በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ዙር የሲሸልሱን ሴንት ሚሸልን የሚያስተናግደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚያደርግ ከክለቡ ታማኝ ምንጮች ያገኘናቸው መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
ፈረሰኞቹ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታቸውን ሃዋሳ ለማድረግ አቅደው የነበረ ቢሆንም የሃዋሳ ስታዲየም በካፍ ዕውቅና እስኪያገኝ የሚፈጀው ግዜ ረጅም ስለሆነ ክለቡ ጨዋታውን በኢትዮጵያ መዲና ላይ ማድረግን መርጧል፡፡
ካፍ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የሃዋሳ ስታዲየምን የገመገመ ሲሆን ለስታዲየሙ ዕውቅና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፈረሰኞቹ ዓምና በተመሳሳይ ውድድር የሜዳ ጨዋታቸውን በባህርዳር ስታዲየም የአልጄሪያውን ኤምሲ ኤል ኡልማን ያስተናገዱ ሲሆን ለሁለተኛ ተከታታይ ግዜ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታቸውን ከአዲስ አበባ ውጪ የማድረግ ተስፋቸው አሁን መንምኗል፡፡
ክለቡ በሃዋሳ ስታዲየም መጫወትን የመረጠው የተሻለ የሜዳ ገቢ ለማግኘት ነበር፡፡ ጊዮርጊስ ለመጨረሻ ግዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታውን ያደረገው ከግብፁ ዛማሌክ ጋር 2-2 በተለያየበት ጨዋታ ነበር፡፡