ከ31 ቀናት መቋረጥ በኋላ ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች በቀጠለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ነገ በ11፡30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን በአዲስ አበባ ስታድየም ያስተናግዳል፡፡
የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ ሲዘጋጅ የቆየ ሲሆን በተለይም ዘንድሮ እያከበረ የሚገኘውን የ80ኛ አመት የምስረታ በአል ምክንያት በማድረግ ከኬንያው ጎር ማሂያ እና ከሱዳኑ ኤል-ሜሪክ ጋር ጨዋታ ማድረጉ ቡድኑን ይጠቅመዋል ተብሏል፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በጉዳት ላይ የሚገኘውና ለህክምና ጀርመን ከሚገኘው ሳላዲን በርጊቾ የማይሰለፍ ሲሆን የመስመር አማካዩ በኃይሉ አሰፋ እና ተከለላካዩ አስቻለው ታመነ በነገው ጨዋታ ላይ የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ አዲስ የፈረመው ናይጄርያዊው አጥቂ ጎድዊን ቺካ ለፈረሰኞቹ የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታውን ነገ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወላይታ ድቻ ከመጀመርያዎቹ 4 ጨዋታዎች ሶስቱን በማሸነፍ ጥሩ የውድድር ዘመን ጅማሮ ቢያሳይም በተከታታይ ሽንፈትን አስተናግዶ ለመንሸራተት ተገዷል፡፡ ድቻ ባለፉት ጨዋታዎች ድክመት እንዳሳየ ያመኑት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ክፍተቶቻቸውን ሊጉ በተቋረጠበት ወቅት ለመድፈን እንደሰሩ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ ባለፉት ጨዋታዎች የነበሩብንን ድክመቶች ለማስተካከል ጠንካራ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ራሳችንን መፈተሸም ችለናል፡፡ በአጠቃላ ከኛ የሚጠበቀውን ሁሉ አድርገናል፡፡ ስለዚህ ነገ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ጥሩ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡
በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ከባድ ጉዳት ያስተናገደው ዘላለም እያሱ ለማገገም ረጅም ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ ወላይታ ድቻ ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚገጥምበት ጨዋታ አይሰለፍም፡፡ ሌላው የቡድኑ አማካይ ኃይለየሱስ ብርሃኑም በጉዳት ከቡድኑ ጋር ወደ አዲስ አበባ አልተጓዘም፡፡
የቅርብ ጊዜያት አቋም
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ7 የሊግ ጨዋታዎች 1 ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት አስተናገዶ መሪው አዳማ ከተማን በቅርብ ርቀት እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በአንጻሩ ወላይታ ድቻ የመጨረሻዎቹን 3 ጨዋታዎች በሽንፈት በማጠናቀቅ የሰንጠረዡ ወገብ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡
ያለፉት 5 ጨዋታዎች ውጤት
ቅዱስ ጊዮርጊስ ፡ አሸነፈ – አሸነፈ – አቻ – አሸነፈ – አሸነፈ
ወላይታ ድቻ ፡ አሸነፈ – አሸነፈ – ተሸነፈ – ተሸነፈ – ተሸነፈ
የእርስ በእርስ ግንኙነቶች
ወላይታ ድቻ በ2006 ወደ ሊጉ ካደገ ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች 4 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ በሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ ግንኙነት ወላይታ ድቻ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሳይጠበቅ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያሸነፈ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለቱን ጨዋ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል፡፡