ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀድያ ሆሳዕና ፡ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ1 ወር መቋረጥ በኋላ ነገ በ9፡00 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ንግድ ባንክ ከ ሀዲያ ሆሳዕና በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል፡፡

በርካታ ለውጦችን አድርጎ የውድድር ዘመኑን የጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 7 ጨዋታዎች ያልተዋሃደ ቡድን ይዞ ቀርቧል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ ለቻን ውድድር መቋረጡ ከጠቀማቸው ቡድኖችም አንዱ ይመስላል፡፡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየትም የሊጉ መቋረጥ እንደጠቀማቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ ለተጫዋቾች ጥቂት የእረፍት ጊዜ ሰጥተን ወደ ልምምድ ተመልሰናል፡፡ መቋረጡም ሳይጠቅመን አልቀረም፡፡ በሂደት ቡድኔ ላይ መሻሻል እተመለከትኩ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል ጥሩ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግም ችለናል፡፡›› ብለዋል፡፡ አሰልጣኝ ጸጋዬ አያይዘውም ሀዲያ ሆሳዕና ግብ ለማስቆጠር የማይቸገር ቡድን በመሆኑ ጨዋታው ፈታኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ ሃዲያ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ በሊጉ በርካታ ግብ ካስቆጠሩ ቡድኖችም አንዱ ነው፡፡ ቶሎ ቶሎወደ ግብ መቅረብ እና አደጋ መፍጠር ይችላሉ፡፡ 90 ደቂቃ በሙሉ ፍላጎት የሚጫወቱ ተጫዋቾች በመያዛቸው ሊፈትኑን እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጉዳት እና በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን በውድድር ዘመኑ እምብዛም ክለቡን ማገልገል ያልቻለው ቢንያም በላ ከቻን መልስ ያለፉትን 3 ቀናት ልምምድ በመስራቱ ለጨዋታው ብቁ ነው፡፡

ሀዲያ ሆሳዕና የሊጉ አዲስ ቡድን ቢሆንም ባልተጠበቀ ሁኔታ በርካታ ግብ በማስቆጠር የሚበለጠው በመሪው አዳማ ከተማ ብቻ ነው፡፡ የአጥቂ ክፍሉን ያህል ጠንካራ ያልሆነው የተከላካይ መስመር በእረፍቱ ተጠቅሞ ተጠናክሮ እንደሚመለስ ይጠበቃል፡፡ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰም ሙሉውን የእረፍት ጊዜ ቡድናቸውን በማዘጋጀት ተጠምደው አሳልፈዋል፡፡

‹‹ ከሊጉ መቋረጥ በኋላ ለተጫዋቾቻችን እረፍት አልሰጠንም፡፡ ዝግጅታችን በጉዳት ምክንያት የተሟላ ነው ማለት ባይቻልም ጊዜውን ተጠቅመን ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡›› ሲሉ አሰልጣኝ ግርማ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ግርማ አክለውም ንግድ ባንክን ጠንካራ እና ደካማ ጎን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ተመልክቻለሁ፡፡ ቡድኑ ልምድ ያለውና ተረጋግቶ የሚጫወት ቡድን ነው፡፡ እንቅስቃሴያቸው ዝግ ያለ ሲሆን ረጅም ኳስን ይጠቀማሉ፡፡ ይህን እንደ ክፍተትም እንደ ጥንካሬም ተመልክተን ጨዋታውን ማሸነፍ ተዘጋጅተናል፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡

የሆሳእናው ክለብ ለረጅም ጊዜ በጉዳት ያጣውን የተዘራ አቡቴን ግልጋሎት የማግኘቱ ጉይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ ክለቡ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያልፍ ቁልፍ ሚና የተጫወተው ተዘራ እና ዘንድሮ ክለቡን የተቀላቀለው አሸናፊ ይታየው ከጉዳቱ ቢያገግምም ለጨዋታው ብቁ እንዳልሆኑ ተነግሯል፡፡  ከድሬዳዋ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበቱት ግብ ጠባቂው ጃክሰን ፊጣ እና ተከላካዩ ሔኖክ አርፊጮ የተጣለባቸው የ3 ጨዋታ ቅጣት የሚያበቃው ከንግድ ባንክ ጨዋታ በኋላ በመሆኑ ይህ ጨዋታ ያመልጣቸዋል፡፡

 

የቅርብ ጊዜ አቋም

ሁለቱም ቡድኖች ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና በ4 ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ሲይዝ ንግድ ባንክ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ያለው የነጥብ ርቀት 1 ብቻ ነው፡፡ ንግድ ባንክ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት የመጨሻውን ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ ሲሸነፍ ሀዲያ ሆሳዕና አቢዮ አርሳሞ ስታድየም ላይ ወላይታ ድቻን በአስደናቂ ሁኔታ 5-1 አሸንፎ ወደ እረፍት አምርቷል፡፡

ያለፉት 5 ጨዋታዎች ውጤት

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፡ አሸነፈ – አቻ – አቻ – አቻ – ተሸነፈ

ሀዲያ ሆሳእና – ተሸነፈ – አቻ – ተሸነፈ – ተሸነፈ – አሸነፈ

 

እርስ በእርስ ግንኙነት

ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ሲሳተፍ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ እንደመሆኑ ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሲገናኙ ነገ ለመጀመርያ ጊዜ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *