ጅማ አባ ጅፋር የስታዲየም ለውጥ ለማድረግ አቅዷል

ጅማ አባ ጅፋሮች ለመጪው የውድድር ዘመን የስታዲየም ለውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ክለቡ ከ1975 ጀምሮ ያለፉትን 37 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ በቆየው በአንጋፋው ጅማ ስቴድየም ውድድሮቻቸውን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተመልካች ቁጥር በመጨመሩ እና የጅማ ስታዲየም ለረጅም ዓመታት ያለዕድሳት በመቆየቱ የክለቡ አመራሮች አማራጮችን ሲያጤኑ መቆየታቸው ተገልጿል።

ሶከር የኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሰረት ክለቡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባውን ግዙፍ ስታዲየም ለመጠቀም ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ሜዳውን ለመጪው የውድድር ዘመን ለማድረስ ተመልካች ከሜዳ የሚለይ አጥር የማጠርና የመጫወቻው ሜዳውን ለውድድር ዝግጁ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

አዲሱ ስታዲየም ያለመቀመጫ ከሰማንያ ሺህ ሰው በላይ እንደሚይዝ የታወቀ ሲሆን የማጠቃለያ ስራዎች ተጠናቀው መቀመጫ ሲገጠምለት አስከ አርባ ሺህ ሰው እንደሚይዝ ታውቋል። ይህም ክለቡ ከመግቢያ ቲኬት የሚያገኘውን ገቢ ከፍ እንደሚያደርግለት ይጠበቃል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ