አአ ከተማ ዋንጫ | ተጠባቂው ጨዋታ በሰበታ ከተማ የበላይነት ተጠናቋል

በሁለተኛው ቀን የአዲስ አበባ ከተማ ተጠባቂ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 1ለ0 ረቷል፡፡

ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ 11 ተሰላፊ ዝርዝራቸው ውስጥ ያለ ተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካይ ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን እንደተጠበቀው ጨዋታው በርካታ የኳስ ንኪኪዎች የተደረጉበትም ሆኗል፡፡

በጨዋታው በተለይ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአመዛኙ ደቂቃዎች ኳስ በቆጥጥራቸው ስር የነበረ ቢሆንም ከጎላቸው ርቀው በቡና የሜዳ አጋማሽ ውስጥ በርከት ብለው ከሚገኙት የሰበታ ተጫዋቾች ጫናን ተቆቁመው ወደ ፊት ለመሄድ ሲቸገሩ ተስተውሏል፤ በዚህም የኢትዮጵያ ቡና አብዛኛዎቹ ቅብብሎች የጎንዬሽን የኋልዮሽ ሆነው ተመልክተናል፡፡

በአንጻሩ ሰበታዎች ከቡና በተሻለ ኳስ ሲይዙ በፍጥነት ወደ ፊት በሚደረጉ ቅብብሎች ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡

በግብ ሙከራዎች ረገድ በጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበው ሙከራ የተደረገው በ34ኛው ደቂቃ በረከት አማረ የሰራውን የማቀበል ስህተት ተጠቅሞ ናትናኤል ጋንቹላ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢልክም ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታል፤ በተመሳሳይ ፍርዳወቅ ሲሳይ በግራ መስመር በፍጥነት ሰብሮ በመግባት ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ናቸው ፤ በአንጻሩ ቡናዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን በተጨማሪ ደቂቃ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከሳጥን ውጭ ወደ ግብ በላከው ኳስ ማስመዘገብ ችለዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽም ከመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም የተለየ መልክ አልነበረውም ፤ በዚሁ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ62ኛው ደቂቃ ላይ አላዛር ከግራ አጥብቦ በመግባት ወደ ግብ የላካትና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በ76ኛው ደቂቃ ሰበታ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት በሀይሉ ቱሳ ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ተከላካዮ አዲስ ተስፋዬ ወሳኝዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በጨዋታውም በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመመረታቸው የተነሳ በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ጫና ውስጥ ቢገቡም የቡድኑ ተጫዋቾች በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ውስጥ ለጨዋታ እቅዳቸው ተገዢ በመሆን ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ዓለምአንተ ካሳ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ