በአዳማ ከተማ ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የተሻገሩ ቡድኖች ታውቀዋል

የአዳማ ከተማ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጠናቀቁ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የተሸጋገሩ ክለቦች ተለይተው ታውቀዋል።

በ7:30 የተገናኙት ሀዲያ ሆሳዕና እና ጅማ አባ ጅፋር ሲሆኑ ሆሳዕናዎች 2-1 ማሸነፍ ችለዋል። የቀድሞው የጅማ አባ ጅፋር አጥቂ ቢስማርክ አፒያህ በ33ኛው ደቂቃ ሆሳዕናን ቀዳሚ ሲያደርግ ብዙም ሳይቆይ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ኤልያስ አሕመድ ወደ ጎልነት ቀይሮ አቻ ሆነው ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ እንደ አፒያ ሁሉ ከዚህ ቀደም ለጅማ የተጫወተው ፍራኦል መንግሥቱ በ63ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ነብሮቹን አሸናፊ ማድረግ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎም ሆሳዕና 4 ነጥቦች በመሰብሰብ አዳማ ከተማን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፍ ችሏል።

በቀጣይ የተደረገው የሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የውድድሩን የመክፈቻ ጎል ከቀናት በፊት አስቆጥሮ የነበረው ብሩክ በየነ በ59ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ሀዋሳ ከተማ ሁለቱንም ጨዋታ አሸንፎ ስድስት ነጥቦች የሰበሰበው ፋሲል ከነማን ተከትሎ በ3 ነጥቦች ወደ ግማሽ ፍፃሜ እንዲሸጋገር አድርጎታል።

ውድድሩ ሀሙስ በሚደረጉ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሲቀጥል 7:00 ላይ አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ፤ 9:00 ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና ይጫወታሉ። አሸናፊ ቡድኖችም በመጪው ቅዳሜ ለዋንጫ የሚፋለሙ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ