ኤሌክትሪክ ከ ሀዋሳ ከተማ ፡ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ1 ወር መቋረጥ በኋላ ከነገ እስከ ረቡእ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡ በ11፡30 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ኤሌክትረክ ከ ሀዋሳ ከተማ የሚፋለሙበት ጨዋታ የአምናውን ውዝግብ አስታውሷል፡፡ በ2007 የውድድር ዘመን 25ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ኤሌክትሪክ ሀዋሳን 6-0 ሲያሸነፍ አስቀድሞ ከመውረድ መትረፉን ያረጋገጠው ሀዋሳ ከተማ ከአቅም በታች ተጫውቷል በሚል ብዙዎችን ማወዛገቡ የሚታወስ ነው፡፡

ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ወደ ጎንደር ተጉዞ በዳሽን ቢራ 1-0 የተረታው ኤሌክትሪክ በጨዋታው በተፈጠረው ግርግር ምክንያት አሰልጣኙን እና ሁለት ተጫዋቾቹን በቅጣት አጥቷል፡፡ አምበሉ አዲስ ነጋሽ ዳኛውን ተማቷል በሚል በቀረበበት ሪፖርት ለአንድ አመት የታገደ ሲሆን አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ በግርግሩ ተሳትፈዋል በሚል 5ሺህ ብር እና 10 ጨዋታ ቡድናቸውን በሜዳ ላይ እንዳይመሩ ታግደዋል፡፡ የግራ መስመር ተከላካዩ አማረ በቀለም የ4 ጨዋታ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

ነገ ከሀዋሳ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታን ጨምሮ ቀጣዮቹን 10 ጨዋታዎች በረዳት አሰልጣኙ ኤርሚያስ ተፈሪ የሚመራው ኤሌክትሪክ በቅጣት ከሚያጣቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ አጥቂው ማናዬ ፋንቱን በጉዳት በነገው ጨዋታ የማያሰልፍ ሲሆን ሌላኛው የመስመር ተከላካይ አለምነህ ግርማ የጋብቻ ስነስርአቱን በዚህ ሳምንት የሚፈፅም በመሆኑ እረፍት ተሰጥቶታል፡፡ በግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ሁለቱንም ተጫዋቾች ያጣው ኤሌክትሪክ ዘንድሮ በመስመር አማካይነት ስፍራ ሲሰለፍ የቆየው አሳልፈው መኮንን ቦታውን ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት የጋብቻ ስነስርአቱን የፈፀመው ፍፁም ገብረማርያም ሌላው በነገው ጨዋታ የማይሰለፍ ተጫዋች እንደሆነ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እንደ ኤሌክትሪክ ሁሉ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት የነበረውን የመጨረሻ ጨዋታ የተሸነፈው ሀዋሳ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ ቡድኑን ወደ መልካም አቋም ለመመለስ እረፍቱን እንደተጠቀሙበትም አሰልጣኝ ውበቱ አበተ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

‹‹ እንደ እቅድ ስንዘጋጅ የነበረው ለየካቲት 5 ታሳቢ አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ጠንካራ አቋም ለመመለስ ስራዎችን ስንሰራ ነበር፡፡ ከኤሌክትሪክ የምናደርገው ጨዋታም ካለን የነጥብ መቀራረብ አንፃር ጠንካራ ይሆናል ብል እንጠብቃለን፡፡›› ብለዋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ ለነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት በርካታ ተጫዋቾችን አያሰልፍም፡፡ ለህክምና ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ተመስገን ተክሌ ፣ በረከት ይስሃቅ ፣ ሙሉጌታ ምህረት እና አስጨናቂ ሉቃስን ጨምሮ 7 ተጫዋቾች በጉዳት የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል፡፡ ጉዳት ላይ የነበሩት ኤፍሬም ዘካርያስ እና ኃይማኖት ወርቁ ለጨዋታው ብቁ መሆናቸው ለሃዋሳ ከተማ መልካም ዜና ሆኗል፡፡

 

የቅርብ ጊዜያት አቋም

ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ሁለቱም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነበሩ፡፡ በተለይም በሊጉ 13ኛ ረጃ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በ4 ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል የራቀ ሲሆን በውድድር ዘመኑ ድል ያሳካው ከብሄራዊ ሊጉ የመጣው ሀዲያ ሆሳእና ላይ ብቻ ነው፡፡ ከሃዋሳ በ1 ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኤሌክትሪክም ባለፉት አመታት የሚታወቅበትን የሚዋዥቅ አቋም ዘንድሮም ቀጥሎበታል፡፡

ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም

ኤሌክትሪክ – ተሸነፈ – ተሸነፈ – አቻ – አሸነፈ – ተሸነፈ

ሀዋሳ ከተማ – አሸነፈ – ተሸነፈ – አቻ – ተሸነፈ – ተሸነፈ

 

ታሪክ

ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረበት 1990 ጀምሮ በሁሉም የውድድር ዘመናት የተሳተፉት ሁለቱ ክለቦች ነገ በሊጉ ለ35ኛ ጊዜ ይገናኛሉ፡፡ በእስካሁኑ 34 የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውም በአጠቃላይ 93 ግቦች ከመረብ አርፈዋል፡፡ ካለግብ የተለያዩትም በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡ በአማካይ በጨዋታ 2.7 ግብ የሚቆጠርበት የሁለቱ ፍልሚያ በግብ መጠን ከለካነው ከሊጉ አዝናኝ ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡

የሁለቱን የእርስ በእርስ ጨዋታ በቁጥር እንዲህ አስቀምጠነዋል፡-

Electric Hawassa Facts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *