ቅዱስ ጊዮርጊስ የሳላዲን ሰዒድን ውል አራዘመ

በቢሾፍቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እያከናወነ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአንጋፋው አጥቂ ሳላዲን ሰዒድን ውል አራዝሟል፡፡

ከስድስት ዓመታት የግብፅ፣ አልጄርያ እና ቤልጅየም ቆይታው በኋላ በ2008 አጋማሽ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመልሶ ሲጫወት የቆየው ሳላዲን በተለይ በ2009 ቡድኑ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ረጅም ጉዞ ሲያደርግ ወሳኝ ግልጋሎት ማበርከት የቻለ ሲሆን ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በጉዳት ቢቸገርም በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ወሳኝ ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

ከክለቡ ጋር በዝግጅት ላይ የሚገኘው ተጫዋቹ ዐምና ካጋጠመው ተደጋጋሚ ጉዳት አገግሞ ሙሉ በሙሉ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ እና ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በክለቡ ለመቆየት ከስምምነት መድረሱንም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በተያያዘ ዜና ዐምና ጉዳት ገጥሞት ወደ ህንድ አምርቶ ህክምና ያደረገው የግራ መስመር ተከላካዩ መሀሪ መናም ከጉዳት ተመልሶ ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ