የአሰልጣኞች ገጽ | አብርሀም ተክለሃይማኖት፡ አስተዳደር እና አስተዳዳሪዎች (ክፍል 4)

የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ በሚዳስሰው “የአሰልጣኞች ገፅ” አሰልጣኝ አብርሀም ተክለሃይማኖትን በተከታታይ እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። በዛሬው የክፍል 4 መሰናዷችን ስለእግርኳስ አስተዳደር፣ አስተዳዳሪዎች እና ተያያዥ ጉዳዮችን እያነሳን ቆይታ እናደርጋለን።


እግርኳሱን በሚመራው አካል ዙሪያ ወይም በአሰልጣኝነት ሙያ ላይ ውይይቶች ሲደረጉ ጽንፍ ይዞ የመሟገት ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ ” እግርኳሱን መምራት ያለበት ተጫውቶ ያሳለፈ ባለሙያ ነው፡፡የሚሉ ወገኖች በአንድ በኩል በስፖርት ሳይንስ፣ በስፖርት አመራር፣ በእግርኳስ አስተዳደር፣እና በሌሎችም የትምህርት ዘርፎች የተማረ መሆን ይገባዋል፡፡የሚሉት ደግሞ በሌላ ወገን ሆነው ክርክሩን ያጦፉታል፡፡ እግርኳስ ሁሉን ዓቀፍ ከመሆኑ አንጻር ይህን ጽንፍ ይዞ የመካረር ሁኔታ እንዴት ታየዋለህ?

★ ያው ጽንፍ ሁሌም ጽንፍ ነው፡፡ በአዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጉዳዮች አንዴ ጽንፍ ከያዝክ ሃሳቦችን አታስተናግድም፡፡ ጽንፈኛ ሁልጊዜ አጥፊ ነው፡፡ እኔ ሰዎችን ጽንፍ እንዲይዙ የሚያደርጋቸው ሒደቱ ይመስለኛል፡፡ እግርኳስ ሳይጫወት ጥሩ አሰልጣኝ የሚሆን አለ፤ ስለዚህ ይቻላል ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የእግርኳስ አሰልጣኝነት የቡድን ሥራ ሆኗል፡፡ ሙያተኞችን አሰባስቦ መሥራት ይቻላል፤ ትልልቅ ክለቦች ሳይጫወቱ ትልቅ አሰልጣኝ የሆኑትን እንደ ጆዜ ሞውሪንሆ ያሉትን እኮ አይተናል፡፡ የራሱን ፍልስፍና ይዞ በመምጣት በአውሮፓ አራት ታላላቅ ሊጎች ሻምፒዮን መቻል የሆነ ሰው ሆኗል፡፡ ይሄ ዝምብሎ የመቧደን ሐሳብ ነው፡፡ እኔ ይህን ተግባር ከኋላ-ቀር አስተሳሰብ ለይቼ አላየውም፡፡ ሰው ከቻለ ቻለ ነው-በቃ፡፡ አንድ ሰው Physics ሳያጠና ጨረቃ ላይ መውጣት ከቻለ- Why not? ገደብ አያስፈልግም፡፡ አንዳንዴ ሙግቱ ራስን ለመከላከል የሚደረግም ይመስለኛል፡፡

በቡድን ሥራ ስኬታማ መሆን የሚችሉ ሰዎች መስራት ይችላሉ፡፡ ድሮ የቴክኒኩን፣ ታክቲኩን፣ አካል ብቃቱን፣ ስነ-ልቦናውን፣ ስነ-ምግቡን ጨምሮ ሁሉንም ነገሮች እኔ ብቻ ነበርኩ የምሰራው፡፡ ያ ውሳኔዬ ስህተት መሆኑን ተረድቼ የተለያዩ ባለሙያዎች አብረውኝ እንዲሰሩ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ አለም ላይ የሚሰራበትን ሁኔታ በማየት ራሴን ለማረም በቅቻለሁ፡፡ ስለዚህ ቡድን የመምራትና የማስተዳደር አቅም ያለው ሰው፣ የ<Leadership Quality> ያለው ሰው፣ ቴክኒሻኖችና ምሁራንን ሰብስቦ ከሰራ ውጤታማ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ተጫወተ-አልተጫወተ አይደለም ቁምነገሩ፡፡ መጫወት ሌላ-መምራት ሌላ፡፡ መጫወት የግል ነው፡፡ መምራት ደግሞ ሰዎችን በአግባቡ ለአንድ ዓለማ ማሰለፍ መቻል ነው፡፡ አንድን ቡድን ወደ ውጤታማነት ማስኬድ ከቻልክ ማነው ባለመጫወትህ የሚከስህ?

ከተጫዋችነት አንስቶ በአሰልጣኝነት፣ ቴክኒክ ዳይሬክተርነት፣ ኢንስትራክተርነት፣ በቴክኒክ ጉዳዮች አማካሪነት እና በአስተዳደርነት የካበተ ልምድ ያለውና ሰፊ ተመክሮዎችን የያዘ ባለሙያ ከሃገሪቱ የእግርኳስ ከባቢ ይህን ያህል ጊዜ መራቁ ተገቢ ነውን?

★ እዚህ ጋር ሁለት ነገሮችን ማንሳት አለብኝ፡፡ አንደኛው እንደተጠቀሰው ከእግርኳስ ተመልካችነት አንስቶ እስከ መጨረሻው ደረጃ ድረስ ሄድኩኝ፡፡ እንዲያውም የቀረኝ የፌዴሬሽኑ ባለስልጣን መሆን ይመስለኛል፡፡ እሱንም መሆን እንደማልችል ተረድቼ ትቼዋለሁ፡፡ ለፕሬዘዳንትነት ለመወዳደር ሞክሬ ነበር፤ ሊያስገቡኝ አልቻሉም፤ እንዳይሳካ ያደረጉት ደግሞ በትውልድ አካባቢዬ ያሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በእርግጥ ለምን እንዳልመረጡኝ አላውቅም፤ ነገርግን ስላልፈለጉኝ ምርጫቸው አልሆንኩም፤ ስለዚህ ካልፈለጉኝ ‘እኔም አልፈልጋቸውም፡፡’ አልኩና ተውኩት፡፡ እንደ ተንታኝም ሆኛለሁ፤ አሰልጣኝ፣ ተጫዋች፣ ተመልካች፣ የክለብ መሪም ነበርኩ፡፡ በቴክኒክ ኮሚቴነት ለመስራት ፌዴሬሽን ገብቼ የነበረበት ጊዜም ነበር፡፡ በወቅቱ ለብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የምልመላ ሥርዓቱን አየሁና ‘እንዲህ ነው ለካ!’ ብዬ እሱንም ትቼ ወጣሁ፡፡ የሚገርመው ባልመረጥኩት እንድፈርም ትዕዛዝ ተሰጠኝ፡፡ “ፈርም!” ተባልኩ፡፡ ያልተስማማሁበትን ‘አሻፈረኝ!’ አልኩ፡፡ ‘አልፈርምም፡፡’ በእኔ ፊርማና ስምማ ይሄ ሰውዬ አይመረጥም፡፡’ ብዬ በአቋሜ ጸናሁ፤ ራሴንም ከኃላፊነት አገለልኩ፡፡ ከዚያ በኋላ አልተመለስኩም፡፡ ሁለተኛው ‘የኢትዮጵያ እግርኳስ ችግር ያለው ችግኝ የማፍላቱ ሥራ ላይ ነው፡፡’ የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ በዚያ መስክ እጅግ ደካሞች ነን፤ ውድቀቱ ደግሞ የዚያ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ‘ ችግኝ ማፍላቱ ላይ ማተኮር ይሻላል፡፡’ አልኩና ወደ አካዳሚ ሥራ ገባሁ፡፡

አሁን በህጻናት ሥልጠና ላይ ነኝ፡፡ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራበት ለሃገሪቱ የእግርኳስ ችግር መፍትሄ መሆን የሚችል ነው፡፡ በሌሎቹ ዓለማት በእግርኳሱ ያደጉ ሃገራት የሚሰሩበትን ሥራ እኔም እየሰራሁበት ነው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ የነበረውን በሜዳ ችግር ዘግቼዋለሁ፤ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ድጋፍ አግኝቼ እዚያ በከፈትኩት አካዳሚ ወደ ሁለት መቶ ህጻናት ተገቢ ሥለልጠና እየተከታተሉ ይገኛሉ፤ አዲስ ስለሆነም ይመሥለኛል የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ደረጃ የሚሰጠው ነው፡፡ የከተማው ትልቁ ቡድን ውጤታማ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ሊሆን ይችላል የሰዉ ፍላጎት ጨምሯል፡፡ እግርኳሱ ላይ ከፍተኛ መነሳሳት ይታያል፡፡ እኔ የጠፋሁት ከኢንስቲቱሽኑ አካባቢ እንጂ ከእግርኳስ አልተለየሁም፤ ፈጽሞም አልለይም፤ ሞት ብቻ ነው ከእግርኳስ የሚለየኝ፡፡

በእግርኳስ አመራሮች በኩል የአሰልጣኞች መመዘኛ መስፈርቶች ውስን የሚሆኑበት ምክንያት ምንድን ይመስልሃል?

★ እሱ ከባለቤትነት ጥያቄ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ክለቦች በአብዛኛው የድርጅት ናቸው፡፡ ኳስ የሚወዱ የድርጅቶቹ መሪዎች ክለቦቹን ይመሯቸዋል እንጂ በስፖርት አመራርነት የተማረ፣ ልምድ ያለው፣ አንድን የእግርኳስ ቡድን ለውጤት ለማብቃት የሚጥር ባለሙያ አይመደብም፡፡ በስሜትና በደመነፍስ ብቻ ክለብ የሚመራው አካል ደግሞ እንዲሁ የፌዴሬሽን አመራርን በተመሳሳይ መንገድ ይመርጣል፡፡ ስለዚህ ድንብርብር የእግርኳስ ከባቢ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ ፌዴሬሽን ይነሳል እንጂ ለእንዲህ አይነቱ ችግር ክለቦችም ቀጥተኛ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ፌዴሬሽኑ ውስጥ ያሉት ሰዎች እኮ የተመረጡት በክለቦች ነው፡፡ የራሳቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሳይወጡና ሥራቸውን አጥርተው ሳይሰሩ ጣታቸውን ወደ ፌዴሬሽኑ ሲጠቁሙና የተቋሙን ዝርክርክ አሰራር በምክንያትነት ሲያነሱ እናያለን፡፡ እግርኳሱን የሚያስተዳድሩ አካላት ስንልም ይህንኑ ፌዴሬሽን ብቻ ሳይሆን በየእርከኑ ያሉ የአመራር አካላትንም ጭምር ነው፡፡ በእግርኳስ ማህበሩ ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች የክለቦች ምርጫ ውጤት ናቸው፡፡ ተመራጩ ደካማ አመራር ከሆነም የሚጠየቁት፥ ጠንካራ አመራር ከመረጡም የሚወደሱት ክለቦች ይሆናሉ፡፡ እናም ትልቅ ትኩረት መደረግ ያለበት እዚህ ላይ ይመስለኛል፡፡ ፌዴሬሽናችንማ በእቅድ እግርኳሱን ለመምራት ይቅርና በቅጡ እንኳ ውድድሮችን ማስኬድ አልቻለም፡፡ የአምስትና የአስር ዓመት ዕቅድ አውጥቶ በትልልቅ ውድድሮች የመሳተፍ ትልም ቀርቶ እጁ ላይ ያሉ ውድድሮችን በአግባቡ መምራት አልሆነለትም፡፡

በእግርኳሳችን በዕቅድ የመመራት፣ በዕቅድ የመሰልጠንና በዕቅድ የመወዳደር መርህን መሰረት አድርገን መሥራት ለምን ዳገት ሆነብን?

★ የእግርኳስ ችግራችን በጥልቀት ካለመረዳት የመነጨ ይመስለኛል፡፡ የችግሮቻችን ጥናቶች እንኳ የሚሰሩት በማን ነው? የዓለም እግርኳስ አካሄድን የሚያውቅ ነው? አይደለም? አንድ ምሁር በእግርኳስ ፒ.ኤች.ዲ. ስላለው ብቻ የኢትዮጵያን እግርኳስ ችግር አጥንቶ ለውጥ ያመጣል ማለት አይደለም፡፡ በቅድሚያ የእኛን (አሰልጣኞች) ችግር ለመረዳት ጥናቱን ማጥናት ያለባቸው ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሰዎች መሆን አለባቸው፡፡ የፕሮፌሽናል እግርኳስ እውቀት ያላቸውና በዚሁ ሥራ ላይ የተጠመዱ ባለሙያዎች ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ አንድ ሰው በስፖርት ሳይንስ PHD ሲኖረው በፊዚዮሎጂ፣ በስነ ምግብ አልያም በእግርኳስ አስተዳደር ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ አጥኚዎቹ ተግባራዊ ልምድ የላቸውም፡፡ ቲዎሪ ደግሞ ወደ ተግባር ሊቀየር የሚችልበት አቅም ያስፈልጋል፡፡ ይህን የሚያሟላ የሰው ሃይል የለንም፡፡ እስኪ የእግርኳስ ደረጃቸው ጣራ የነኩትን ሃገራት ተመክሮ እንይ- ጀርመንን በምሳሌነት እናንሳ፡፡ እግርኳሳቸው ቁልቁል ሲወርድ አንድ ጥናት ያስጠናሉ፡፡ “ወጣቶቻችንን ላይ አልሰራንም፤ ተጫዋቾቻችን አርጅተዋል፤ ስለዚህ የአስር ዓመት እቅድ እናውጣ!” ብለው እነ ኦዚልን አፈሩ፡፡ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆኑ፡፡

እኛም በአስተዳደሩ፣ በፋይናንሱ፣ በስልጠናው፣ ….. በሌሎችም ዘርፎች የሚሰሩ ብቁ ሰዎችን ማምጣት መቻል አለብን፡፡ ቴሌን እንመልከት፦ ድርጅቱን ማስተዳደር ከሰዎቻችን አቅም በላይ ሲሆን ከውጭ ባለሙያዎች መጡ፤ አመራር ቦታው ላይ ተቀመጡ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ትልቅ ለውጥ መጣ፡፡ እግርሳችንንም ለውጥ እስኪያገኝ መታገል ይጠበቅብናል፡፡ ሃገራችን እስካሁን የፕሮፌሽናል እግርኳስ ባለሙያ አላፈራችም፤ አንድ ፕሮፌሽናል ተጫዋች መፍጠር ያቃተን ሰዎች ነን፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በተሰራ ጥናት ጋና ሶስት መቶ ስልሳ አምስት የተመዘገቡ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ነበሯት፡፡ አሁን ቁጥሩ ጨምሮም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ዘርፍ ከአፍሪካ የምትመራው ከአምስት መቶ በላይ ፕሮፌሽናሎችን ያስመዘገበችው ናይጄሪያ ናት፡፡ አፍሪካን ተሻግሮ በአውሮፓ የሚጫወት አንድ ተጫዋች የለንም፡፡ በእርግጥ ቢንያም በላይ በአልባኒያ እየተጫወተ ነው፡፡ ግን የሃገሪቱ እግርኳስ ደረጃ ምን ያህል ያደገ ነው? ልምዱ ለቢኒያም ጥሩ ቢሆንም እኛን እንደ ሃገር የሚያኩራራን ቁጥር አይሰጠንም፡፡ ከአመታት በፊት አንተነህ ፈለቀ ተጫዋች እያለ ጀርመን ለሙከራ ሄደ፤ ሲመጣ አንድ ጋዜጣ ላይ” አንችልም፤ እግርኳሳችን ኋላ-ቀር ነው፡፡” የሚል አስተያየት ሰጠ፡፡ እውነት ተናግሯል፡፡ በአካል ብቃትም፣ በቴክኒክም በታክቲክም ብዙ ይቀረናል፡፡  እኔ በራሴ እኮ አውቀዋለሁ፤ ያለኝ ውስን እውቀት ነው፡፡ ከእኔ ጋር የሚሰሩትን ኢንስትራክተሮችንም አውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም እውቀታቸው ውስን ነው፡፡

በአጠቃላይ በእግርኳሳችን ዙሪያ ያለው ውስን እውቀት ነው፡፡ አንዳንዶች የእግርኳስ እውቀትን በPHD እና በሁለተኛ ዲግሪ ይመዝኑታል፡፡ ቁም ነገሩ ያ አይደለም፡፡ እነ ፕላቲኒና ኢንፋንቲኖ የእግርኳስ ትምህርት አጥንተው ነው እንዴ እንዲህ ታላላቅ መሪዎች የሆኑት? አይደለም፡፡ ጥሩ ልምድና የመምራት ብቃት ስላላቸው መጠነኛ ኮርሶችን ወስደው አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በእኛ ሃገር ዩኒቨርሲቲ ያሉት የስፖርት ምሁራን ስለ አካዳሚ ጉዳዮች እንጂ እግርኳሱን ጠንቅቀው ያውቃሉ ብዬ አልገምትም፡፡ ጥናትና ምርምር ማካሄዳቸው ጥሩ ነው፡፡ የጥናታቸው ውጤት ግን እግርኳሳችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሰዋል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ሊሞግቱኝ ይችላሉ፤ ዝግጁ ነኝ፡፡ እኔም ለመናገር፣ ከተሳሳትኩም የእነርሱን ለማድመጥ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ “እናንተ አታውቁም፤ እኛ ነን የምናውቅላችሁ፡፡” የሚለው የሚያዋጣ አልመሰለኝም፡፡ የፕሮፌሽናል እግርኳስ ልምድና እውቀት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ እግርኳሳችን ይህንን አቅጣጫ የሚያመላክተው ባለሙያ ይሻል፡፡

ሁሉንም የእግርኳስ ችግሮቻችን ምንጭነት ለፌዴሬሽን የመስጠት፣ ለሁሉም የእግርኳሳችን ችግሮች መፍትሄንም እንዲሁ ከፌዴሬሽኑ የመጠበቅ ልማዳችን መቼ የሚቆም ይመስልሃል?

★ ሁላችንም ሰከን ስንልና ራሳችንን ማወቅ ስንጀምር፡፡ እኔም ራሴ ስሳሳት ነበር፡፡ በቅርቡ ነው ሁኔታዎች ግልጽ እየሆኑ የመጡልኝ፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ችግሮች እየጎሉ ሲመጡ ‘እነዚህን የፌዴሬሽን ሰዎች ማን መረጣቸው? ለመሆኑ ክለቦቹ ለምንድነው ጣታቸውን ወደ ፌዴሬሽኑ የሚጠቁሙት? ራሳቸው የመረጧቸው አመራሮች አይደሉም እንዴ?’ እያልኩ መጠየቅ ጀምሬአለሁ፡፡ ክለቦች ፌዴሬሽኑን የሚያስተዳድሩ አካላት እንዲሾሙ ምን ያህል ገንዘብ እንዳፈሰሱ ታውቃላችሁ፡፡ ትልልቆቹ ክለቦች ሳይቀሩ በየክልሉ እየዞሩ ተመራጮችን ለመያዝ ስንት ሲለፉ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ እኔም ለመመረጥ የራሴን ጥረት አድርጌያለሁ፤ ገና ሳልጀምር ነው የተቀጨሁት፡፡ ለምን? ቲፎዞ የለኝማ! ቲፎዞ ያልኩት በጎ ድጋፍ አድራዎችን አይደለም፡፡ በቃ-<ኔትወርኩ> ውስጥ የለሁበትም፡፡ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ የፌዴሬሽን ምርጫ በ<ኔትወርክ> እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ የአመራረጥ ሒደቱን በሚገባ ተረድቻለሁ፡፡ በእርግጥ ከዚያ በፊትም ጥርጣሬ ያድርብኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ግልጽ ሆነልኝ፡፡ሃገሪቱ ሳትቀጣ በፊት የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኜ ተሾምኩ፤ ሆኖም ቡድኑ ጨዋታዎችን ስለማያደርግ በፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ክፍል እንድሰራ ተመደብኩ፡፡ ያኔ ምርጫው ገና ሳይጀመር ማን የፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት እንደሚሆን ከሶስትና አራት ቀናት በፊት አውቅ ነበር፡፡ እንዲያውም ሰውየውን ሁሉ አግኝቼ አብሬው አምሽቻለሁ፡፡ ይህ አይነቱ ልምድ ያለኝ ሰው ስለሆንኩ የኢትዮጵያ እግርኳስ ውድቀት አያስገርመኝም፡፡

ጣታችንን ወደ ፌዴሬሽን የምንጠቁመው ራሳችንን ስለማናውቅ፣ ረጋ ብለን ግራ-ቀኙን ማየት፣ መመራመር፣ መረዳት፣….. ስላልቻልን ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ራሱን ‘እኔ ምን ሰራው?’ ብሎ ቢጠይቅ ለራሱ ኃጢያቱን የማየት አጋጣሚ ይሰጣል፤ ያኔ ንስኃ የመግባት ዕድልም ያገኛል፡፡ የየክለቦቻችን መሪዎች መጀመሪያ ንስኃ መግባት አለባቸው፡፡ ጋዜጠኞችም ጭምር፡፡ ‘ለዚህ ሃገር የእግርኳስ ዕድገት ምን አስተዋጽኦ አደረግሁ?’ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እውነት መናገር አለብን፤ ከራሴ ጀምሮ፡፡ እኔም ብዙ ነገሮችን አበላሽቻለሁ፤ በእርግጥ ‘ሆን ብዬ ነው፡፡’ በማለት አስቤ አላውቅም፡፡ ነገርግን እንደዚያ የሚመስለኝ ጊዜ አለ፡፡ ማንም አውቆ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለመጉዳት የሚነሳ አይኖርም፡፡ ” የእኔ ብቻ ነው ትክክል፡፡” ማለትም ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ ሁላችንም ውስጣችንን እንፈትሽ፡፡ “ምሩኝ!” ብሎ መርጦ መልሶ አድማ ማድረግ ምንድን ነው? ሌላው እዚያው ፌዴሬሽኑ ውስጥ ለረጅም ዓመት የኖሩ ሰዎች “ለምንድነው ለውጥ ያልመጣው?” ብለው ራሳቸውን ይጠይቁ፡፡ ዝም ብሎ እድሜ ብቻ ማስቆጠር ትርጉሙ ምንድን ነው? ነገ’ኮ እናልፋለን፡፡ ለውጥ የማላመጣ ከሆነ ለምን እዚያ ውስጥ እንቦጫረቃለሁ? እኔ ያንን አስቤ ነው የወጣሁት፡፡ ሁሉም እዚያ አካባቢ ያለ ሰው እንደዚያ ቢያደርግ ጥሩ ነው፡፡ ሰላሳና አርባ ዓመታት እዚያው የሚንቦጫረቅ አለ፤ ያለ ለውጥ ከክለብ ክለብ እየዞረ ክለብ የሚያስተዳድር አለ፡፡

የክልል ፌዴሬሽኖችን የመሩ፣ ክለቦችን የመሩ፣ ዋናውን እግርኳስ ፌዴሬሽን የመሩ፣…..እነዚህ ሰዎች ለእግርኳሱ ለምን አያስቡም? ማሰብ አቃታቸው ወይስ ሆዳቸው ነው የሚመራቸው? እዚህ ጉዳይ ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ፡፡ አሁንም ያለውን መበጣበጥ የሚመሩት እነዚሁ አካላት ናቸው፡፡ በደርግ ጊዜ የነበሩ፣ አሁንም ያሉ ናቸው፡፡ ለህዝቡ ሲሉ “ምን ፈየድን?” ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው፡፡ ተመልካቹ እኮ በእግርኳስ ውጤት ናፍቆት እየሞተ ነው፡፡ ጥሩ የአየር ንብረት ስላለ ሃገሪቱን የእግርኳስ ማዕከል አድርጎ የአውሮፓ ክለቦችን ማምጣት እየተቻለ- ነገር ግን አልተሰራም፡፡ የአስራ ሶስት ወር ጸጋ (Thirteen Months of Sunshine) የታደልን ነን፤ ከባህር ጠለል በላይ ባለን ከፍታ (High Altitude) ተጠቅመን እዚሁ ክለቦች ከሌሎች ዓለማት  እየመጡ ልምምድ እንዲያደርጉ እስከ ማሰብ መቻል አለብን፡፡ የእግርኳስ መሪዎቻችን በስፖርቱ ግዙፍ ኢንደስትሪ ያላት ሃገር እንድትሆን ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ ነበረ፡፡ ግን እነርሱ ገና የመንደር መቆራቆስ ላይ ናቸው፡፡ የእገሌ ቡድን-የእገሌ ቡድን በመባባል ላይ ይገኛሉ፤ ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ መቆርቆር አቅቷቸዋል፡፡ እስቲ ቆም ብለው ያስቡ- ነገ ምን አይነት ስም ትተው ነው የሚያልፉት? በሃሳብ ትግል ውስጥ ሳንገባ ሁልጊዜም እየተቧደንን አንዱ ሌላኛውን ለማጥቃት የምናልም ከሆነን አሁንም ለውጥ አናመጣም፡፡

በቅርቡ እየሰማሁ ያለሁት ነገር ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ “ሊግ ያስፈልጋል? አያስፈልግም?” ክርክር ላይ ናቸው፡፡ ይሄ ራሱን የቻለ አጀንዳ ስለሆነ እዚህ ላይም መነጋገር አለብን፡፡ በቅርቡ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ቀርቤም ‘ለምን?’ ብዬ ተቃውሜያለሁ፡፡ ሊጉ ምን አደረገን? “…..ሊጉ ስለመጣ ነው፡፡” ምን ማለት ነው? ሊግ እኮ በየትኛውም ዓለም ያለ የውድድር ፎርማት ነው፡፡ የዛሬ ሃምሳ ዓመትም በኢትዮጵያ የሊግ ውድድር ይካሄድ ነበር፡፡ ሊጉ ሳይሆን እኛ ነን ያጠፋነው፡፡ ጋና ሊግ አለ፤ ብራዚል ሊግ አለ፡፡ በዚህ ርዕስ ላይ ጋዜጠኞች የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ ህዝቡ ሊጉን ደካማ አድርጎ እንዲያይ ሆኗል፡፡ አሰራሩ እንጂ ደካማ የሊጉ ሲስተም አይደለም፤ ሰዎቹ እንጂ ደካማ ሊጉ አይደለም፡፡ በፕሮፌሽናሎች የሚተዳደር ሊግ ብናስቀምጥና በህግ ብንመራ ሊጋችን ቀጥ ብሎ ይሄዳል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በህግ የሚመራ ህዝብ ነው፡፡ ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ ሃይማኖተኛ ነው፡፡ ከህግ ወጣ ያለ ሰው ሊኖር ይችላል- ያንን በህጉ መሰረት መቅጣት ነው-በቃ፡፡ አሁን የመጣው ነገር አልገባኝም- ሊጉን ለማፍረስ መሯሯጥ ማን ማለት ነው? በዚህ ጊዜ የህዝብ ቡድኖች ተፈጥረዋል፤ በህግ አግባብ ከተመሩ ትልልቅ ክለቦች ይሆናሉ፡፡ ጎንደር ትልቅ ክለብ ተፈጥሯል- ህግ ነው የሚገዛው፤ መቐለ ትልቅ ክለብ ተፈጥሯል-እዚያም እንደዚያው ፤ ጅማ ትልቅ ክለብ ተፈጥሯል-ተመሳሳይ ነው፤….. ሙሉ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያቅፍና የሚያንቀሳቅስ የእግርኳስ ከባቢ ይሻላል? ወይስ በየክልሎች የተማከለ እግርኳስ መምራት ይሻላል? የትኛው ነው የሚያሳድገን? ከሥር ያለው ሲስፋፋ አይደለም እንዴ ከላይ ጥሩ ውጤት ሊመጣ የሚችለው? ሊጉ አይደለም ድክመታችን-ሰዉ ነው፡፡ አስተሳሰባችን ነው- አመለካከታችን ነው ደካማ ጎናችን፡፡ ድክመታችንን በሊጉ አናሳብብ፤ እኛ አርቀን ማሰብ አልቻልንም፡፡ ‘የእንግሊዝ እግርኳስ እንዴት ይመራል?’ እንናገራለን-በተግባር ግን ማሳየት አልቻልንም፡፡

በሃገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ክልሎች ያለው የአጨዋወት ሥልት ይለያያል፤ የደቡቡ እግርኳስ የአካል ብቃትን ያሟላ ነው፤ ወደ ሰሜን ስንሄድ  ደግሞ ወጣቶቹ ቴክኒክ ላይ ጥሩ ናቸው፡፡ ይህንን አቀናጅተን ጥሩ የእግርኳስ ሥራ መስራት ይቻላል፡፡ ወደድንም ጠላንም እግርኳስ ኃይል ያስፈልገዋል፤ ስለዚህ “እንዴት እንስራ?” የሚለው ላይ ነው ማተኮር ያለብን፡፡ ‘እግርኳሳች ውበት እንዲኖረው ምን እንስራ? ሊጋችንን በምን መልኩ ውጤታማ እናድርገው?’ መጠየቅ የሚገባን ይህንን ነው፡፡ እንጂማ “ሊጉ አይረባም!” ተብሎ ከሃያ ዓመት በኋላ “እናፍርሰው፡፡” አያዋጣንም፡፡ ይህ ውሳኔ ከሃምሳ ዓመታት በፊትም ተወስኖ ነበር፡፡ ለምንድን ነው ታሪክ እየደጋገምን ወደ ውድቀት የምናመራው? ያኔ እነ ሓማሴን፣ አካለ ጉዛይ፣ እንደርታ፣….. ጥሩ አድገው ነበር፡፡ ከዚያ “ስማችሁን ቀይሩ!” ተባሉ፡፡ የኢትዮጵያን እግርኳስ ታሪክ በሚያወሳ መጽሄት ላይ ተጽፏል፤ ላሳያችሁ እችላለሁ፡፡ ለምሳሌ፦ እንደርታ ትልቅ ቡድን ነበር፡፡ የከተማውን ህዝብ ከዳር-ዳር አነቃንቆ ሰፊ ድጋፍ አግኝቷል፤ አባቴ የቡድኑ አባል ሆኖ መዋጮ አዋጥቷል፡፡ ስለ እግርኳስ ምንም የማያውቅ ነጋዴ ነበር፡፡ ” አባል ሁን፤ ክፍያም ክፈል፡፡” ተባለ- ይከፍላል፤ በሚችለው ሁሉ ቡድኑን መደገፍ ጀመረ፡፡ እኔም እንደርታ የገባሁት አባቴ ባደረገልኝ አስተዋፅኦ ነው፡፡ ትልልቆቹ ወንድሞቼም የእንደርታ ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ ህዝብ ይህንን ታሪክ ያውቃል፡፡ ነባር ታሪክ የያዘ፣ <Community-Based> የሆነ፣ ህዝብ ያቀፈው፣… ቡድን ነበር፡፡

አሁን ያለው የፖለቲካ ድባብ’ኮ ያልፋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲያልፍ ምን ልንል ነው? እስቲ የባህርዳር ከተማን ቡድን እንይ- በባህርዳር ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ያፈራ ክለብ ሆኗል፡፡ በሌሎችም ክልሎች እንዲሁ ነው፡፡ ክለቦቻችን ህግና ሥርዓት እንዲያከብሩ ማድረግ ነው ዋናው መፍትሄ፡፡ ስለ ሙያው ከልቡ በሚያስብ ጠንካራ አመራር ታግዘን ሊጋችንን <ፕሮፌሽናል ሊግ> ብናደርገው ውጤታማ እንሆናለን፡፡ ሌላው ችግራችን <አማተሪዝም> ስለነበር ባህላዊ አሰራር ለምደናል፤ ሁሌም በእዚያ ሁኔታ መቀጠል እንፈልጋለን፡፡ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ እግርኳሳችን በራሱ “ወደ <ፕሮፌሽናል> መንገድ ላምራ፡፡” እያለን ነው፡፡ ማን ወደዚያ ጎዳና ያሻግረው? መላሽ የለም፤ እውቀት ጠፍቶናል፡፡ እግርኳሳችን “ልውጣ፤ ልደግ!” ሲለን “አይ አትወጣም!” እያልነው ነን፡፡ በአሁኑ ጊዜ <ፕሮፌሽናል የእግርኳስ ሊግ> ለመመሥረት አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ አንደኛው ገንዘብ ነው፡፡ በእግርኳሱ ዙሪያ 2.2 ቢሊየን ብር ተንቀሳቅሷል፤ እናስተውል- ቁጥሩ ከሚሊዮኖች አልፎ ወደ ቢሊየን ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ የ”ትናንቶቹ” ክለቦች ትልልቅ ስታዲየሞች ይዘው መጥተዋል፡፡ እኛ ሃያ ሺህ እና ሰላሳ ሺህ ነበር የለመድነው፡፡ አሁን ግን ባህር ዳር ስድሳ ሺህ፣ መቐለ ስድሳ ሺህ፣ ወልዲያ፣ ሐዋሳ፣ ነቀምቴ፣… ስታዲየሞችን ገንብተው ሃገራዊ እግርኳሱን እያስፋፉት ይገኛሉ፡፡

በመሃል አዲስ አበባ የሁለትና ሶስት ክለቦች ብቻ የነበረው እግርኳስ አሁን የሁሉም ሆኗል፡፡ የባህርዳር፣ ጎንደር፣ መቐሌ፣ ሽሬ፣ ሐዋሳ፣ ወላይታ፣ …..ሰው “ይመለከተኛል!” እያለ ነው፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው ይህን ሁኔታ ያልሆነ ሥም የምንለጥፍበት? አስተካክለንና ጥሩ አድርገን ከመራነው ውጤታማ እግርኳስ ይኖረናል፡፡ ቡናና ጊዮርጊስ ብቻ እያልን በሁለት ቡድኖች ላይ ብቻ ተቸክለን አንኖርም፤ እነርሱም ካልቻሉ ጥግ ይይዛሉ፤ ከቻሉ ይሄዳሉ፡፡የውድድር ዓለም ላይ ነው ያለነው፡፡ “ስለ እነዚህ ክለቦች ብቻ ነው የምናስበው፡፡” ካልን አስተሳሰባችን በእነርሱ አድማስ ውስጥ ብቻ ይሆናል፡፡ እነዚህ ክለቦች ሰማንያ ዓመት ሙሉ ምን ለውጥ አመጡ? ስታዲየሞችን ሰሩ ወይ? አንድ ልጅ እንኳ አፍርተው ለእነ አርሰናል አይነት ክለብ አበቁ ወይ? ለእነ ሊቨርፑል ሸጡ ወይ? ‘አልቻሉም!’ ስለዚህ አካሄዳቸው ልክ አልነበረም ማለት ነው፡፡ አስተሳሰባቸውን መለወጥ አለባቸው፤ <ሲስተም> ላይ መንጠላጠል ይቅር፡፡ ‘እኛ ነን ወይስ ሲስተሙ ነው ችግራችን?’ ጋዜጠኞችም በዚህ ርዕስ ላይ በሰፊው ማወያየት ይጠበቅባችኋል፡፡ እኔ የማንም ክለብ ደጋፊም ተቃዋሚም አይደለሁም፤ የማንንም ሐሳብ አከብራለሁ፤ የእኔ ሐሳብ እንዲደመጥ ደግሞ እፈልጋለሁ፡፡ የታሰበው የውድድር ፎርማት ለእኔ የወረደ አስተሳሰብ ውጤት ነው፤ የድክመት ምንጭ ነው ብዬ አስባለሁ፤ይህንን ሐሳብ በሚያራምዱ ሰዎችም በጣም አፍራለሁ፡፡ አለም እየሄደ ያለበትን አሰራር ትተህ በራሴ ጎዳና ልሂድ ማለት ከዓለም ውድድር መውጣት ማለት ነው፡፡ በአንድ ወቅት ብሄራዊ ቡድናችን ሞሪታኒያ በምትባል ሃገር የክላሽን መሳሪያ በጫኑ መኪኖች ታጅቦ ከአየር ማረፊያው እስከ ሆቴላችን ድረስ ሄደናል፤ ጦርነት ስለነበር ተከበን ነው ወደ ማረፊያችን የደረስነው፡፡

የትም ቦታ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላል፤ ‘እንዴት ይፈታሉ?’ የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ ‘ችግሮቻችንን ፈትተን ያለውን የሊግ ፎርማት እንዴት ሰላማዊ እናድርገው?’ በሚለው ሐሳብ ላይ ነው መወያየት ያለብን እንጂ በመሸሽ የመፍትሄ አካል ልንሆን አንችልም፡፡ መሸሽ መፍትሄ አያመጣም፡፡ ከእነዚህ ቡድኖች የወደድኩት በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ <Challenging Environment> ፈጥረዋል፡፡ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ሆነ ኢትዮጵያ ቡናን የሚያንቀጠቅጡ ሆነዋል፡፡ ለምን? በርካታ ደጋፊ አላቸው፤ ገንዘብ አላቸው፡፡ ወደ እግርኳሳችን አቅም ይዘው መጥተዋል፡፡ ይህን አቅም ይዘው ሲመጡ ግን ረብሻ ተፈጠረ፡፡ ስለዚህ ረብሻውን ” ይሄ ረብሻ አይጠቅመንም፡፡” ብሎ መከላከል አልያም ማቆም፡፡ ረብሻው የመጣው ህግን ማክበር የሚችል አካል ስለሌለ እንጂ እነርሱ ረባሾች ስለሆኑ አይደለም፡፡

ቡድኖቹ ራስን በራስ የማስተዳደር የክለብ ቁመና ኖሯቸው ያገኙት አቅም ሳይሆን በበጀት መልክ ከመንግስት ካዝና ከሚወጣ ገንዘብ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ እናገንዘብ አላቸው፡፡ሊባልላቸው ይችላል እንዴ

★ የክልሉ መንግስት “እችላለሁ!” ካለ እዚህ ያለው ሰው ምን አገባው? እውነት ለመንግስት ታስቦ ነው? ወይስ ለምን ቡድኖቹ ሃብታም ሆኑ ተብሎ ነው? እኔ ይህንን አስተያየት በበጎ ጎኑ አላየውም፡፡

ሒደቱ እኮ ጥሩ የውድድር መንፈስ አይፈጥርም፡፡ በራሳቸው መንገድ ገንዘብ የሚያመነጩ ክለቦች እና ትርፍ ሳይጠበቅባቸው ከግብር ከሚሰበሰብ ብር በጀት በሚመደብላቸው ክለቦች መካከል እንዴት ነው ፍትሃዊ ውድድር የሚደረገው

★ ሥጋታቸው’ኮ ይገባኛል፡፡ ግን ጥያቄው “በጎ የሆነ ሥጋት ነው ወይ?” የሚለው ነው፡፡ እኔ እጠራጠራለሁ፡፡ በዚህ አለም ላይ ሁልጊዜ ማንም የበላይ ሆኖ አይኖርም፤ ጊዜው የወድድር ነው፡፡ ቡድኖቹ በሚመቻቸው መንገድ መጥተዋል፡፡ “በቀጣይ ይህን ችግር እንዴት እናስተካክለው?” አንድ እልባት ነው፡፡ ” የመንግስት ገንዘብ ተጠቅመዋል፡፡” የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ መድን፣ መብራት ሃይል፣መከላከያ፣… የማንን ገንዘብ ነበር የሚጠቀሙት? ቡና የማንን ገንዘብ ነው ሲጠቀም የነበረው? ብር እየተዋጣለት አልነበረም እንዴ? ቅዱስ ጊዮርጊስ የመንግስት ክለብ አልነበረምን? ፋብሪካው የመንግስት፣ተጫዋቾቹስ የመንግስት ተቀጣሪ አልነበሩም? ይህ በጎ አመለካከት አይመስለኝም፡፡ ይልቁንስ “ሰላማዊ የእግርኳስ መድረክ እንዴት እንፍጠር?” በሚለው አብይ ጉዳይ ላይ እናተኩር፤ ከዚያ በኋላ “ክለቦች የገንዘብ ምንጫቸው ምንድን ነው? በምን መልኩ ወደ <ፕሮፌሸናል ክለብ>ነት ይቀየሩ?” የሚለውን ለመፍታት እንጥራለን፤ ይህንን አስተሳሰብ ነው ማራመድ ያለብን፡፡

ለምሳሌ፦ የሐዋሳ ከንቲባ “ገንዘብ አለን፡፡” ብሎ ቢያስብ፣ ውሳኔው የህዝብ ድጋፍና ፈቃድ ቢያገኝ እዚህ አዲስ አበባ ያለው ህዝብ “ኧረ የሐዋሳ ህዝብ ገንዘብ ነው እየወጣ ያለው፡፡” ብሎ የሚሟገትበት ምክንያት ይኖረዋል? ስትበለጥ ” የህዝብ ገንዘብ እየባከነ ነው፡፡” ብለህ መበለጥህን ለማስቆም ካሰብክ ትክክል አይደለም፡፡ ነገሩ ትክክለኛ አስተሳሰብ ሳይሆን ስጋት ነው፡፡ ስለዚህ ክለቦቹ “ስጋቱን እንዴት እንቋቋመው?” ብለው ነው ማሰብ ያለባቸው፡፡ የክልሎቹ ክለቦች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አላቸው፤ የአዲስ አበባዎቹ ክለቦች ያላዩትን ማለት ነው፡፡ ሐዋሳ ፤ጅማ፣ መቐለ፣ ባህርዳርና ፋሲል ይህንን በተግባር አሳይተዋል፡፡ ይህን ሁሉ ደጋፊ የያዘ ክለብ “ገንዘብ ያጣል፡፡” ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በዚህች ሃገር እናይ የነበረው የሁለት ክለቦችን መለያ ነበር፡፡ የአርሰናል አልያም የማንችስተር ዩናይትድ-አልፎአልፎ የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና፡፡ አሁን-አሁን ግን የአስራ ስድስት ክለቦች መለያ እየተሸጠ- ህዝብም ያን መለያ ለብሶ እያየን እንገኛለን፡፡ ይህ በጎ ጅማሬ ነው፡፡ “በትክክል ይሸጣል? አይሸጥም?” ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ክለቦቹ ራሳቸውን ፈትሸው የገበያውን ሥርዓት ያስተካክሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ይህንን ታሪክ በኢትዮጵያ ለማየት በቅተናል፡፡ የጎንደር ልጅ ነጭና ቀይ መለያ ለብሶ አዲስ አበባ ላይ ፋሲልን ሲደግፍ ተመልክተናል፤ ልክ እንደ አውሮፓ፡፡ የመቐለ ልጅም ድሬደዋ እየሄደ መቐለ ሰብዓ እንደርታን ሲደግፍ አይተናል፡፡ ይህን በጎ ጅምር እንዴት ነው የምንቃወመው? የመቐለ ሥራ አስኪያጅ እንደነገረኝ ክለቡ ዘንድሮ ከስታዲየም ገቢ ወደ አስራ ስድስት ሚሊየን ብር አግኝቷል፡፡ ጊዮርጊስና ቡና ይህን ያህል ገንዘብ አግኝተው አያውቁም፡፡ እነዚህ ክለቦች ” እንዴት አድርጌ የገቢ መጠኔን ላሳድግ?” ብለው ለምን አያስቡም፡፡  መቐለ በሚቀጥለው ዓመት ሃያ አምስት ሚሊየን ብር ገቢ ለማድረግ አቅዷል፡፡ እርግጠኛ ነኝ-ያሳኩታል፡፡ ምክንያቱም እጅግ ተነሳስተዋል፡፡ ህዝቡ “ክለቡ መገለጫችን ነው፡፡” ብሎ መነሳሳት ፈጥሯል፡፡ በእርግጠኝነት በጎንደርም ፋሲል ያደርገዋል፤ ባህርዳርም እንዲሁ፡፡ ” በዚህ ፈታኝ ከባቢ ላይ የበላይነታችንን እንዴት እናሳይ? ለኢትዮጵያ እግርኳስ እድገትስ እንዴት እንጠቀመው? እንደ በጎ ግብዓትና ጸጋ ወስደነው እንዴት እናስተካክለው?” ብለን ብናየው፣ እኔም ባማክራቸው በጣም ደስ ይለኛል፡፡ “እንገነጣጠል” ግን ወደ ውድቀት ይመራናል፤ የውድቀቱ ጥንስስ ደግሞ ከመሪዎቹ ይጀምራል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት አስራ ስድስቱ ክለቦች ሰብሰብ ይበሉ፤ ይወያዩ፤ ይነጋገሩ፡፡ እስካሁን ተገነጣጥሎ የተመቸው ሃገር አላውቅም፡፡

ሰፊ የቆዳ ስፋትና ከመቶ ሚሊየን በላይ ህዝብ ባላት ሃገራችን የሚገኙት ክለቦች ቁጥር ከሦስት መቶ አይበልጡም፡፡ ከዚህ አንጻር ከውድድር ፎርማታችን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች አሉ፤ በሃገራችን የሊግ ፎርማቱ ውክልና ተኮር ስለመሆኑ በሰፊው እየተነሳ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአንድ የክልል ከተማ ላይ ከአንድ በላይ ክለብ አለመኖሩ የራሱን ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ በየክልሉ በርካታ ክለቦች እንዲኖሩ ምን ቢደረግ ይሻላል?

★ በከተሞች መካከል የኢኮኖሚ አለመመጣጠን አለ፤ እስካሁን የታየው መቀራረብ እጅግ ደካማ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሁሉም ነገር የነበረው በአዲስ አበባ ነው ማለት ይቻላል-እግርኳሱንም ጨምሮ፡፡ ድሮ ከክልሎች የሚገኙ ጥሩ ጥሩ ወጣቶች ወደ መዲናዋ ይመጣሉ፤ እዚህ ይጫወታሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በክልሎች አቅም ያላቸው ክለቦች ተመስርተው ያየንባቸው አጋጣሚዎች እምብዛም ነበሩ፡፡ አሁን ግን ወደዚያ አቅጣጫ እየሄድን ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ፦ ባለፉት ዓመታት ከደቡብ ክልል ወደ አራት ክለቦች በትልቁ የሊግ እርከን ሲወዳደሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን ግን ሌሎችም ክለቦች <Initiative> ወስደው ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ የፊፋ ህግ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን ጅምር ማበረታታት አለብን፤ ጎጂ የሆኑትን ነገሮች በምናስወግድበት ሁኔታ ላይ እየተወያየን መሄድ ያስፈልጋል፡፡ አንዱ የበላይ ሆኖ “ይህን እፈልጋለሁ፤ ይህን አልፈልግም፡፡” ማለት የለበትም፡፡ ሁሉም ችግሮቻችን ላይ የጋራ ምክክር በማድረግና መፍትሄ በመፈለግ የኢትዮጵያን እግርኳስ ማሳደግ ይቻላል፡፡ እኔ የምቃወመው አንድ ክለብ የሆነ ሰነድ አዘጋጅቶ “በዚህ መልኩ መጓዝ አለበን፡፡” ብሎ የሚያደርገውን ሒደት ነው፡፡ ማን ነው አንድን ክለብ የኢትዮጰያ ክለቦች ወኪል ያደረገው? ሁሉም ክለቦች ተጋብዘው እኩል ቢወያዩና የጋራ ስምምነት ላይ ቢደርሱ ለውጥ ይመጣል፡፡ “በአዲስ አበባ የምንገኝ ክለቦች የራሳችንን ሊግ እንመሥርት፡፡” የሚለው አቋም ለእኔ ውድቀት ነው፡፡ ውሳኔውን <Politically>ም ብናየው ያው ውድቀት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጋራችን እንድትሆን እንደመሥራት “እነዚያም በዚያ ይሂዱ፤ እኛም በእዚህ እንሄዳለን፡፡” ማለት ውድቀት ነው፡፡

በነገራችን ላይ ሁሉም ነገር የሃገሪቱ የፖለቲካ ነጸብራቅ ነው፡፡ ማናችንም ከዚያ ውጪ መሆን አንችልም፡፡ ስለዚህ “እግርኳሳችንን ከፖለቲካው እንዴት እንነጥለው? በምን መንገድ ስፖርቱን የሰላም መድረክ እናድርገው?” የሚለው ሐሳብ ላይ በጎ መንፈስ መያዝ አለብን፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ እግርኳሳዊ በሆነ ቋንቋ እንወያይ፡፡ የምናገረው ክለብ ወክዬ አይደለም፤ ይልቁንም አሰራሩን ታቃውሜ እንጂ፡፡ እኔ የማንም ክለብ ደጋፊ አይደለሁም፤ ማንም አካል አልወከለኝም፤ ውክልናዬ የኢትዮጵያ እግርኳስ ነው፡፡ ‘አሁን የያዝነው መንገድ ሩቅ አያስኬደንም፡፡’ የምለውም በራሴ ሃሳብ ነው፡፡ ይህን የምናገረው ምን ልባል እንደምችል ስለማውቀው ነው፤ ተመክሮዬ ብዙ አሳይቶኛል፡፡ የሊግ ፎርማት ከመቀየሩ በፊት ሁሉም የሚመለከተው አካል ሰከን ብሎ በጥልቀት ቢያስብ መልካም ይመስለኛል፡፡ የክለብ አመራሮችና ደጋፊዎች ላይ ጥድፈት ይታያል፤ እስቲ ረጋ ብለው ይወያዩ፡፡ መቐለ ያደግሁባት ከተማ ስለሆነች ነው ደጋግሜ እያነሳኋ ያለሁት፤ እኔ ጉናን በማሰለጥን ጊዜ አይደለም ሃምሳ ሺህ ሰው ከአምስት ሺህ እስከ አስር ሺህ ተመልካች ስታዲየም ገብቶ የሚያየን ጊዮርጊስና ቡና ሲመጡ ብቻ ነበር፡፡ ይህን መሰል ሁኔታ ባየሁበት ከተማ እግርኳሱ እያበበ ሄዶ በዚህ ወቅት ሃምሳና ስድሳ ሺህ ሰው ወደ ስታዲየም ሲተም ሳይ ‘ እኔም እኮ ለዚህ ለውጥ የራሴን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡’ ብዬ ምንያህል እንደምኮራ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡ እኔ ብዙ ዓመታት ደብረ ማርቆስ ተጫውቻለሁ፤ ሜዳ መጥቶ የሚያየን ሰው አምስት ሺህ ሞልቶ አያውቅም፤ ባህርዳርም እንዲሁ አስር ሺህ አይጠጋም ነበር፡፡ ጎጃምን ወክዬ ጎንደርም ተጫውቻለሁ- እዚያም ተመልካቻችን እንዲሁ መጠነኛ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ እኛ እኮ ያለ ተመልካች ነው የተጫወትነውም-ያሰለጠነውም፡፡ አሁንስ? መንፈሳዊ ቅናት እስከሚያድርብን ድረስ የተመልካቹ ቁጥር ንሯል፡፡ ከገጠር ሁሉ ሳይቀር ሜዳ ገብተው ጨዋታ የሚከታተሉ ሰዎች እየታዩ ነው- ምንም ሳያውቁም ለእግርኳስ “ሆ!” ማለት ጀምረዋል፡፡ ይህ’ኮ የሚያኮራና እግርኳስ መስፋፋቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ‘ይህ ሒደት ለወደፊቱ የኢትዮጵያን እግርኳስ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም?’ ከሚለው አንጻር ብንዳስሰው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ የክለቦቹ አማካሪ ብሆን ‘መቐለ፣ ፋሲል፣ ጊዮርጊስ፣… እያልን ሳይሆን የኢትዮጵያን እግርኳስ ብለን ማሰብ ነው የሚበጀን፡፡’ ብዬ ሐሳቤን እሰጥ ነበር፡፡ ‘ እናንተ የያዛችሁት መንገድ ሃገራችን በእግርኳስ እነ ጋናን የምታሸንፍበትን አቅም ይፈጥርልናል ወይ? እነ ካሜሮንን የምንረታበት ዕድል ያመጣልናል ወይ?’ ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ ልዩነቶቻችንን በጸጋ ተቀብለን እንስራበት፤ ካልሆነ እንቀይረዋለን፡፡ እያንዳንዱ የየራሱን መድረክ ፈጥሮ መወዳደርማ መበታተን ነው- ያ እንዲሆን ደግሞ ፍጹም አንፈልገውም፤ መለያየትን እኮ አንወድም ጃል፡፡

1990 ሃገሪቱ በእግርኳስ የላይኛውሊግ ውድድር እርከኗን በአዲሱ የፕሪምየር ሊግ ፎርማት ስትቀይር የእግርኳስ ማኅበሩ ፕሬዘዳንት ኢንጂነር ግዛው ነበሩ፡፡ እግርኳስን በመላ ኢትዮጵያ የማስፋፋት ዓላማ ስለነበራቸው ነው የፎርማቱን መቀየር ያጸደቁት?

★ ትክክል! ፕሬዘዳንቱ ቀና አመለካከት ነበራቸው፡፡ ከእግርኳሱ ጎን ለጎን ኦሎምፒክ ኮሚቴንም አስተዳድረዋል፡፡ ውጤታማ ጊዜንም አሳልፈዋል፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖም ከአቶ መላኩ ጴጥሮስ ጋርም አብረው ሰርተዋል፤ እዚህ ላይ የአቶ መላኩ ጴጥሮስን አስተዋፅኦ ማሳነስ የለብንም፡፡ አቶ መላኩ በኮተቤ የተማረ የስፖርት ምሁር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም ቡልጋሪያ ሄዶ ሰልጥኗል፡፡ በወጣቶች ሥልጠናና በሊግ አመሰራረት ዙሪያ ከእርሱ የመነጩ ሐሳቦች በጣም ጥሩ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በፌዴሬሽኑ ብቃት ያላቸው አመራሮች ተሰባስበው ጠንካራ ቅንጅት የተፈጠረበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በነገራችን ላይ መላኩ አብሮ አጀጌ ነው፡፡ ለእንደርታ አውራጃም አብረን ተጫውተናል፡፡ እኔ ለመጨረሻ ጊዜ ከመቐለ ስወጣ ነው የተለያየነው፤ ስንወያይ የእግርኳስ አስተሳሰቡ በቀላሉ ሊረዱት የሚቻል ነበር፡፡ ኢንጅነር ግዛውም ሐሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ የሄዱት ርቀት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ይቀጥላል…


ክፍል ሦስትን ለማግኘት ይህን ይጫኑ :point_right: ክፍል 3