሩን ከኤንፓ አገናኝቶ አብዲ ቦሩ በሰፊ የጎል ልዩነት ከጨዋታ ብልጫ ጋር 6-2 በማሸነፍ የዋንጫ አሸናፊ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል። እንደ ፍፃሜ ጨዋታ ብዙም ፉክክር ባልታየበት ይህ ጨዋታ አብዲ ቦሩዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰው ማሸነፍ ቢችሉም ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ኤንፓዎች ናቸው። በዘንድሮ ውድድር የቅጣት ምት ጎል በማስቆጠር የተካነው አማኑኤል አዳነ ከቅጣት ምት ኤንፓዎችን መሪ ማድረግ ቢችልም ብዙም ሳይቆይ በተመሳሳይ መንገድ አብዲ ቦሩዎች በመሐመድ አብዱልአዚዝ ጎል አቻ ሆነዋል። ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ የተቆጣጠሩት አብዲ ቦሩዎች በግሩም ሁኔታ በግራ እግሩ የበረኛውን አቋቋም አይቶ ብሩክ ፍቃዱ ባስቆጠረው ጎል መምራት ችለዋል።

ከእረፍት መልስ አብዲ ቦሩዎች አከታትለው ዮናስ ከበደ እና ፉራኦል አብዩ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች የጎል መጠናቸውን ወደ አራት ማድረስ የዋንጫ የማንሳት ዕድላቸውን አስፍተዋል። ተስፋ በቆረጠ እንቅስቃሴ በአንድ አጋጣሚ አምሐ ዳምጠው ለኤንፖዎች ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የተነቃቁ ቢመስሉም አብዲ ቦሩዎች የውድድሩ አሸናፊ ሆነው እንዲያጠናቅቁ ያስቻሉ ሁለት ጎሎች ብሩክ ፍቃዱ በጨዋታ እና ሀቢብ አስማው በፍፁም ቅጣት ምት አምስተኛ እና ስድስተኛ ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በአብዲ ቦሮዎች 6-2 በማሸነፍ የውድድሩን ዋንጫ አንስተዋል።

በመጨረሻም የውድድሩ መዝግያ ሥነ ስርዓት ላይ የክብር እንግዳ የሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ አባል አቶ ዳዊት ውብሸት፣ የክለቡ የቴክኒክ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛቸው እና የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን በቀለ በየተራ ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡት ቡድኖች የሜዳልያ እና ለእያዳዳቸው ቡድኖች አምስት የኳስ እንዲሁም የስፖርት ትጥቅ ሲያበረክቱ ለወድድሩ አሸናፊ ለአብዲ ቦሩ ታዳጊዎች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።

ከዓመት ዓመት ተተኪ ተጫዋቾችን እያፈራ በአጓጊነቱ እየቀጠለ የሚገኘው እና እጅግ ስኬታማ ሆኖ የተጠናቀቀው የዘንድሮው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር በቀጣይ ዓመት ብዙ ታዳጊዎች እንዲያነሳሳ እና ስፖርት ቤተሰቡ በቅርበት የሚከታተለው ውድድር እንዲሆን የውድድሩ አዘጋጅ አካላት በተሻለ ሜዳ እና ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ውድድሩ ቢካሄድ መልካም ነው እንላለን።


* ኮከብ ተጫዋች – አብዱልሃዚዝ አብዱሬ (አብዲ ቦሩ)

* ኮከብ ጎል አስቆጣሪ – አማኑኤል ገ/ሚካኤል (በ9 ጎል ከአዳማ ብሩህ ተስፋ)

* ኮከብ አሰልጣኝ – አበበ ተስፋዬ (አብዲ ቦሩ)


© ሶከር ኢትዮጵያ