የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዛሬ ሲጀምር ኤርትራ እና ዩጋንዳ ነጥብ ተጋርተዋል

2010 በኤርትራ አዘጋጅነት ከተካሄደ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ ቆይቶ ከወራት መስተጓጎሎች በኃላ ዛሬ የተጀመረው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ዛሬ በመክፈቻው ሦስት ጨዋታ ሲያስተናግድ አዘጋጇ ዩጋንዳ ከ ኤርትራ ጋር አንድ አቻ ተለያይታለች። ሱዳን ደግሞ በድል ውድድሩን ጀምራለች።

ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ በዋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዓለምሰገድ ኤፍሬም ስር በዝግጅት የቆዩት የቀይ ባህር ግመሎች በውድድሩ ጥሩ ግምት ከተሰጣት ዩጋንዳ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት አቻ ተለያይተው ነጥብ ማስጣላቸው የብዙዎችን ትኩረት እንዲስቡ አድርጓቸዋል።

ቡድኖቹ በዚህ የብሄራዊ ቡድን እርከን 2010 ኤርትራ ባዘጋጀችው ውድድር ለመጨረሻ ጊዜ ተገናኝተው ዩጋንዳ በፍፁም ቅጣት ምት ማሸነፏ ይታወሳል።

በሌሎች የመክፈቻ ጨዋታዎች ሱዳን ጅቡቲን በቀላሉ 4-0 በማሸነፍ በጥሩ ሁኔታ የውድድሩ ጉዞዋን ስትጀምር ቡሩንዲ ከ ደቡብ ሱዳን ያደረጉት ጨዋታ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውድድሩ ለቀጣይ አስራ አራት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን በምድብ አንድ የሚገኙት ቡድኖች በጉሉ ከተማ፤ በምድብ ሁለት እና ሦስት የሚገኙት ቡድኖች ደግሞ ንጁሩ በተባለ ከተማ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።

የነገ ጨዋታዎች
ኬንያ ከ ዛንዚባር
ኢትዮጵያ ከ ታንዛኒያ


© ሶከር ኢትዮጵያ