ቻን 2020| የዋልያዎቹ አሰልጣኝ እና አምበል ከጨዋታው በፊት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና አምበሉ አስቻለው ታመነ ከጨዋታው አስቀድመው ዛሬ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል።

11:00 ይጀመራል ተብሎ አርባ አምስት ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረው ጋዜጣዊ መግለጫው የፌደሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት አቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫው በተባለበት ጊዜ ባለመጀመሩ ይቅርታ ጠይቀው ሲከፍቱት ዋና አሰልጣኙ አብርሀም መብራቱ እና አምበሉ አስቻለው ታመነ አከታትለው ሃሳባቸውን በመስጠት ከጋዜጠኞች የተነሱትን ጥያቄዎችም መልሰዋል።

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ

ልምምዳችንን የጀመርነው ቅዳሜ ሲሆን ለስምንት ቀናት ልምምድ ሰርተናል። ከዝቅተኛ ጫና ነው ልምምዳችን የጀመርነው። ከአቀባበል ጀምሮ በጣም ጥሩ አቀባበል ነው የተደረገልን። ከሆቴል ጀምሮ ጥሩ መስተንግዶ ተደርጎልናል።

በመጀመርያዎቹ ቀናት የሜዳው ሳር በማደጉ እንደፈለግነው ልምምዳችን አላከናወንም ነበር። በኋላ ግን የክልሉ ፌዴሬሽን ባደረገው ጥረት ሳሩ ከተስተካከለ በኃላ በጥሩ ሁኔታ ልምምዳችን ሰርተናል። የመቐለ 70 እንደርታ እና የወልዋሎ አሰልጣኞች ገ/መድህን ኃይሌ እና ዮሐንስ ሳህሌ የራሳቸውን ፕሮግራም ገፍተው የልምምድ ሜዳ ስለሰጡን እናመሰግናለን።

ከጀማል ጣሰው ውጭ ሁሉም ከጉዳት ነፃ ሆነው ዝግጁ ናቸው። ከነዓን ማርክነህ ከገጠመው መጠነኛ ጉዳት አገግሟል። ሱራፌል ዳኛቸው በካፍ ውድድር ባለው ቢጫ ምክንያት አይሰለፍም። ፍፁም ዓለሙ ደግሞ በፓስፖርት ምክንያት አይሰለፍም። ፍፁም የስም ለውጥ ካደረገ በኃላ (ከኤፍሬም ወደ ፍፁም) ሂደቱ ቶሎ ማለቅ አልቻለም።

አሰቻለው ታመነ

ከአቀባበል ጀምሮ የተደረገልን ነገር ጥሩ ነው።
የመቐለ ነዋሪ እናውቀዋወለን እግር ኳስ ወዳድ ነው። ቡድኑ መካከል ጥሩ መንፈስ አለ። ከአሰልጣኙ የተሰጠንን ነገር በሚገባ እየሰራን ነው።

ከጋዜጠኞች ለተነሱት ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ

አሰልጣኝ አብርሀም

ስለ ግብ ማግባት ችግር

መቐለ ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ በአጨራረስ ብዙ ስራዎች ሰርተናል። የሚታየው የአጨራረስ ችግር ቡድኖች ላይ የሚታየው ችግር ነው መሰረት ላይ ክለቦች ስላስተሰራለት ነው እሱን በሂደት እናስካክላለን። ለነገ ጨዋታ ግን ብዙ ስራዎች ሰርተናል ብዙ መሻሻልም አለ።

ስለ ተጋጣሚ

ጠንካራ ቡድን ነው። የዓለም ዋንጫ ማጣርያው የደርሶ መልሱ ጨዋታ አይተናል። ሲሰልሽን ከገጠመው ቡድን አራት ተጫዋቾቻቸው እኛን አይገጥሙም፤ እሱን ጨዋታ ፊልሙን በደምብ ተመልክተናል። እዚህ ከመምጣታቸው በፊት ስላደረጉት ጨዋታ ከፅሁፍ ውጭ በቪድዮ ማየት አልቻልንም። እነሱ የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርገዋል፤ እኛ በአንፃሩ አላደረግንም። ግን እሱን ክፍተት እዚህ ባደረግናቸው የእርሰ በርስ ጨዋታዎች ለመፍታት ሞክረናል።

ስለ ፓስፖርት

ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ይህንን ችግር ለመፍታት እየሞከርንን ነው። ፍፁም ዓለሙ ከዚ ቀደም የሚታወቅበት ስሙ ስለተቀየረ እሱን በጊዜው ማስተከከል አልቻልንም።

ስለ አጠቃላይ ዝግጅታቸው

በተጫዋቾቻችን ላይ ያለው መነሳሳት በጣም ጥሩ ነው። እንደ ቤተሰብ እየሰራን ነው። የተጫዋቾቻን የስነ-ልቦና ዝግጅትም ጥሩ ነው። ከአዳማ እና አዲስ አበባ ዩንቨርስቲዎች በመጡ ባለሞያዎች እገዛ እየተደረገልን ነው። የመቐለ እና አከባቢው ህዝብ የነገው ጨዋታ ድጋፍ ይሰጠናል ብዬ እጠብቃለው። ህዝቡ ሜዳ ገብቶ ቡድናችን እንዲያበረታታም ጥሪዬን አቀርባለው።

አስቻለው ታመነ

ስለ ዝግጅታቸው

ሌሶቶ ላይ ጥሩ የሥራ ፍላጎት ነበረን። ያንን ለማስቀጠል አሁንም እንሰራለን። የሃገር ውስጥ ተጫዋቾች ደረጃ የት ነው ያለው የምናውቅበት ስለሆነ ጨዋታው ወሳኝ ዝግጅታችንም ጥሩ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ