የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ዋንጫ ዝግጅቱን ቀጥሏል

በታንዛኒያ አስተናጋጅነት በሚደረገው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ከጀመረ ሦስተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል፡፡

በአዲሱ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው እና ረዳቶቹ መሪነት በኢትዮጵያ ሆቴል ማረፊያቸውን ካደረጉ በኃላ ሰኞ ማለዳ ዝግጅታቸውን የጀመሩት ሉሲዎቹ በአዲስ አበባ ስታዲየም ብሔራዊ ቡድኑ በቀን አንድ ጊዜ እየተዘጋጁ ሲሆን አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውም ተጫዋቾቹ በየክለባቸው በልምምድ ላይ የቆዩ ስለነበር እና ተጨማሪ ልምምዶች ስለማያስፈልጉ ታክቲኩ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ እየተዘጋጁ እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ቡድኑ መጀመሪያ ለሀያ አራት ተጫዋቾች ጥሪ ያደረገ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ከሀዋሳ ከተማ የተመረጡት ግብ ጠባቂዋ ዓባይነሽ ኤርቄሎ በቤተሰብ ሀዘን እንዲሁም አጥቂዋ መሳይ ተመስገን ደግሞ በክለቧ በልምምድ ወቅት በገጠማት ጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል። በምትኩም የንግድ ባንኳ ግብ ጠባቂ ንግስቲ መዓዛ እና የመከላከያ አዲስ ፈራሚ ዐይዳ ዑስማን ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠርተው ለመተካት ችለዋል፡፡

ቡድኑ በቀጣይ ቀናት ከተለያዩ ቡድኖች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ሲጠበቅ የማልታው ሊግ ከአንድ ሳምንት በኃላ ወደ እረፍት የሚያመራ በመሆኑ የቢርኪርካራዋን አጥቂ ሎዛ አበራን በቡድኑ ውስጥ ለማካተት ጥረት ላይ መሆኑንም ሰምተናል፡፡

ከህዳር 5 እስከ 13 ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ከዩጋንዳ ጅቡቲ እና ኬንያ ጋር የተደለደሉት ሉሲዎቹ በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ አመሻሽ ወደ ዳሬሠላም የሚያመሩ ሲሆን ዓርብ ህዳር 5 የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ኬንያን በመግጠም ይጀምራሉ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ