በአፍሪካ ሃገራት ዋንጫ የምድብ 4 ጨዋታ ዛሬ በስታደ ኡሙጋንዳ እና ስታደ ናያሚራምቦ ተደርገው ዛምቢያ እና ማሊ የመጨረሻዎቹ ስምንት ውስጥ መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የሴካፋ ሻምፒዮኗ ዩጋንዳ ከዚምቧቡዌ ጋር አቻ በመለያየቷ ከምድቧ ሳታልፍ ቀርታለች፡፡
ዛምቢያ እና ማሊ ባደረጉት ጨዋታ ቺፖሎፖሎዎቹ ቀድመው ማለፋቸውን በማረጋገጣቸው ጨዋታው አስፈላጊ የነበረው ለምዕራብ አፍሪካዊኑ ነበር፡፡ ያለግብ አቻ የተለያዩት ሁለቱ ሃገራት ተያይዘው ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል፡፡ ዛምቢያ በሶስት የምድብ ጨዋታዎች 2 ግቦችን ብቻ ስታስቆጥር ግቧን ሳታስደፍር ሶስቱንም የምድብ ጨዋታ ጨርሳለች፡፡ በ2012 ቢቢሲ አፍሪካ የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ክርስቶፈር ካቶንጎ እና አይዛክ ቻንሳ ፊት አውራሪነት ቺፖሎፖሎዎቹ ምድባቸውን በበላይነት ጨርሰዋል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት በተደረገው የምድቡ ሌላ ጨዋታ ለማለፍ የጠበበ ዕድል የነበራት ዩጋንዳ መውደቋን ቀድማ ካረጋገጠችው ዚምቧቡዌ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታዋን ጨርሳለች፡፡ ግብ በማግባት ቅድሚያውን የወሰደችው ዚምቧቡዌ ነበረች በዊልያም ማኖንዶ አማካኝነት፡፡ ማኖንዶ በ49ኛው ደቂቃ ነበር ዚምቧቡዌን መሪ ያደረገው፡፡ በአይዛክ ሙሌማ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ጆፍሪ ሴሬንኩማ ክሬንሴቹን በ94ኛው ደቂቃ አቻ አድርጓል፡፡ ዩጋንዳ የቻን2016 ዕቅዷ የነበረው ግማሽ ፍፃሜ መድረስ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ምድብ አራትን ዛምቢያ በ7 ነጥብ በበላይነት ስታጠናቅቅ ማሊ በ5 ነጥብ ሁለተኛ ሆኗ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅላለች፡፡ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች በመጪው ቅዳሜ ጀምረው ይደረጋሉ፡፡
ቅዳሜ
ሩዋንዳ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ
ካሜሮን ከኮትዲቯር
ዕሁድ
ቱኒዚያ ከማሊ
ዛምቢያ ከጊኒ
ምስል – CAF እና soka.co.ke