በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ተካሂደዋል፡፡ ፔትሮጀት ኢኤንፒፒአይን ባስተናገደበት ጨዋታ ሽመልስ በቀለ ለፔትሮጄት ተቀይሮ ገብቶ ሲጫወት አጥቂው ኡመድ ኡኩሪ ግን ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ከኢኤንፒፒአይ ቡድን ውጪ ሆኗል፡፡
በአል ሱዌዝ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን የአጥቂ አማካዩ ሽመልስ በ86ኛው ደቂቃ አህመድ ጋፍርን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ አንድ ቀሪ የሊግ ጨዋታ የሚቀረው ፔትሮጀት በ23 ነጥብ 7ኛ ሲሆን ሁለት ቀሪ ጨዋታ የሚቀረው ኢኤንፒፒአይ በ2 ነጥብ አንሶ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
የግብፅ ፕሪምየር ሊግን ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው የግብፅ ሱፐር ካፕ አሸናፊው አል-አህሊ በ32 ነጥብ ይመራል፡፡ የሊጉ ሻምፒዮን ዛማሌክ በተመሳሳይ ሁለት ቀሪ ጨዋታ እየቀረው በአንድ ነጥብ አንሶ ሁለተኛ ነው፡፡ መከላከያን በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሚገጥመው ምስር አል ማቃሳ በ30 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በተያያዘ ዜና በአብሳ ፕሪምየርሺፕ አማተክስ ማፑማላንጋ ብላክ ኤስን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ጌታነህ ከበደ ከቡድኑ ውጪ በመሆኑ ሳይሰለፍ ቀርቷል፡፡ ጌታነህ በዓመቱ መጀመሪያ ቤድቬስት ዊትስ ለቆ በውሰት የፕሪቶሪያውን ክለብ የተቀላቀለ ሲሆን ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ ለአማተክስ የአሸናፊነቷን ግብ የማላዊ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነው አቱሳዬ ናዮንዶ ጨዋታው በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡
የጌታነህ ባለቤት ክለብ ቢድቬትስ ዊትስ ሁለት አጥቂዎችን በጥር የዝውውር መስኮት ያዘወረ ሲሆን በዓመቱ መጨረሻ ለጌታነህ የውል ማራዘሚያ የማቅረብ እድሉ የጠበበ ይመስላል፡፡